በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ በ17 ወረዳዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

0
1103

በአማራ ክልል በሰሜን ሽዋ ዞን ውስጥ ካሉት 24 ወረዳዎች በ17 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የበረሃ አንበጣ ተከስቶ ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት ማድረሱን የዞኑ የግብርና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡
በዞኑ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ እስካሁን በሌሎች አካባቢዎች ላይ ከተከሰተው መንጋ ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ ብዛት ያለው መንጋ እንደሆነ እና ለመከላከል አደገኛ እንደሆነ የሰሜን ሽዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ መሰረት ኃይሌ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
መንጋው በተከሰተባቸው በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች እንድሁም 131 ቀበሌዎች ከ61 ሺህ ሄክታር በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ሰብሎች እና ዛፎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ ከፍተኛ የመንጋ ብዛት ባለው የበረሃ አንበጣ ጉዳት ከደረሰው 61 ሺህ በላይ ሔክታር 22 በመቶ የሚሆነው እንደወደመ መሰረት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ስፍራዎች ላይ ያረፈባቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደሙም መሰረት አክለዋል፡፡
መንጋው ከተከሰተባቸው ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰብሎች ውስጥ እንደ ጤፍ፣ ገብስ፣ በርበሬ፣ ሽንኩርት፣ ማሾ የመሳሰሉት የምግብ ልማቶች እና በተለያዩ ተክሎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉ ተጠቁሟል፡፡
የበርሃ አንበጣው በዞኑ የተከሰተው ሰኔ 5/2012 እንደሆነ እና መነሻውን ከአፋር ክልል አድርጎ ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን እንደገባ የገለጹት የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ መሰረት ተናግረዋል፡፡ የበርሃ አንበጣው ከተከሰተባቸው ወረዳዎች ውስጥ ግሸ ራቤል፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ መሐል ሜዳ፣ መንዝ ቀያ እና ጣርማ በር ወረዳዎች ይገኙበታል፡፡
በዞኑ የተከሰተውን ከፍተኛ መንጋ ያለው የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ከክልል ግብርና ቢሮ እስከ ፌደራል ግብርና ሚኒስቴር ድረስ በጋራ በመሆን መንጋውን ለማባረር እና ለማዳከም የኬሚካል እርጭት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ፣ መንጋውን በአውሮፕላን ኬሚካል በመርጨት ለመከላከል እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በአውሮፕላን ኬሚካል እርጭት ተደርጎ መከላከል ያልተቻለበት ምክንያት መንጋው የሚያርፍበት ቦታ ምቹ ለርጭት ምቹ ባለመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መንጋውን ለመበተንና ለማዳከም የኬሚካል እርጭት ስራው እየተሰራ ያለው በሰው ኃይል በመሆኑ አስካሁን ድረስ የመከላከል ስራው ከአቅም በላይ እንደነበር መሰረት ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ በንፋስ ኃይል እና ያሰፈረበት ቦታ የሚመገበው ሲያጣ ወደ ሰሜን ወሎ ዞን እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ወደ ዞኑ የገባው የበርሃ አንበጣ መነሻው ከአፋር ክልል እንደሆነ የጠቆሙት መሰረት፣ የአፋር ክልል መንግስት እና የፌደራል ግብርና ሚኒስቴር መንጋውን ከመነሻው ለማዳከም ባለመስራታቸው ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተሰፋፋ መሄዱን ያነሱት መሰረት፣ መንጋው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የፌደራል ግብርና ሚኒስቴር እና የክልሉ መንግስት ከአፋር ክልል ጋር በጋራ በመሆን ከመነሻው የኬሚካል እስጭት በመርጨት መንጋውን ማዳከም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከመነሻው ማዳከም ካልተቻለ ወደፊትም ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል መሰረት አመላክተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከልና ለመቆጣጠር “የኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ ምላሽ ሰጪ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዕቅድ” ባዘጋጀው ፕሮጀክት የበርሃ አንበጣውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር 63 ሚሊዮን ዶላር እንደሚስፈልግ አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡
የዓለም ምግብና ግብርና ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል 175 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ግምቱን አስቀምጧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here