አዋሽ ባንክ 4 .1 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ከተመሠረተ 25ኛ ዓመቱን ያስቆጠረውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ባንክ አዋሽ ባንክ የ2012 ያልተጣራ፣ ኦዲት ያልተደረገና የተበላሹ ብድሮች ያልተቀነሱበት 4.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ በማስመዝገብ ከግል ባንኮች መሪነቱን ለአምስተኛ ዓመት ማስጠበቅ መቻሉን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰማች።

ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ ከአምናው የ3.3 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አንጻር የ25 በመቶ ብልጫ አለው። የባንኩ የሒሳብ ሪፖርት በውጪ ኦዲተሮች ሲመረመር አሁን ከተጠቀሰው አንጻር የተወሰነ ለውጥ ሊኖረው እንደሚችል ቢጠበቅም፣ ልዩነቱ ግን ከፍተኛ እንደማይሆን ባለፉት ዓመታት የወጡት የባንኩ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ለትርፍ መጨመር ምክንያቶች ከወለድ፥ ከውጪ ምንዛሬ ኮሚሽንና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኘው ገቢ መጨመር እንደሆነ ምንጮቹ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩ ከተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኘውን ገቢ (service charge) በመከለስ ገቢውን ሲያሳድግ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በጣም አትራፊ የሆነ የአገልግሎት ዘርፍ ሲሆን፤ መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ዝግ ማድረጉና በብሔራዊ ባንክ በኩል ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር መኖሩ ለትርፋማነታቸው ዐቢይ ምክንያት ተደርጎ ይገለፃል።

ዘርፉ ባለፉት አራት ዓመታት እያሳየ የመጣው ዕድገት ከመቼውም ጊዜ የበለጠና አገሪቱ ከምትገኝበት የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የተቀዛቀዘ የንግድና ኢንቨስትመንት አንጻር አስገራሚ እንደሆነ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አገሪቱ ከግጭት እያገገመች የመጣች ቢሆንም፣ በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና መንግሥት ወጪ መቀነስ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽኖ በመበራከቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተበዳሪዎች ብድራቸውን ለመመለስ እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል።

በተለይ ዘንድሮ በዓለማችን ላይ ከጥር ጀምሮ እንደዚሁም በአገራችን በመጨረሻው ሩብ ዓመት የተከሰተው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ከፍተኛ የንግድና ኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ ከማስከተሉም ባሻገር በርካታ የንግድ ድርጅቶች በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎችና የአቪዬሽን ዘርፍ ላይ ብርቱ ክንዱን እያሳረፈ ይገኛል።

በዚህም ምክንያት ሁሉም ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ በቀረበ መመሪያ መሰረት የብድር መክፈያ ጊዜዎችን ለማራዘም ተገደዋል። የቫይረሱ ስርጭት ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖውን ማሳረፍ ከመጀመሩ በፊት ምጣኔው ትንሽ የማይባል ብድር በሁሉም ባንኮች ዘንድ በተበላሸ ብድርነት ተመዝግቦ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት የባንኮች የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከስምንት በመቶ በላይ መሆኑ የባንክ ሥራ ኃላፊዎችን ብቻ ሳይሆን የማእከላዊ ባንኩን ገዢዎች ጭምር ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።

የተበላሸ ብድር የባንኮቹንም ሆነ የተቆጣጣሪውን የብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች እያስጨነቀ የመጣ ጉዳይ በመሆኑ አብዛኞቹ ባንኮች ዘንድሮ ትርፋቸውን ሲያሰሉ የተበላሹ ብድሮች ባይመለሱ የሚፈጠርን የኪሳራ ስጋት ለመቀነስ የሚይዙት መጠባበቂያ (provision) ከምን ጊዜውም በላይ ከፍ እንዲል መደረጉ አይቀርም።

የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉ ከመቼውም በላይ ውድድር የበዛበትና ዘርፉ ለአንድ አክሲዮን የሚያስገኘው አማካይ ትርፍ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሁንም ድረስ የባንክ አክሲዮን መግዛት አስተማማኝ የኢንቨስትመንት አማራጭ አድርገው ይቆጥራሉ። ለዛም ነው በአሁኑ ሰዓት 17 የንግድና አንድ የኢንቨስትመንት በድምሩ 18 ባንኮች በምሥረታ ላይ የሚገኙት።

ይሁን እንጂ የአዳዲሶቹ ባንኮች የመመሥረቻ ካፒታል ከቀደሞዎቹ አንፃር ከፍተኛ በመሆኑ በአንድ አክሲዮን የሚያስመዘግቡት ትርፍ እንደበፊቶቹ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ካለመቻሉም በተጨማሪ፣ ትርፍ የሚያስመዘግቡበት ዓመትም ሊራዘም እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይተነብያሉ። በተጨማሪም መንግሥት እየወሰደ ካለው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንፃር ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚያደርግበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ይጠቁማሉ። በባንክ ዘርፍ ትርፍ መዛቅ እያከተመ መምጣቱ አይቀሬ እንደሚሆን ከወዲሁ ያሳስባሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here