“እነ ጃዋርን ማሰሩ መፍትሔ አይሆንም“ ፕሮፌሰር መረራ ጉድና

0
677

በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር በተገናኘ የፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ መታሰር ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር መፍትሔ እንደማይሆን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

ፕሮፌሰሩ አያይዘውም እነ ጃዋር በብዙ ወጣቶች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት እና ድጋፍ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን በመጥቀስ እነሱን ማሰሩ ከመፍትሔው ይልቅ በእሳት ላይ እሳት መለኮስ ነው ሲሉም አክለዋል።

ከአርቲስቱ ግድያ ጋር ተያይዞ ችግር ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉትን እነ ጅዋር መሃመድን እና በቀለ ገርባን ከማሰር ይልቅ መንግሥት ወጣቱን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች የመረጋጋት አካል እንዲሆኑ ማድረግ እንደነበረበት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል። እነ ጅዋርን ማሰሩ የመተማመን ፖለቲካ እንደማይፈጥርም ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸዋል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት አሁን በተፈጠረው ችግር በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ፖለቲከኞችን ከማሰር ይልቅ መደራደር መልካም መሆኑን ጠቁመዋል።ፕሮፌሰር መራራ አክለውም አሁን የተፈጠረውን ችግር መንግስት ብቻውን ሚወጣው አይደለም ብለዋል።በመሆኑም ችግሮችን ለመፍታት የጋራ መተማመንን የሚያስችል የፖለቲካ አካሄድ መፈጠር እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
መንግስት ሰሞኑን የተፈጠረውን ግርግር ለማረጋጋት እና ለመቆጣጠር በሰለጠነ የፀጥታ ኃይል ሕይወትን ንብረትም እየጠበቀ ማረጋጋት አለበት ሲሉ ፕሮፌሰሩ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮያ ፖለቲካ ላለፉት 50 ዓመታት አንድ ቀውስ ሌላ ቀውስ እየወለደ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ አካሄድ እስካሁን በቀውስ የተቃኘ በመሆኑ ከችግር መውጣት እንዳልተቻለ የጠቆሙት መራራ፣ አገሪቱን እና ህዝቦቿን ሰላማዊ ወደሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመመለስ እና ሰላሟ የተረጋጋ አገር ለመፍጠር እንደ አገር ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥር የፖለቲካ አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
እንደ ፕሮፈሰር መራራ ገለጻ በኢትዮጵያ አሁን የተፈጠረው ችግር አንዱ የአገሪቱ ፖለቲካ ትኩሳት መለኪያ ነው ብለዋል።ፕሮፌሰሩ አክለውም የ2012 ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምከንያት መራዘሙን ተከትሎ ሽግግሩ በአንድ ወገን ብቻ የተወሰነ መሆኑ ብሔራዊ መግባባትና መተማማን እንዳልፈጠረ አመላክተዋል።በመሆኑም በኢትዮጵያ መሰረታዊ የሆነ በአንድ ወገን ብቻ ያልተገደበ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡

እንደ አገር ሊፈነዳ የሚችል ፖለቲካዊ ፍጥጫ እንደተደረም መረራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።በመሆኑም በኢትዮጵያ እንደ አገር 110 ሚሊዮን ህዝብን በአንድ መንገድ ይዞ የመሄድ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ያመላከቱት ፕሮፌሰር መራራ፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ቢኖራቸውም የአሽናፊነት እና ተሸናፊነት አካሄድ ቀርቶ ሁሉንም ያማከል የአሸናፊነት ፖለቲካ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።በፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል አለመግባባት ቢኖርም አለመግባባትን አጣጥሞ መሐል መንገድ መገናኘት እንደሚያስፈልግ መረራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ለሁላችንም የምትበጅ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንደት እንፍጠር በሚለው ጉዳይ ላይ ልዩነት ቢኖርም የሁላችንንም ጥቅም በሚስከብር ሁኔታ መተማመን እና መነጋገር ወቅቱ የሚፈልገው ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ፕሮፌሰር ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞኛ ሙዚቃ አቀንቃኙ አርቲስት ሀጫሉ ሁንደሳ ሰኔ 22/2012 ምሽት ሶስት ስዓት በአዲስ አበባ በጥይት ተመቶ መገደሉን ተከትሎ፣ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ከ80 በላይ ሰዎች ሂወት ሲልፍ፣ በንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት መድረሱን መንግስት ተናግሯል።የአርቲስቱን ሞት ምክንያት በማድረግ በአድስ አበባ ችግር ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል ተብለው ጅዋር መሀመድ፣ በቀለ ገርባ፣ የባልደራስ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ፣ የባልደራስ ምክትል ስንታየሁ ቸኮል እና ሌሎችም የነሱ ግብረ አባሮች የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here