በአርሲ ዞን እና ሻሽመኔ ከተማ ኹከቶች አልበረዱም

0
897

በኦሮሚያ ክልል የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ የተከሰተው ችግር በአርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ እና በሻሸመኔ ከተማ ኑሬሳ ወራዳ ችግሩ አሁንም መኖሩን እና አስጊ የሚመስል ድባቡ መኖሩን የክልሉ መንግሥት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ተባብሶ ሊቀጥል የቻለበትን ምክንያትም የክልሉ መንግሥት የኮምኒኬሽን ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የተፈጠረው ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም እና የሰው ሕይወት መጥፋት በቀላሉ እንዳይበርድ እንዳደረገው እና ተባብሶ እንዲቀጥል ምክንያት እንደሆነም አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በአካባቢው የደረሰው እና ተባብሶም እየቀጠለ ያለው ጥፋት ብሔርን እና ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ጌታቸው ባልቻ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በሌሎች አካባቢዎች እስካሁን ከተፈጠረው ጥፋት ይልቅ በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመሆኑ ከፍተኛ የሰው ሕይወትና የንብረት ጥፋት ተከስቷል ብለዋል፡፡

በአንፃሩ ችግሩ የተከሰተባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች አንፃራዊ መረጋጋት እንደሚታይ እና በአንዳንድ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እየተመለሱ መሆኑን የኮሙኒኬሽን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት የክልሉ መንግሥት በኹሉም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በጉዳዩ የተባበሩ፣ የተሳተፉ እና ያስተባበሩ ተጠርጣሪዎችን እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ አሁንም እርምጃ የመውሰድ ሥራው በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥልም ኃላፊው አመላክተዋል፡፡

የአርቲስቱ የትውልድ ቦታ የሆነችው አንቦ ከተማ በአሁኑ ሰዓት የተረጋጋ ሰላም እንዳላት የገለጹት ጌታቸው፣ በአርቲስቱ ቀብር ስነ ስርዓት ላይ በተፈጠረ ችግር የኹለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና በ14 ሰዎች ላይ መቁሰል አደጋ መድረሱንም ጌታቸው አክለው ገልጸዋል፡፡ እንደ ክልሉ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ችግር የፈጠሩት ችግሩን ውጥን ያዘጋጁት እና መሩት የሕወሀት አመራሮችና ደጋፊዎች እና ከነሱ ጋር ተባብሮ ችግሩን የፈጠረው ራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ብድን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሀላፊው አክለውም አርቲስቱን ያስገደሉትም ቀብሩን ያስተጓጎሉትም ሕውሀት እና ኦነግ ሽኔ ከውጭ ሀይሎች ጋር በመተባበር አገሪቱን የማተራመስ እና ለውጡን ለማደናቀፍ ያለመ አጀንዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ችግሩ በሁሉም የክልሉ ከተሞች በሚባል ልክ ተከስቶ የነበረ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ አሁን ላይ ችግሩ የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች ችግሮችን ለማረጋጋት የክልሉ መንግስት ህግን የማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም ህዝብን የማወያየት ሥራ እየሰራ መሆኑን አመላከተዋል፡፡

እንደ ክልሉ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ገለጻ የችግሩ መነሻ የኦሮሞን እና የአማራን ህዝብ በብሔር ለማጋጨት የታሰበ በመሆኑ፣ አሁንም ክልሉ ላይ ሁለቱን ብሔር የሚጋጭ ነገር ለመፍጠር የሚተጉ አካላት ስለሚኖሩ ክልሉ ፖሊስ ለሌሎች ብሔሮች ከለላ እና ጥበቃ አላደረገም በማለት አላማቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙት ስልት እንጅ የክልሉ ፀጥታ ኃይል እንዲህ አይነት ተግባር አልፈፀመም ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ ከፀጥታ ሀይልም ከአማራርም እንዲህ አይነት ችግር ሊፈጽሙ ይችላሉ ያሉት ጌታቸው፣ የፀጥታ አካላት የውግንና ስራ ሰርተው ከተገኙ ችግሩ ተጣርቶ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በክልሉ የ87 ሰዎች ሂወት እንዳለፈ እና ከ200 በላይ ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰ ሲሆን፣ እንደ ክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ ገለጻ የሟቾችና የቁስለኞች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here