ያልተመዘገበውስ?

0
498

ባለፉት ቀናት በድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ሰላም ማጣቶች ተስተውለዋል። በዚህም ምክንያት መገመት እንደሚቻለው ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል በመንግሥት በኩል ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ነው። ታድያ ኢንተርኔት ቢኖር ኖሮ፣ ሰሞኑን በሴቶች ጉዳይ ላይ መነጋሪያ ይሆን የነበረው ምን ይሆን?
ይመስለኛል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለይ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሴቶችን ጥቃት ጨምሯል የሚለው ላይ የሰጡት ሐሳብ አነጋጋሪ ይሆን ነበር። በእርግጥ በንግግራቸው ‹በኮሮና ምክንያት ቤት ውስጥ ሰዎች ስለተቀመጡ የቤት ውስጥ ጥቃት ጨምሯል የሚለው ትክክል አይደለም› የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል። ሆኖም ግን ይህን እንዲሉ ያስቀመጡት ምክንያት በእጅ ያሉ መረጃዎች ተጨባጭ ባለመሆናቸው ነው።

በሴቶች ላይ በየጊዜው ጥቃቶች እንደሚደርሱ፣ አልፎም ሕጻናት ወንዶችም ጭምር የጥቃት ሰለባ እንደሚሆኑ የታወቀ ነገር ነው። የአዘቦቱም ግን በሚገባ በሰነድ የተቀመጠ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እነዚህን መረጃዎች አቀናጅተው የሚይዙ አካላት ጥቂት ሲሆኑ፣ ይፋ ለማድረግም አንዳች ምክንያት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ አይናገሩትም። በጠቅላላውስ የመረጃ አያያዛችን መች የሚመሰገን ነውና!

የቤት ውስጥ ጥቃት፣ በሕጻናት ላይ በሴቶችም በወንዶችም የሚደርሱ አሰቃቂ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ጥቂት ናቸው ለማለት አያስደፍርም። እንደውም መች ፈንድተው ችግር እንደሚፈጥሩ ለመገመት እንኳ አልተዘጋጀንም። ዛሬ የሚታየው በትንሽ መድረክ ላይ የሚደረግ የሚመስል የሴቶች ጥያቄና አጀንዳ፣ ነገ በምን መልክ ሊፈነዳ እንደሚችል ልብ ብሎ የሚመለከተው አካል ያለ አይመስልም።

እናም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብና ንግግር መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ተጠናቅረው ካለመቅረባቸው አንጻር ተገቢ ሊሆን ይችላል። ችግሮች መኖራቸውን ግን አለሳልሶ ማየትና ተጠያቂነቱን ባህልና ስርዓት ላይ ማኖር በቂ አይደለም። ዛሬ የአስገድዶ መድፈር ሰለባ የሆኑ ወንድ ሕጻናት ተስፋቸው ምንድን ነው? የሴቶቹስ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ምን ያስከትላል? ከተነገሩት ይልቅ ያልተሰሙት አይብሱም ወይ? መረጃዎች አልተጠናቀሩምና በአግባብ አለመቅረባቸው ችግሩ እንደሌለና ተመሳሳይ ትኩረት እንዳያገኝ ያደርገዋል ወይ?

እነዚህ የእኔ ጥያቄዎች ናቸው። ምክንያቱም ሁላችንም በየአካባቢያችን ልብ ብለን ካየን ልንታዘብ የምንችላቸው ችግሮች አሉ። ሕግን ማጥበቅ ላይ ለሚመለከታው አካላት ኃላፊነቱ እንደተሰጠ ሁሉ፣ ማስፈጸም ላይም ተጨባጭና ‹ፍትህ አለ› የሚያሰኙ ተግባራት እንዲታዩ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ይህን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወርደው እንዲያደርጉት አይደለም፣ ትኩረት እንዲሰጥበት ካዘዙ ግን ከጉዳዩ ዐይናቸውን እንደማይነቅሉ ስለሚታመን፣ ውጤት ለማምጣት ያስችላል። አዎን! ያልተመዘገቡት ይቆዩንና ተመዝግበው የተያዙ ጉዳዮችም ላይ ችግር አለ። አንዲትን የ10 ዓመት ልጅ ከ2 ዓመት ገደማ በፊት አስገድዶ የደፈረና በፍጥነት ተይዞ ለሕግ የቀረበ ሰው በማግስቱ በዋስ ተፈትቶ፣ ‹አሁን ጉዳዩ ምን ደረሰ› ሲባል፣ ‹ዋሱም ሆነ ተጠርጣሪው ያሉበት ጠፋ› የሚል ነገር መስማት አያምም?

መረጃ አያያዝና ጥንቅር መስተካከል እንዳለበት እሙን ነው። ችግሮችን ለመቅረፍ ባለመፍትሔውም ችግሩን በሚገባ እንዲያየው ያስፈልጋልና፣ የሕመሙን ምልክቶች ከመናገር አልፎ መድኃኒት ለማግኘት የሚያመውን ቦታ እንደሚያሳይ ታካሚ፣ ትክክለኛ መረጃዎችን ማሳየት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔርና የዜግነት ፖለቲካ እያሉ ጉዳዩን የሙግታቸው አንድ አካል እንዳደረጉት ሁሉ፣ የሕጻናት ወንዶችና ሴቶችን ጥቃትና ጉዳት ተጠቃሽ አጀንዳቸው ውስጥ እንዲካተት ማድረግ ይቻላል። ለውጥ ለማምጣት ተሰሚነት ይቀድማል!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here