ጊዜና ዘመን

0
758

ጊዜ እንደ አየር ሁሉ ትልቅ ዋጋ አለው። ግን እንደ አየር እንደልብ የሚገኝ ሳይሆን እየገፋ ሲሄድ የሚያልቅ ሀብት ነው። በተለይም ለሰው ልጅ ለእያንዳንዱ በእድሜ ተወስኖ እና ተለክቶ የተሰጠው የጊዜ ገደብ አለ። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በተለይ ከተሜ ብዙውን ጊዜ በጊዜ አጠቃቀም ላይ ሥሙ በጥሩ አይነሳም። እንዲህ ሆኖ ሳለ ውጪአዊ ጊዜ አጠቃቀም ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ሲታከሉ ደግሞ ጉዳዩ ‹በእንቅርት ላይ…› መሆኑ አይቀሬ ነው። መቅደስ ቹቹ ይህን ጉዳይ በማንሳት ወቅታዊ የአገር ሁኔታዎች በተለይ አሁን እያለቀ ባለው ዓመት ምን ያህል ጊዜን እያባከኑ እንደሆነ አንስተዋል።

ጊዜ ውዱ ሀብት ነው። ለሰው ልጅ ሲሰጥም ተመጥኖና ተወስኖ እንጂ እንደ አሸን የሚሰጥም የተሰጠም አይደለም። የአገራችን እናቶችና አባቶች ከምኞታቸውም ከእቅዳቸውም አስቀድመው ‹እድሜና ጤና ይስጠን እንጂ…› የሚሉት ለዚህ ነው። በእድሜ የሚሰፈረው ለሰው ልክ ለእያንዳንዱ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ማለቂያ አለው። መጠኑም የሚታወቀው ሲሰጥ ሳይሆን ሲያበቃና ሲያልቅ ነው። የጊዜ ዋጋንም የምናውቀው ያኔ ነው።

አሁን ጊዜያችን በብዙ አስጨናቂ ሐሳቦችና ጉዳዮች ተውጧል። ይህም በዓለማችንም ሆነ በአገራችን በምናስተውላቸው በቂ ምክንያቶች የተነሳ ነው። ለምሳሌ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ማንሳት እንችላለን። ይህ በዓለማችንም በአገራችንም የተነሳ ወረርሽኝ በእንቅስቃሴያችን ላይ፣ ባሰብናቸው ክዋኔዎችና በያዝናቸው እቅዶች ላይ የማይሻር እንቅፋት ሆኖብናል። 2012 ዓመት እንዳልነበር ይቆጠር ወይስ እንዳለፈ እንዝለለው?

ይህን ጥያቄ ተማሪ ለሆነ ትልቅ ጥያቄ ነው። መመረቁን ለሚጠብቅ፣ የመሰናዶ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ጓግቶ ላለና እንደ አዲስ ልጆቹን ትምህርት ቤት ሊልክ ላሰበ ወላጅ፣ እንኳ 2012 ቀጣዩ 2013 ራሱ እንዴት እንደሚሆን ከወዲሁ ስጋት ሞልቷል።

ያም ብቻ አይደለም። ብዙዎች ያሰቡትን እንዳያደርጉ፣ መንገዱ ባይዘጋ እንኳ በሥነ ልቦና ጫና እና በጭንቀት ምክንያት በዓመቱ ውስጥ ከፈለጉበት እንዳይደርሱ የተለያዩ ኹነቶችም በምክንያትነት ለማስቀመጥ ግድ ብሏቸዋል። ኮቪድ 19 ብቻ አይደለም። በአገራችን ምክንያት ፈልገው አልያም ምክንያት ፈጥረው የሚከሰቱ ኹከቶችን በየጊዜው እንታዘባለን። እነዚህም በአካልም በሥነ ልቦናም ከሚያሳድሩት ጫና የተነሳ ጊዜን መጠቀም አይደለም ስለ ነገ ለማሰብ እንኳ ፋታ አይሰጡም።

ይህን ስንል የግብጽን ነገርም አብረን ልናነሳ እንችላለን። የህዳሴውን ግድብ መገንባትና የውሃ ሙሌት ሊጀመር መሆኑ ያልጣማትና ያልተዋጠላት ግብጽ ኢትዮጵያን ለማወክና ከእቅዷ ለማስታጎል የተለያዩ አጀንዳዎችን ልትፈጥር እንደሚችል ይገመታል። ታድያ ብጥብጡ መነሻው ግብጽ ብትሆንስ? አገራቸውን ተከፍሏቸው የሚሸጡ፣ ለመቀበሪያ እንኳ አገር እንደሚያስፈልግ የማያውቁ ሰዎች በብዛት ቢኖሩስ?

እነዚህ ስጋቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጊዜያችን ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ። በተመሳሳይ የአንበጣ መንጋ የሚያሳስበው ብዙ ነው። በተለይ መደበኛ መገናኝ ብዙኀንን የሚከታተልና የአንበጣ መንጋው የሚያወድመው የሰብል መጠን፣ የሚጓዝበት ርቀትና የሚራባበትን ፍጥነት ለተከታተለ፣ ‹አገራችን ረሀብ ቢገባስ!› ብሎ መጨነቁ አይቀርም።

በድምሩ በአገራችን ያንን ተከትሎም በየአንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ 2012 ከፍተኛ ተጽእኖ አምጥቷል። ‹የሆነ ነገር ቢኖር ነው እንጂ ካልጠፋ ዓመት ከመቶ ምናምን ዓመታት በኋላ እንዴት ዘንድሮ ላይ ሙሉ የፀሐይ ግርዶች ሊታይ ቻለ!› የሚሉም ተሰምተዋል። ‹እውነትም ሠኔ እና ሰኞ ገጠመብን!› የሚሉም አይጠፉም።

በድምሩ ግን በእያንዳንዱ ዓመት በሀሳብም ይሁን በቁስ ያሰባሰበውን ለቀጣይ እንደሚያጠራቅም ሰው ከሆንን፣ ይህኛው ዘመን ለወደፊት የሚያቀብለንና በአስተሳሰባችንና አመለካከት፣ አኗኗርና አቀራረባችን ላይ የሚፈጥረው ለውጥ ይኖራለ።

እነዚህ ሁሉ በአእምሮ የሚፈጠሩ የሐሳብ ክምሮችና ጭንቀቶች በጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖን ያሳርፋሉ። ሁሉም ዋጋ የለውም ብሎ ከማሰብ ጀምሮ በሚሠሩት ሥራ ላይ ቸልታ፣ በሚወዱት ነገር ላይ የፍላጎት መቀነስ፣ ነገን አሻግሮ ለማየት መቸገርና መሰል ስሜቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ይህን ጉዳይ እኔ በጨዋ አነጋገር ብዙ ልገልጸው የሚገባ አይደለም። ይልቁንም የሥነ ልቦና እና ሥነ አእምሮ ባለሞያዎች በጉዳዩ ብዙ የሚሉት ይኖራቸዋል። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፣ ጊዜና ዘመን። በየትኛውም አቅጣጫ ብናይ ከላይ እንዳነሳናቸው ዓይነት ውጪአዊ ኹነቶችና ውስጣዊ ሰላም ማጣትና አለመረጋጋቶች ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም አይፈቅዱልንም።
ኢዮብ ማሞ (ዶ/ር) ካበረከቷቸው መጻሕፍት መካከል አንደኛው ‹የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ› ይሰኛል። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ2004 ለሕትመት የቀረበውና በ155 ገጾች የተቀነበበው ይህ መጽሐፍ ጊዜና አጠቃቀማችንን በሚመለከት ሰፋ ያሉ ሐሳቦችን አጋርቷል።

ሰባት ምዕራፎችና አንድ የማጠቃለያ ክፍልን የያዘው መጽሐፉ፣ የጊዜን ትርጉምና አስፈላጊነት፣ በአግባቡ የመጠቀምን ወሳኝነት፣ የባህል ተጽእኖውን፣ ከተግባር ጋር የማቀናጀት ጥበብን እና የጊዜ አጠቃቀም ቅደም ተከተልን መረዳትን እንዲሁም ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮችን በሰፊው ተመልክቷል። በተጨማሪም የጊዜ አጠቃቀም እንቅፋቶች አሉ ሲል በሦስት ከፋፍሎ አስቀምጧቸዋል።
እነዚህም ሙያ ነክ እንቅፋቶች፣ ውጪአዊ እንቅፋቶች እና ሥነ ልቦናዊ እንቅፋቶች ናቸው። ይህን ጉዳይ በሸፈነው የመጽሐፉ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንዲህ የሚልና ሳሙኤል ማይልስ ከተባለ ሰው የተወሰደ አጭር ቃል ተቀምጧል። ‹የባከነ ሀብት በሥራ ይተካል፣ የባከነ እውቀት በጥናት ይተካል፣ የጠፋ ጤንነት በመድኃኒት ይመለሳል፣ የባከነ ጊዜ ግን ለዘለዓለም ጠፍቷል›

ሰዎች ጊዜን በአግባብ እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ይሆናሉ ከተባሉ ኹነቶች መካከል ሙያ ነክ የተባሉት እንቅፋቶች ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህንም መጽሐፉ ሲዘረዝር የተግባር ዝርዝር አለማውጣት፣ ለሥራ ቀጠሮንና የጊዜ ገደብን አለመመደብ፣ ለሥራው የማይስማማ ሰዓትን መመደብ፣ ለሥራ በቂ ጊዜ አለመመደብ እንዲሁም የአሠራር ሂደት ጉድለት ተብለው ተቀምጠዋል።
ከዛ ባለፈ የተቀመጡት ደግሞ ውጪአዊ የተባሉት የጊዜ አጠቃቀም ላይ ያሉ እንቅፋቶች ናቸው። እነዚህ ደግሞ ከሰዎች ቁጥጥር ውጪ ከሆኑ ሁኔታዎች የሚመነጩ ናቸው፣ እንደ መጽሐፉ ገለጻ። ‹‹አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ እንቅፋቶች እንዳይከሰቱ መቆጣጠር አይቻልም። ለተከሰቱ ሁኔታዎች ግን የምንሰጠውን ምላሽ መቆጣጠር ይቻላል።›› ይላል መጽሐፉ።

በዚህ ውስጥ ደግሞ በቀዳሚነት የሰፈረው የድካምና ሕመም ስሜት ነው። እነዚህም በሕክምና የሚገኙ የቫይረስና የባክቴሪያ ተዋህስያን የሚያደርሱት ብቻ ሳይሆን፣ ስሜትን የሚያዝሉም ጭምር ናቸው። መጽሐፉም ‹‹አንድ ሰው አካሉ፣ ስሜቱና አእምሮው ሲዝል ጊዜውን በአግባቡ ለመጠቀም ያዳግተዋል›› ሲል ያስቀምጣል። ይህም ስሜት አንዳንድ ጊዜ ጊዜአዊ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ በዚህ ስሜት ውስጥ ያለማቋረጥ የሚኖሩ ሰዎች አሉ።

ይህ የዝለት የድካም፣ እርሱን ተከትሎ የሚመጣ የሕመም ስሜት ምንጩ ምን እንደሆነ ማወቅ ተገቢ እንደሆነ መጽሐፉ ያትታል። እንቅልፍ ማጣትም ቀንደኛው ጉዳይ ነው ሲል፣ ሕመምንም በተመሳሳይ ደረጃ ያስቀምጠዋል። ከመጽሐፉ ቃል ቃል በቃል እንዋስ፣ እንዲህ ይላል፤
‹‹ከአካል ሕመም ባሻገር የስሜትም ‹ሕመም› በጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ታላቅ ተጽእኖ አለው። ከተለያዩ አሉታዊ ገጠመኞች የተነሳ ስሜት ሲወድቅ፣ ሲጎዳና ድብርትና የሀዘን ጫናዎች ማንነት ላይ ሲደራቡ፣ ጊዜን በተገቢው ሁኔታ የማዋቀር ፍላጎቱም ሆነ ጉልበቱ አይኖርም››

በተጨማሪ የኑሮ ሁኔታ ለውጥም ተጠቃሽ ነው። ይህም አሁን ላይ በአገራችን እያየነው ያለነው ዓይነት ለውጥ ነው። በተለይም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ፣ የትምህርትና የሥራ መደበኛ እንቅስቃሴ መታጎል ወዘተ የኑሮ ሁኔታችን ላይ ለውጥ አምጥተዋል። እንደ መጽሐፉ ገለጻ ከሆነ ታድያ እነዚህም ጊዜን በአግባቡ እንዳንጠቀም የሚያግዱ ናቸው። እንዲህም ሲል ያስቀምጣል፤

‹‹አብዛኞቹ ለውጦች ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ከሆነ የኑሮ ሂደት የሚመጡ ናቸው። የለመድነውና የተደላደልንበት የኑሮ ሁኔታ በድንገት ሲለወጥ የጊዜአችንንም አወቃቀርና ሂደት ይነካዋል።››
ግርግር የሞላበት አካባቢ ሌላው ሲሆን፣ ቀድሞ የተረጋጋና አንድ ሰው የራሱን ሐሳብ ብቻ በራሱ መንገድ ሊከውን ካሰበበት መንገድ ውጪ በከባቢው ላይ ያላሰበው አዲስ ግርግርና ኹነት ሊከሰት ይችላል። በሕይወታችንም ድንገቴ ክስተቶች እንደሚኖሩ ማሰብም ሆነ እነርሱን ታሳቢ አድርጎ ማቀድ ስለሌለ፣ ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ይበላል። በዚህ ላይ ታድያ ‹ብልሀትን የመፍጠር ሸክም በእኛ ላይ ነው›› ሲል መጽሐፉ ይጠቅሳል።

ከዚህ ውጪ በመጽሐፉ የተጠቀሰውና ከሰዎች ቁጥጥር ውጪ የሆነ ውጪአዊ ተጽእኖ የሰዎች ተጽእኖ ነው። በማንኛውም አጋጣሚ በሥራችን ከሰዎች ጋር መገናኘታችን አይቀርምና፣ አካሄዳችን የእነዚህን ሰዎች ፍላጎትና ምርጫ እንዲሁም አካሄድ እንዲከተል ግድ ሊለን ይችላል። ይህም ቀላል የማይባል ውጪአዊ ተጽእኖ ነው። ከዚህ ባለፈ ሥነ ልቦናዊ እንቅፋችም የጊዜአችን አጠቃቀም ላይ ተጽእኖ ማሳረፋው አይቀሬ ነው።

ይህን እንዴት ማለፍ እንችላለን? በአለመረጋጋትና በኹከት ምክንያት ከቤት ወጥቶ ያሰበውን መሥራትና መከወን ያልቻለ ሰው አገር ሰላ እስኪሆን ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬውን ጠብቆ ጊዜ እስኪያልፍ ከመጠቀበቅ ውጪ አማራጭ ላይኖረው ይችላል። ያም ሆኖ በቤት ውስጥ መቀመጥ ግድ በሚልበት ጊዜም ሐሳብ ላይ መሥራት ትልቅ ቁምነገር ነው።
መጽሐፉ እንደሚለው ደግሞ በቅድሚያ ችግሮች መኖራቸውን ማመንና መቀበል ተገቢ ነው። ከዛም በተጓዳኝ የረጅም ጊዜ እቅዶችን መያዝና ይህ ጊዜ እንደሚያልፍ ማመን ያስፈልጋል። ይህም በእቅዶቻችንና ሰዎች በአቅማቸው ሊያደርጉ በሚችሉት ላይ ተነሳሽነታቸው እንዳይጠፋ፣ ፍላጎታቸውን እንዳይባክን ያስችላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here