የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በወቅዊ ተፈጥሮ መንገድ የውሃ ሙሌት መጠኑ እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ስለሺ በቀለ (ኢንጅነር) ገለጹ።
የግደቡ የውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን የሳታላይት ምስሎች እያሳዩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባሳለፍነው ሳምንት መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል። ነገር ግን አሁን ላይ እየጨመረ የመጣው የግድቡ የውሃ ሙሌት በተፈጥሯዊ መንገድ እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ የግድቡን ውሃ ሙሌት አለመጀመሩን የውሃና መስኖ ኢነርጅ ሚኒሰቴሩ ጠቁመዋል።
የሳታላይት ምስሎችን መሰረት በማድረግ የግድቡ ውሃ ሙሌት እየጨመረ መሆኑ በዓለማቀፍ ሚዲያዎች መገለጹን መሰረት በማድረግ፣ ግብጽ የኢትዮጵያ መንግሥት የግድቡን የውሃ ሙሌት በይፋ መጀመሩን በተመለከት አስቸኳይ ምላሽ ይስጠኝ ስትል ለኢትዮጵያ የማይዋጥላትን የተለመደ የአዛዥነት ቅዥተዋን አንፀባርቃለች።
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን ይፈታ በሚል በቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ፣ የሦስቱ አገራት ድርድር ወደ አፍሪካ ኅብረት ቀርቦ እንዲታይ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ፣ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት መሪነትና በተጋባዣ ባለሙያዎች ታዛቢነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል።
ሆኖም በግብጽ በኩል እየታየ ባለው ስግብግብነት ያለ ስምምነት መበተኑን ሚኒስትሩ በቲውተር ገጻቸው አስፍረዋል። ሚኒስትሩ አክለውም ድርድሩ ያለ ስምምነት የተበተነው ግብጽ ያቀረበችው ሐሳብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳና ወደፊት ተጠቃሚነቷን የሚቃረን የአልገታ ባይነት ክርክሯን ስለቀጠለች መሆኑን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የድርድሩን ሂደት በተመለከት ለአፍሪካ ኅብረት ሪፖርት ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል የሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር ውጤታማ ቢሆንም ባይሆንም፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሐምሌ ወር የመጀመሪያ ሳምንት በይፋ ሙሌት እንደሚጀምር መግለጹ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012



