የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስርአት በአዲስ መልክ ሊሰጥ ነው

0
666

የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስርአት በአዲስ መልክ እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ጤና ሚኒስቴሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳስታወቁት፣ የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስርአት በአዲስ መልኩ ይሰጣል።
ስርአቱ አሁን ካለበት የተበጣጠሰ እና ደካማ አሰራር ወደተሻለ እና ወጥነት ወዳለው ስርአት ለማደራጀት በማለም የተዘጋጀ ነው ብለዋል። ወቅቱን የሚመጥን የጤና ባለሙያዎች የሙያ ማጎልበቻ ስርአት መቅረፅ እና መተግበር እጅግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ገልፀዋል።
ስርአቱ በዋናነት የጤና ባለሙያውን ብቃትና ክህሎት ለማጎልበት ያለመ ቢሆንም፣ የጤና አገልግሎቱን ጥራት በማሻሻል በኩል የማይተካ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል። የሙያ ማጎልበት ስርአት በሁሉም ደረጃ እና የሙያ ዘርፍ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን እውቀት እና ክህሎት ከማሳደግ በተጨማሪ ሙያ እድገት ተወዳዳሪነትን ያድጋልም ብለዋል።
አሰራሩን ከጤና ባለሙያዎች የሙያ ጤና እድሳት ጋር በማያያዝ ዋነኛው ብቃት ቁጥጥር መመዘኛ እንደሚሆን አስታውቀዋል። ስርአቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን መመርያ መሰረት በማድረግ እንደሚተገበር የገለፁት ሚኒስትሯ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የሙያ ማጎልበቻ ስርዓት በምን መልኩ ተፈፃሚ እንደሚሆን ሚኒስትሯ በቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡም ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here