የሰው ልጅ ከጅማሬው ጀምሮ በማኅበረሰባዊ ጎኑ እየጎለበት እስከ መጣበት እና አሁን ደግሞ ወደ ቀደመው ብቸኝነት ሕይወት መመለስ እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ጉዳዮችን ፈጥሮ አጎልብቷል። በጥንታዊው ሰው የተጀመሩት እና ሰውን ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ከፍ በማድረግ የዝግመት ዕድገቱን ካፋጠኑት አንዱ ታዲያ መረጃ ልውውጥ ነው። ጥንታዊው ሰው በዋሻዎች፣ በአለቶች እና በዛፎች ላይ ቅርጽን እየቀረጸ ስለ አደን ውሎው፣ ስላጋጠመው ድንቅ እና አስገራሚ ቀልብን ስለሚገዙ ጉዳዮች መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ለዘመናዊው ሰው የመረጃ ልውውጥን አሻራ አሳርፎ ለማለፉም ትልቅ ተምሳሌት ነው።
በዘመናዊውም ሰው ቢሆን ከአስተዳደር እና ከአዋዋል ጥየቃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የአገርና የሕዝብ መረጃዎችን እለመስከ መቀባበል የሚደርስ ሒደት መኖሩም እሙን ነው። ይህ ታዲያ የመረጃ ልውውጥም ለዘመን ጋር እየዘመነ ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው እየተደነገገ እና መረጃዎችም የሚተላለፉበት መንገድም እየረቀቀ መምጣት ጀመረ። ቀደም ሲል በአገር አቋራጭ ነጋዴዎች፣ ሲራራዎች፣ እና ተጓዦች ሲከወን የነበረው የመረጃ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ማስተላለፍ ሒደት አሁን ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ዘምኖ በእጃችን ላይ ባለው ተንቀሳቃሽ ስልኮች መምጣት ጀምሯል።
ከዙህም ጎን ለጎን ታዲያ በስልክ እና መሰል መገልገያዎች ወደ እያንዳንዳችን መዳፍ የወረደው መረጃ ታዲያ ዋነኛው ተዋናዩ እና አጋዥ መሳሪያው በየነ መረብ ነው። ቀደም ሲል የሰው ልጅ መሰረታዊ ነገሮችን የማግኘት ሰብዓዊ መብት እንዳለው እናውቃለን ስንማረውም አድገናል። ልብስ፣ ምግብ እና መጠለያ ታዲያ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነገሮች መሆናቸውንም እንደ ዳዊት ስንደግም አድገናል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በየነ መረብ አራተኛው የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ ሊያገኛቸው ከሚገቡ መሰረታዊ ነገሮች አንዱ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመዝግቧል። ይህ ጉዳይ ታዲያ ዕለት ጉርሱን ለማግኘት ደፋ ቀና ለሚለው እና ከድኅነት ወለል በታች ለሚገነው በርካታው የዓለም ሕዝብ ከቅንጦትም ያለፈ ቅንጦት እንደሚሆንም አይጠረጠርም፤ ለዚህም ደግሞ የመንግስታትን እርምጃ መመልከት ብቻ በቂ ነው።
ወደ አገራችን ስንመጣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ወሰደቻቸው እና እንደ ራሷ አገር ሕግ አድርጋ የተቀበለቻቸው ሕግጋት መኖራቸው አይዘነጋም።ይሁን እንጂ ሕዝብ የበይነ መረብ ተተቃሚነቱን በሚመለከት ግን በግልጽ የተቀመተ ጉዳይ እንደሌለ ግን መታዘብ ተጨማሪ ምርምር አይጠይቅም። ለዚህም ማረጋገጫ ታዲያ በየጊዜው የሚወሰደው በየነ መረብን የማጥፋት እና ሕዝብ ከመረጃ እና ከግንኙነት እንዲቋረጥ የማድረግ ተግባር አንዱ እና ዋነኛው ነው። ከቀደመው ግንባር ኢህአዲግ የመጨረሻ ዕድሜ ጀንበር ጥቂት ጊዜያትን አስቀድሞ በአገር ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶችን መንግስት በቁጥጥር ስር ለማዋል በመጀመሪያ ደረጃ በየነ መረብን መዝጋት እንደ አማራጭ የወሰደው ጉዳይ ነበር። ያኔ ታዲያ ሕዝብ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ብቻ ሳይሆን ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር ኢትዮጵያ እንደ አገር የተቆራረጠችበት መጥፎ አጋጣሚ እንደነበርም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ አሁንም አገርን በለውጥጎዳና እየመራኋት ነው፤ የቀደመው እና አሮጌው የጭቆና ስርዓት ላይመለስ ተቀብሯል በሚል ወደ ሕዝብ ልብ ውስጥ ለመግባት የሚፍጨረጨረው አዲሱ መንግስት ታዲያ ከሰሞኑ ለአጋጠሙት ችግሮች በየነ መረብን በመዝጋት ቀደመውን መፍትሔ ሲከተል ታዝበናል። አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ማስቀመጡን ያልተገነዘበው የለውጡ ኃይል ታዲያ በይነ መረብን በመዝጋት አለመረጋጋቶችን ለመፍታት ሲሞክርም ታይቷል። እነዚህ የቀደመው እና ያረጁ ያፈጁ ግጭቶችን ለማብረድ የሚወሰዱ እርምጃዎች ታዲያ ሊቀጥሉ እንደማይገባ አዲስ ማለዳ አበክራ ታስገነዝባለች። ሕግን እናስከብራለን ተብሎ ሕግ ቢጣስም ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳትም በውል ታይቶ የተጠና መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይም ነው ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች። ከተለመደው እና ባህላዊ አሰራር ወጥተን ወደ ዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ወለድ የሕይወት ዘየ እየተመነደግን ነው እያልን በምንለፍፍበት በአሁኑ ወቅት ለቀናት ብሎም ለሳምንታት በየነ መረብን ዘግቶ ሕግን ለማስከበር መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆንም መንግስት ሊገነዘብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አቋሟን ትገልጻለች።
በተለይም ደግሞ ቀድሞም በቋፍ ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ጥላውን ያጠላበት ዓለም አቀፉ ወረርሽኝን በመታገል ለመሰንበት በሚደረገው ትግል ላይ ይባስ ብሎ ዋነኛ የመገበያያ ሜዳ እየሆነ የመጣውን በይነ መረብ በማጥፋት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማድረግ ሊቆም የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ታምናለች። በዚህ ብቻ ሳይበቃ የእስካሁኑ የበይነ መረብ መዘጋት እና በከፊልም ደረጃ መለቀቅ በቂ እንዳልሆነ እና የተንቀሳቃሽ ስልኮች የበይነ መረብ አገልግሎትም መለቀቅ እንደሚኖርበት እና ወደ ነበረበት አኗኗር ሕብረተሰቡ መመለስ እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ግልጽ ያለ አቋሟን ታስቀምጣለች።
በይነ መረብ በተዘጋባቸው ቀናት የንግድ እንቅስቃሴዎች ተገተዋል፣ የግል እና የሕዝብ ድርጅቶችም ለቀናትም ቢሆን አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፣ በዚህም የተነሳ ሕዝብ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ይልቅ በበይነ መረብ መቋረጥ ብዙ ጊዜ ተጎድቷል። በእርግጥ አገርን በማስቀደም የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ በመንግስት በኩል የተሔደበት መንገድ እና ቁርጠኝነት ይበል የሚያሰኝ እና የሚያስመሰግን ቢሆንም በይነ መረብን በመዝጋት ጠቃሚ እና ከአሉባልታ የራቁ መረጃዎች ወደ ሕዝብ እንዳይደርሱም አድርጎ ሰፊ ጫና አድርሷል። በተለይም ደግሞ በግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ያሳደረው ጫና ይህ ነው የሚባል አይደለም። የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሰሯቸውን እና ወደ ሕዝብ ቢደርሱ ጠቃሚ መረጃዎች ሊሆኑ የሚችሉ መርሃ ግብሮችን ወደ ጎረቤት አገር በበረራ አስተናጋጆች በኩል በመላክ ወደ ሚሰራጩበት አገር እንዲሻገሩ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ውጣ ውረድ ውስጥም ገብተው ነበር። ይህን በሚመለከት ታዲያ አዲስ ማለዳ አራተኛ መንግስት ነው እተባለለ የሚለፈፍለትን እና በተግባር ግን የማይኖረውን የሚዲያውን ምቹ አሰራር እንዲፈጠርለት ከማሰብ አንጻር በይነ መረብን ማቋረጥ ከፍተኛ በደል ማድረስ እንደሆነም ታምናለች።
በሕትመት ሚዲያውም ቢሆን የበይነ መረብ አለመኖር ከባድ ጫና አሳድሯል። ውስን ከሆነው ተደራሽነት አንጻር ጋዜጣ እና መጽሔት ለአንባቢያን በስፋት መዳረስ የሚችሉበት አገር አይደለችም ኢትዮጵያ። ይህንንም ተከትሎ ታዲያ በይነ መረብን በመጠቀም ታትመው የወጡ መረጃዎችን ጋዜጦችን ወይም መጽሔቶችን ላላገኙ አንባቢያን በነጻ በማቅረብ መረጃዎችን የማሰራጨት ስራም ሲሰራ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በየዓመቱ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነው የሕትመት ሚዲያም ከመረጃ እጥረት እና ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት እያለበት በበይነ መረብ መቋረጥ ደግሞ ይባሱኑ ሲቀጭጭ መታዘብ ተችሏል። አዲስ ማለዳ ይህን ጉዳይ መንግስት በይደር የሚያስቀምጠው እና በቸልተኝነት የሚየው ጉዳይ ሳይሆን በአንክሮ በመከታተል መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል ስትልም ታሳስባለች።
የእስካሁኑ እርምጃ ያለፈ እና ወደ ኋላ ተሒዶ መመለስ የሚቻል ባይሆንም፤ መንግስት ለከእንግዲህ ወዲያው ይህን አይነት እርምጃ ለመውሰድ ከመወሰኑ በፊት ቆም ብሎ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ እና ችግር መገንዘብ ይኖርበታል ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትደመድማለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012


