የ2012 የመንግሥት ዓመታዊ ግዢ ከ50 በመቶ በታች ቅናሽ አሳየ

0
470

የመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2012 በጀት ዓመት የ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብቻ ግዢ በመፈጸም ከ50 በመቶ በላይ የግዢ ቅናሽ በማሳየት ዓመቱን አገባዷል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እቅዱን መፈጸም እንቅፋት እንደሆነበት ለአዲስ ማለለዳ የተናገረው አገልግሎቱ፣ በቀደመው የ2011 በጀት ዓመት 14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግዢ ፈጽሞ እንደነበር አስታውቋል።

በ2012 በጀት ዓመት ያቀደውን ያህል እንዳላሳካ ያመላከታው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የታየው ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ሲሆን፣ ባለፈው በጀት ዓመት 14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግዢ ሲፈፀም በተገባደደው ዓመት ግን የስትራቴጂክ ግዢዎችን ጨምሮ የ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ግዢ ብቻ ተፈጽሟል።
ከዛም በተጨማሪ ባለፈው በጀት ዓመት 94 ሚሊዮን ብር ንብረት ማስወገድ ያከናወነ ሲሆን፣ በአሁኑ 2012 በጀት ዓመት ግን 50 ሚሊዮን ብር ንብረት ማስወገዱን ነው ተቋሙ ለአዲስ ማለዳ የተናገረው።

የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ መልካሙ ደፋሊ እንደተናገሩት፣ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ካቀደው ውስጥ 85 በመቶውን ማሳካት ችሏል። ነገር ግን ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩበት። ተቋሙ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንደኛው የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ንብረት ግዢ መፈጸም ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ጥቅም ላይ የዋሉትንና አገልግሎታው ያበቃውን ደግሞ የማስወገድ ሥራ ነው። በግዢው በኩል የማዕቀፍ ስምምነት እና አስትራቴጂክ ግዢ የሚባሉ ሲኖሩ፣ ይሄንንም የሚጠቀሙት ፌዴራል መሥርያ ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው።

ከኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ጋር የሚገናኙ እቃዎች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አንድ ምድብ ሲሆኑ፣ የጽሕፈት መሣሪያ፣ የፅዳት እቃዎች፣ የቢሮ እቃዎች፣ ፕሪንተር እና ፎቶ ኮፒ ማሽን በአጠቃላይ ወደ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ግዢ እንደተፈጸመ ጠቅሰዋል። ነገር ግን የስትራቴጂክ ግዢዎችን ጨምሮ በድምሩ 5.1 ቢሊዮን ብር ግዢ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

ንብረት ማስወገዱን በሚመለከት አገልግሎቱ የተለያዩ ንብረቶች ማስወገድ ላይ እንደሚሠራ ገልፀው፣ ተሽከርካሪዎች፣ ያገለገሉ የቢሮ እቃዎች ከዚህ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ተሽከርካሪን በሚመለከት የ46 መሥርያ ቤቶች 110 ተሽከርካራዎችን 43 ሚሊዮን ብር ሽያጭ መፈፀሙን ነው የተቋሙ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

በዚህ ዓመት ከሌላው ዓመት ለየት በሚል ሁኔታ መስተጓጎል ነበረ የሚሉት መልካሙ፣ ይህም የሆነው የተለያዩ የሚከፈቱ ግዢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲራዘሙ በመደረጉ ነው ብለዋል።
ከዛም በተጨማሪ አቅራቢዎች እና ተጫራቾች እንዲገኙ የሚያደርግ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክንያት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብ በመከልከሉ ግዢዎቹ በተደጋጋሚ ለማራዘም በመገደዳቸው ካለፈው ዓመት ጋር ልዩነቱ እንዲሰፋ አድርጓል በማለትም ሁኔታውን አስረድተዋል።
እንደ መልካሙ ገለጻ ከሆነ ካለፈው አመት ግዢ ከተፈፀው 14 ቢሊዮን 11.1 የስንዴ ግዢ ነበር ብለዋል።

ያለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ከግዢ ኤጀንሲ ጋር በመሆን ውይይት ከተደረገ በኋላ ጨረታው ከተጫራቾች የተወሰነ ሰው እንዲወከል፤ ጨረታው ደግሞ ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲከፈት እና በሌላ አካል ደግሞ እንዲገመገም አድርገን የተወሰነውን ግዢ ማከናወን ችለናል ነው ያሉት።

ተቋሙ በሚቀጥለው በጀት ዓመት እቅድ እንዳስቀመጠ እና ዘንድሮ ሳይሳኩ የቀሩትን ግዢዎች የመኪና ጎማ፣ የደንብ ልብስ በተደጋጋሚ አቅራቢዎቸ ቴክኒክ መመዘኛውን አልፈው የሚሳተፉ ካልሆነ በቀር ስለማይቀላቀሉ በተደጋጋሚ ተሰርዞ ነበር። ስለዚህ ይህንን በሚመለከት ተጨማሪ እቅድ እንደተያዘ መልካሙ ተናግረዋል።

ነገር ግን ተሽከርካሪ እና ሌሎች ስትራቴጅክ ግዢዎች የሚባሉትን በመንግሥት መሥርያ ቤቶች እቅድ መሰረት አድርገን ነው የምንፈጽመው በማለትም የሕዝብ ግንኙነቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here