በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ የተከሰሱ የእምነት ክህደት ቃል መሰማት ተጀመረ

0
802

ባለፈው ዓመት ሠኔ 15/2011 በተፈጸመው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ እና ሕገ መንግሥትን በኃይል ለመናድ በመሞከር የተከሰሱ ተከሳሾችን የመጀመሪያ የእምነት ክህደት ቃል የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 8/2012 መስማት ጀመረ።

ፍርድ ቤቱ ሠኔ 7/2012 በዋለው ችሎት ተከሳሾች የመጀመሪያ የእምነት ከህደት ቃላቸውን በቀጣዩ ቀን ሠኔ 8/2012 እንዲሰጡ ውሳኔ ማሳለፉ የታወቀ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ በ2011 ሠኔ 15 በተፈጸመው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ እና ሕገ መንግሥትን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል ተብለው በተጠረጠሩ 55 ሰዎች ላይ የተለያዩ ክሶችን በመመስረት የመጀመሪያ የእምነት ክህደት ቃል መቀበል መጀመሩን የተከሳሾች ጠበቃ በሙሉ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ተከሳሾች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ምርምራ በማካሄድ ፍርድ ቤቱ ሠኔ 7/2012 በዋለው ችሎት ብይን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ለተከሳሾች የክስ ዝርዝር ጋር የምስክሮች ስም ዝርዝር አልቀረበም በማለት የተከሳሾች ጠበቃ ላቀረቡት ተቃውሞ፣ የምስክሮች ሥም ዝርዝር ያልተያዙ ተከሳሾች ስላሉ ለደኅንነታቸው ሲባል ለተከሳሾች መገለጽ የለበትም ሲል ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ የምስል (የቪድዮ) ማስረጃ አለኝ በማለት ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ሐሳብ ላይ፣ የምስል ማስረጃውን ዐቃቤ ሕግ ለተከሳሾች እና ለፍርድ ቤቱ በኮፒ እንዲያቀርብ ብይን መስጠቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ክስ ከተመሰረተባቸው ተከሳሾች ውስጥ 49 የሚሆኑት በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ክሳቸውን እንደሰሙ እና ስድስቱ ተከሳሾች እስከ አሁን ድረስ በሕግ ቁጥጥር ስር አለመዋላቸውን ጠበቃ በመሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ፍርድ ቤቱ የኮቪድ-19ኝ ወረርሽኝን ባገናዘበ መልኩ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል በየተራ ለመስማት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ሐምሌ 8/2012 ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል በሰማበት ጊዜ አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት ሻንበል ሙላት ጌትነት በሕግ ቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን አልሰጡም።
ኹለተኛ ተከሳሽ ሻንበል ልደቱ አባተ፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ሻለቃ አዱኛ፣ አራተኛ ተከሳሽ ሻለቃ ታደሰ፣ አምስተኛ ተከሳሽ ሃምሳ አለቃ በላቸው ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። እንደ ጠበቃው ገለጻ ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት ከኹለተኛ እስከ አምስተኛ ያሉ ተከሳሾች በተከሰሱበት ወንጀል እንዳልተሳተፉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ዐቃቤ ሕግ በ55 ተከሳሾች ላይ ያቀረበው ክስ መዝገብ የሚጠራው አንደኛ ተከሳሽ በሆኑት በሻንበል ልደቱ አባተ ሲሆን፣ ተከሳሾች በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸው ክስ ከአንድ እስከ 35 ድረስ ክስ የተመሰረተባቸው እንዳሉ ጠበቃው ጠቁመዋል። በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ከመሰረታቸው ክሶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በመግድልና ሥልጣን ለመቆጣጠር በመሞከር፣ በሰው መግደል ወንጀል የሚሉት ናቸው።

ፍርድ ቤቱ 49 ተከሳሾችን በተከታታይ ቀናት የእምነት ክህደት ቃላቸውን በመቀበል ላይ ነው።
እስከ አሁን በሕግ ቁጥጥር ስር ያልዋሉ ስድስት ተከሳሾችን ፖሊስ ከአካባቢው ማግኘት አልቻልኩም በማለት ለፍርድ ቤቱ በማቅረቡ፣ ተከሳሾች በሌሉበት ክሳቸው እየታየ ነው። ተከሳሾች ሐምሌ 22/2012 እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ በጋዜጣ ጥሪ እንደተደረገላቸው ጠበቃ በሙሉ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ሠኔ 15/2011 በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር ከተማ ከፍተኛ የአማራ ክልል አመራሮች እና በአዲስ አበባም በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄነራል ገዛዒ አበራ ላይ የተፈጸመው ግድያ ኢትዮጵያ አንገት ያስደፋ እለት እንደነበር ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here