አትክልት ተራ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተገነባ ነው

0
1222

በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ስፍራ ብቻ ተወስኖ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው አትክልት እና አሳ መሸጫ ስፍራ ወይም በተለምዶ አትክልት ተራ በዐስሩም ክፍለ ከተሞች እንደሚከፈት እና እስከ አሁን አራት ክፍለ ከተሞች ላይ ተጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የገበያ ማእከላቱ በዐስሩ ክፍለ ከተማዎች ላይ ሲሆኑ፣ የሚሸፍኑትም ቦታ በትንሹ ከ15 ሺሕ እስከ 20 ሺሕ ሔክታር እንደሚሆን ተገልጿል። እስከ አሁን ተሠርተው ለተጠናቀቁት ማእከላት ደግሞ ከ20 ሚሊዮን እስከ 27 ሚሊዮን ብር እንደወጣባቸው አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ተገንብተው ያለቁት የገበያ ማእከላት ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ አትክልት እና ፍራፍሬ ማእከላት ሲሆኑ፣ የቁም እንስሳት መሸጫ ማእከላት በአራት ቦታዎች ማለትም በንፋስ ስልክ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ቂርቆስ እና የካ ክፍለ ከተማ ይገኛሉ ተብሏል። በየካ ክፍለ ከተማ ካራሎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ የሚገኘው ማእከልም ግንባታው አልቆ ማክሰኞ ሐምሌ 14/2012 የሚመረቅ እና ወደ ሥራ የሚገባ የቁም እንስሳት ገበያ ማእከል እንደሆነ ነው የንግድ ቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል ሙኤሳ የገለጹት።

አራቱ የቁም እንስሳት መሸጫ ማእከላት ተጠናቀው ወደ ሥራ የገቡት ንፋስ ስልክ፣ ቂርቆስ እና የካ ላይ ነው ያሉት ዳንኤል፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ደግሞ ኮልፌ ሙሉ በሙሉ አልቆ ወደ ሥራ ማስገባት ብቻ እንደቀረ እና የንፋስ ስልኩ ማእከል ግን ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ እንደሚገኝ አክለው ተናግረዋል።

የገበያ ማእከሉ የሚገነባው 95 በመቶ በላይ የሚሆነው የብረታ ብረት ውጤቶችን ጨምሮ በአገር ውስጥ ምርት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አያይዘው፣ እነዚህ የአትክልት እና የቁም እንስሳት መሸጫ የንግድ ማእከላት ቢገነቡና ወደ ሥራ ቢገቡም ከዚህ ቀደም የነበሩት አትክልት ተራዎች እንደማይቀነሱ እና ሥራ እንደማያቆሙ ገልጸዋል።

ይሄ መሆኑ የአካባቢው ተደራሽ ለማድረግ፣ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ እንዲሁም ዘመናዊ የግብይት ስርአትን ለመፍጠር ጠቃሚ ይሆናል። የዚህ ግንባታ ዋና ዓላማም ከሁሉም ገበያ ማእከላት ከፍተኛ ተጠቃሚ እና ሰው ጭንቅንቅ የሚስተዋልባቸው አትክልት ተራዎች ለኅብረተሰቡ በቅርብ እርቀት እንዲገኙ ለማድረግ፣ ወደ ገበያ ማእከላቱ ለመድረስ ኅብረተሰቡ የሚያወጣውን የትራንስፖርት ወጪ እና ድካሙንም ለመቀነስ ታስቦ እንደሆነ ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ቦታዎች ኅብረተሰቡ ባለበት ቅርብ ርቀት ላይ ሲሆን ከዋናው ገበያ በሚገኙበት ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ለሚሠሩት የገበያ ማእከላት ከአዲስ አበባ መስተዳድር የቦታ ርክክቡ እንዳልተጠናቀቀ እና ቀጣይ ክፍለ ከተሞች ላይም ያለውን ሥራ የመሥራት ሂደት በቀጣይ እንደሚኖር ተናግረዋል።
በርካታ ነጋዴ መነሻው አትክልት ተራ ላይ ነው የሚሉት ዳንኤል፣ እነዚን በዐስሩም ክፍለ ከተማ ሲደረጉ ሁሉም ከክልሎች ጋር የራሳቸው የሆነ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስችላልም ብለዋል።
መንግሥት እዚህ ያሉትን ነጋዴዎች ክልል ካሉት ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ዋና ሰንሰለት በመሆን ያገለግላል ያሉትም ሲሆን፣ ይህም ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች በመሃል በመግባት የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጉ የነበረውን ችግር ለመቆጣጠር ዋነኛ መፍትሔ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here