የመጀመሪያው የልውጥ ሕያዋን (GMO) የጥጥ እርሻ ውጤታማነት አወዛገበ

0
831

በኢትዮጵያ በጥጥ እርሻ ላይ የተጀመረው የልውጥ ሕያዋን (GMO) ውጤታማነት ከመነሻው አወዛጋቢ መሆኑ ተጠቆመ።
ውዝግቡ የተነሳው ይህ ለግብርና ምርታማነት ፍቱን መፍትሄን ያመጣል ተብሎ የቀረበው ቴክኖሎጂ ከነባሩ አገር በቀል ዝርያ ጋር ሲነፃፀር እምብዛም ለውጥ እንዳልተገኘበት በመታወቁ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የልውጥ ሕያዋንን (GMO) ምርምር ውጤታማነት ደግፈው ዝርያዎቹን እያስተዋወቁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ግን ጉዳቱ እንዳያመዝን ያለውን ስጋት እየገለፀ ይገኛል። የቁጥጥር ሥራውን እንዲሠራ ሥልጣኑ የተሰጠው የአካባቢ፣ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጧል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የልውጥ ሕያዋን ጥጥ ዝርያ (Bt cotton) ባሳለፍነው የምርት ዘመን በግል እርሻ ደረጃ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ጋምቤላ ክልል ላይ በሚገኙ አምስት የሰፋፊ እርሻ ባለቤቶች 130 ሔክታር መሬት ላይ መዘራቱን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ልማት ዘርፍ ኃላፈ መሰለ መኩሪያ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እነዚህም JKCH-1050 እና JKCH-1947 የተሰኙት የልውጥ ሕያዋን የጥጥ ዝርያዎች በአንድ ኪሎግራም 28 ዶላር ወጪ 1400 ኪሎግራም ዝርያዎች ከህንድ አገር ተገዝተው ለገበሬዎቹ የተከፋፈሉ ሲሆን፣ በ130 ሔክታር ላይ እንዲዘሩ ተደርጓል። ይህም ዘር ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል በመሆኑ በየዓመቱ አዳዲስ ወይንም ሌላ ዘር መገዛት እንዳለበትም ተገልጿል።
GMO በኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈቀድ ምርታማነትን ያሳድጋል ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ከነባሩ የጥጥ ምርት ዘይቤ ጋር ሲነፃፀር ይሄ ነው የሚባል የምርት ልዩነትን እንዳላመጣ የገለፁት መለሰ፣ አያይዘው የቴክኖሎጂው ዋና ጥቅም ተባይን በማጥቃት መከላከል ሲሆን ‹African Ball Worm› የተሰኘ ተባይ በተለየ ሁኔታ ጥጥን ስለሚያጠቃና እስከ 60 በመቶ የሚደርስ የምርት መቀነስን ስለሚያስከትል እሱን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ታስቦ እየተሠራበት እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

እንደ አገር እስካሁን ሲሠራበት የነበረው የፀረ ተባይ ኬሚካል ከውጪ የሚመጣ እና ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሬን የሚጠይቅ በመሆኑ በተሻለ መንገድ ይህን ዝርያ ብንጠቀም ጥጡን የሚያበላሸውን ተባይ በቀላሉ ልንከላከል እንችላለን የሚል እሳቤ ተወስዶ ምርምሩ እንዲካሄድ እና በሕግ ተፈቅዶ ወደ ተግባር እንዲገባ ተደርጓልም ብለዋል።

የውጪ ምንዛሬ እጥረት አለብን፣ ተባዩ ደግሞ ጊዜን አይሰጥም፣ በቂ ኬሚካል የለም። ስለሆነም ጥጥ አምራቾች በአሁኑ ሰዓት የኬሚካል ፍላጎታቸው እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ቴክኖሎጂ እንደ አማራጭ በማየት እና የሌሎችን አገሮች ተሞክሮ በመመልከት የጥጡን ምርት በተሻለ መንገድ ማስቀጠል ይገባል ያሉት መለሰ፣ እርሻዎችም በጥንቃቄ ካመረቱት ለፋብሪካዎች የሚቀርበው የጥጥ መጠንን ማሻሻል ይቻላል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ይህ ምርምር የተጀመረው እንደማንኛውም ምርምር የግብርናውን እና የገበሬውን ችግር ለመፍታት ነው ያሉት ደግሞ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ባዮ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ታደሰ ዳባ (ዶ/ር) ናቸው።

ታደሰ አክለውም አዲሱ ዝርያ ለኬሚካል የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ ባሻገር በኬሚካሉ ሳቢያ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ብክለት ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።
ስለሆነም አስፈላጊ የሆኑ ምርመራዎች እና ፍተሻዎች ተደርገው በኢትዮጵያ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ውስጥ የሚገኙ ፓቶሎጂስት እንዲሁም አግሮኖሚስቶች ተመድበው በራሳቸው ገለልተኛ የሆኑ መረጃዎችን ሲሰበስቡ እንደቆዩ የገለፁት ታደሰ፣ ይህም የተገኘው መረጃ አዋጭና የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ በመታወቁ እና በአካባቢ፣ በሰውና በእንስሳ ላይ ምንም ጉዳት እንደማያደርስ በመረጃዎች የተደገፉ ውጤቶች በመቅረባቸው እንዲሁም የግብርናውን ችግር ለመቅረፍ ጉልህ ሚናን መጫወት እንደሚችል በመረጋገጡ ከአካባቢ፣ ደን እና አየር ለውጥ ኮሚሽን ፍቃድ ተሰጥቶት ወደሥራ መግባቱን ገልፀዋል።

እንደ አንድ ምርምር ከአንድ ቴክኖሎጂ ልቀት በኋላ ከቴክኖሎጂው ጋር አብረው የሚመጡ የግብርና ፓኬጆች በሥራ ላይ እንዲውሉ መመሪያ፣ ሥልጠናና ክትትል ስለሚደረግ በተባለለት ደረጃ ባይሆንም ከነባሩ እጅግ የተሻለ ምርት መገኘቱን የጠቀሱት ታደሰ፣ ሰፊና ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች በቂ የሆነ የማሳ ዝግጅት አለመደረግ የተጠበቀውን ያህል የምርት ውጤት እንዳይገኝ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ልውጥ ሕያዋን (GMO) በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ጥቅም ላይ ከዋለበት ከ1989 እ.ኤ.አ ጀምሮ በዓለማቀፍ ደረጃ ኹለት ጎራዎች ተፈጥረዋል። እነሱም የቴክኖሎጂው ተቃዋሚዎች እና የቴክኖሎጂው ደጋፊዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የብዝኀ ሕይወት ሀብት ቢኖራትም GMOን የሚፈቅድ አዋጅ ከብዙ ጭቅጭቆች በኋላ በ2009 አፅድቃለች። ‹Bt cotton› የተባለ GMO የጥጥ ዝርያ ከባለፈው ዓመት 2019 ጀምሮ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ጋምቤላ ክልል ላይ እየተዘራ ሲሆን የልውጥ ሕያው በቆሎና እንሰት አዝርቶችም በሙከራ ላይ ይገኛሉ።
GMOን የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን ዘሩ በኢትዮጵያ የተፈቀደው የምግብ እጥረት ስለከፋ ወይንም የተሻሉ ዝርያዎች በአገሪቱ ስለጠፉ ሳይሆን ጠንካራ የGMO ተቃዋሚ የሆኑ እንደእነ ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር (ዶ/ር) ያሉ ሰዎች ከኃላፊነት ከተገለሉ በኋላ መሆኑን እንደ መከራከሪያ ያነሳሉ።

እንስሳትን ከዕፅዋት ጋር በማዳቀል የዓለምን የዘር አቅርቦት እና ምግብ ፍሰት ከዐስር በማይበልጡ ዶላር ጠገብ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን የሚቃወሙ የአካባቢ እና የሸማቾች ጥበቃ ተከራካሪዎች ናቸው።

በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት እና ኃላፈዎች የሆኑት የGMO ደጋፊዎች ግን GMO ምርትን የሚያጠፉ ተባዮችን ስለሚከላከል ተመራጭ መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ አውሮፓ ኮሚሽን፣ ጃፓንና አንዳንድ የአፍሪካ አገራት GMOን እየከለከሉ ሲሆን፣ የአሜሪካ እጅ ረጅም የሆነባቸው አገራት ግን GMOን በስውር ማስፋፋት እንደቀጠሉ ገለልተኛ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።

ከወራት በፊትም ‹USDA› ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ GMOን መቀበል ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት ትልቅ እመርታን ይፈጥራል ብሎ ነበር። GMO ከሚያስከትለው የጤና እክሎች በተጓዳኝ ተፈጥሮን በማፋለስና አርሶ አደሮችን የጥቂት ከበርቴዎች ባሪያ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ነው እየተባለም በብዙዎች ዘንድ ይተቻል። በተጨማሪም ጉዳዩ ከሳይንስነት በዘለለ የፖለቲካ መጠቀሚያና የትርፍ ማግበስበሻ መሣሪያ ነው መባሉ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነቱን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here