ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አንድ መንደር በሙሉ ኳራንቲን ተደረገ

0
1674

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ስሙ 24 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኮሮና ቫይረስ ከሌሎች አካባቢዎች በላቀ ሁኔታ በስፋት በመታየቱ አንድ መንደር በሙሉ ተለይቶ ኳራንቲን መደረጉ ታወቀ።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች ከስፍራው እንዳስታወቁት ስፍራው ከመገናኛ ወደ ቦሌ በሚወስደው መንገድ ውሃ ልማት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ኦክስፋም ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ‹‹አስቤስቶስ›› የተባለ መኖሪያ መንደር ሙሉ በሙሉ መዘጋቱን አረጋግጠዋል። ከሐምሌ 15 /2012 ጀምሮ ከመኖሪያ መንደሩ መውጣት እና ወደ መንደሩ መግባት እንደማይቻል ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ሰዓት በተዘጋው መንደር ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የኮቪድ ምርመራ እየተካሔደ እንደሆነ እና ናሙና እየተወሰደ እንደሆነ ታውቋል። ከመንደሩ መዘጋት ጋር ተያይዞም ከቀናት በፊት በመንደሩ ውስጥ ከሰባ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በመታመኑ እንደሆነም ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልደታ ክፍለ ከተማ አንድ መኖሪያ መንደር ቫይረሱ በስፋት ተሰራጭቷል በሚል በመንግስት ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ እና እንቅስቃሴ እንዳይኖር መደረጉ የሚታወስ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here