በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ በከተማ ውስጥ የሚገኙ የአረጋውያን፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞች መርጃ ማእከላት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲበተኑ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።
በመርጃ ማእከላቱ ውስጥ ካለው የተጨናነቀ አኗኗር እና ርቀትን ካለመጠበቅ አንጻር ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በመለየቱ፣ በመርጃ ማእከላት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወደተለያዩ ስፍራዎች በመበታተን እና ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ለማድረግ የታሰበ ነው። ይህንንም ተከትሎ በተመደቡባቸው ስፍራዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው እርዳታዎችን የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በአዲሰ አበባ ጤና ቢሮ የበሽታ ስርጭት እና ምላሽ ሰጪ ቡድን ዋና አስተባባሪ ሮማን መንግሥቱ ጉዳዩን በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ ‹‹እኛ በግላችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በምንችለው አቅም እየሠራን ነው›› ብለዋል።
ከአረጋውያን እና ሕጻናት መርጃ ማእከላት ባለፈ በከተማ ደረጃ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፤ የ‹ቡና ጠጡ› ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ የቫይረሱ ስርጭት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል የተባሉ 136 ቦታዎች እንደተለዩ አስታውቋል። ቢሮው የዳሰሳ ጥናት አካሒዶ በለያቸው ስፍራዎች ላይም የቫይረሱን ስርጭት መጠን ይቀንሳል በሚል የተቀመጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ታውቋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአገር ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝን በሚመለከት የሕክምና ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡ የጤና ሚኒስቴር በመዘናጋቱ የስርጭት መጠኑ እንዲጨምር እንደሆነ አስታውቀዋል።
ባለሙያዎቹ ከፍተኛ ክፍተት ካሏቸው ውስጥ በተለያዩ ክልል ከተሞች ውስጥ የግንዛቤ መስጫ የለም በሚባል ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን እና በአንዳንድ ክልል ከተሞች ውስጥ ማስክ ማድረግ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) እንደመደገፍ የሚታይ እሰከመሆን የደረሰ መሆኑን ታዝበናል ብለዋል።
በተጨማሪም በገለጻቸው ከዚህ በፊት አንድ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሲኖር ተያያዥ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች አብረው ምርመራ እንደሚደረግላቸው ጠቅሰው፣ አሁን ግን ያ እስከነ ጭራሹ በሚባል ሁኔታ እንደሌለ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመውሰድ በባለሥልጣናት በኩልም አረአያ መሆን አስፈላጊ ነበር ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ላይ መንግሥታዊ የሥራ ክዋኔዎች ሲተገበሩ፤ ስብሰባዎች ሲከናወኑና አንዳንድ ፕሮጀክቶች በሚመረቁት ሰዓት የበዛ ቁጥር ያላቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ እንዲሁም ርቀታቸውን ሳይጠበቁ መታየታቸው ለመዘናጋቱ ዋነኛ ማሳያ እንደሆነ ተነስቷል።
እንደ ሚነስቴር መሥሪያ ቤት የጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙ መከሰቱ በታቀወበት ሰሞን ያደርግ የነበረው የማስተማር እና ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን እያደረገ አይደለም ያሉት ለአዲስ ማለዳ አስተያየት የሰጡት የሕክምና ባለሙያ፣ ‹‹ምንም እንኳን ማኅበረሰቡ እየተሰላቸ ቢመስለንም ማስተማሪያ መንገዶቹን እየቀያየሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን አማራጮች መሥራት ይገባል።›› ሲሉ አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ደረጃ በስርጭት ረገድ በርካታ የቫይረሱ ተጠቂዎች ያሉባቸው ክፍለ ከተሞች የትኞቹ ናቸው ብሎ በመለየት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ይደረግ የነበረው ሥራ አሁን ላይ መቅረቱ ለተፈጠረው ክፍተት አንዱ ማሳያ እንደሆነም ተገልጿል። በእዚህ ቫይረስ ተጠቂ እንደሆኑ ተለይተው ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ናሙናቸውን ብቻ እንዲሰጡ አድርጎ እነሱን ወደ መኖሪያቸው መላክ እና ውጤቱንም በስልክ ማሳወቅ ለቫይረሱ ስርጭት መባባስ በዋና ምክንያትነት የተቀመጠ ሌላው ጉዳይ ሆኗል ሲሉም በመንግሥትና በግል ከፍተኛ የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ከሰጡ ባለሙያዎች ውስጥ ባለሞያው በሚሠሩበት ሆስፒታል ከሦስት ወራት በፊት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ለሌላ ሕክምና አምርተው ምርመራ ካደረጉ ዜጎች መካከል አምስት ከመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል።
ከኹለት ወራት በፊት በተሠራ ሌላ የዳሰሳ ጥናት በእዚያው ሆስፒታል ለሌላ ሕክምና መጥተው ምርመራ ከተደረገላቸው ዜጎች መካከል ቁጥርቸው ካለፉት ሦስት ወራት ከነበረው ከእጥፍ በለቀ ሁኔታ አድጎ 12-15 ከመቶዎቹ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ባለፈው አንድ ወር ደግሞ ከ25 ከመቶ በላይ የሆኑት በቫይረሱ መያዛቸውን የሕክምና ባለሞያው ጠቅሰዋል።
በዚህ መነሻነትም ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋት ለመሰራጩት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል ያሉ ሲሆን፣ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ተከሰተ በተባለበት ጊዜ ይደረጉ የነበሩ ተግባራት አሁንም በስፋት ሊደረጉ ይገባል ሲሉ ሐሳባቸውን ለግሰዋል። ቫይረሱን ከመከላከል አንፃር አዲስ አበባ ላይ በአንፃራዊነት የተሻለ ነገር ያለ ቢመስልም፣ በሌሎች ክልሎች ላይ ግን እንደሚታሰበው እየተሠራ ባለመሆኑ በእጅጉ አስጊ እንደሆነ ባለሙያው ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012



