በኮቪድ-19 መከሰት ትምህርት አቋርጠው በቤታቸው የሚገኙ የመጀመሪያ ዲግሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂ ተማሪዎች ያቋረጡትን ትምህርት ከ45 ቀን እስከ ኹለት ወር በሆነ ጊዜ ውስጥ ተምረው በማጠናቀቅ እንዲመረቁ አቅጣጫ ተቀመጠ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ከተመራቂ ተማሪዎችም በተጨማሪ ሌሎች በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች በተቀመጠው ጊዜ ያለፋቸውን ትምህርት አጠናቀው ወደ 2013 ትምህርት ዘመን እንዲሸጋገሩ ውሳኔ ላይ መደረሱንም ለማወቅ ተችሏል።
በአገር ዐቀፍ ደረጀ የተወሰነው ይህ አቅጣጫ ተማሪዎቹ መቼ ወደ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚመለሱ ቀን እንዳልተቆረጠለት ተመላክቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት ተማሪዎቹ መቼ ወደ ዩኒቨርሲቲ መመለስ እንዳለባቸው ኮቪድ-19 ያለበትን ደረጃ ያገናዘበ የመንግሥትን ውሳኔ የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ እንደሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
መሥሪያ ቤቱ አቅጣጫውን ያስቀመጠው ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተቋርጦ የሚገኘውን ትምህርት ኮቪድ-19 ቢጠፋም ባይጠፋም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እና ዝግጅት በማድረግ ለማስቀጠል በተደረገ ውይይት ነው ተብሏል። በዚህ መሠረት በ2012 ትምህርት ዘመን በ2ኛው ወሰነ ትምህርት ተጀምሮ የተቋረጠውን የአንድ ወሰነ ትምህርት ከ45 ቀናት እስከ ኹለት ወራት ጊዜ በማጠናቀቅ የ2013 ትምህርት ለመቀጠል ታቅዷል።
በዚህ ሂደት ከወረርሽኙ አንጻር በጥንቃቄ ለማስኬድ እንዲረዳ በመጀመሪያ ተመራቂ ተማሪዎች ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ እንደሚደረግ እና እነሱ ሲያጠናቅቁ ቀጥሎ ተመራቂ ያልሆኑ ተማሪዎች እንደሚገቡ አዲስ ማለዳ ከሚኒስቴሩ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ደቻሳ ጉርሙ ጨምረውም ኮቪድ-19 በአገር ውስጥ በመከሰቱ በድንገት የተቋረጠው ትምህርት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እኩል የትምህርት ሽፋን እንዳልተሰጠ ጠቅሰዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በወቅቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ስላሉ ከ45 ቀን እስከ ኹለት ወር የተቀመጠው ጊዜ ገደብ እንደየ ዩኒቨርሲቲዎች አፈጻጸም ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን ሲቀጥሉ ቅዳሜ እና እሁድንም ጨምሮ ትምህርት እንደሚወስዱ ደቻሳ አመላክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ተማሪዎች ቀሪ ትምህርታቸውን በአጭር ጊዜ አጠናቀው ወደ ቀጣዩ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ‹አንድ ትውልድ አለማስመረቅ አገራዊ ቀውስ ስለሚያስከትል› የሚኖረውን ጫና ተቋቁሞ የአንድ ዓመት ከግማሽ ትምህርት በአንድ ዓመት ማጠናቀቅ የተሻለ በመሆኑ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው ያቋረጡትን ትምህርት በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ተመራቂዎችን በማስመረቅና ከመመረቂያ ዓመት በታች የሆኑ በትምህርት ላይ የነበሩ ተማሪዎችን የቀራቸውን ትምህርት በአጭር ጊዜ አጠናቀው የ2013 ትምህርታቸውን እንዲያስጀምሩ ተብሏል። አዲስ ገቢዎችን በመቀበል ለማስተማር ኮቪድ-19 መከላከል የሚያስችሉ መሠረታዊ ዝግጅቶችን እንዳደረጉ አቅጣጫ መሰጠቱም ተመላክቷል።
እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከመቀበሉ በፊት የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችን እንደ ሳኒታይዘር፣ ማስክ፣ ሳሙና እና መሰል አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል።
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጥንቃቄ እየተደረገ የወረርሽኙ ሁኔታ ሲቀንስ ወይም ሲቆም በቀጣይ የትምህርት ሂደት እንዴት ይደረጋል በሚለው ዙሪያ በአገር ደረጃ ከተያዘዉ አቅጣጫ አንጻር ተማሪዎችና መምህራን ዝግጅት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ደቻሳ አመላክተዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተማሪዎች የየትምህርቱ መርጃ መሣሪያዎችን በማግኘት ከትምህርት ይዘት ሳይርቁ እንዲቆዩ ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በነጻ እንዲያገኙ መደረጉን ደቻሳ አስታውሰዋል።
ሚኒስቴሩ የወሰነው ውሳኔ ተገቢ መሆኑንና ወቅቱን የጠበቀ ችግር መሻገሪያ አማራጭ መሆኑን ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ፕሮፌሰር እንደሚሉት ሚኒስቴሩ ያስቀመጠው አቅጣጫ መልካም መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ከወዲሁ ተማሪዎችንና መምህራንን በሥነ ልቦና ዝግጁ በማድረግ የሚፈጠሩ ጫናዎችን ማቃለል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን ሲቀበሉ በመጀመሪያ በተለይም ሴት ተማሪዎች እንዳይቀሩ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ጥሩሰው፣ የሚማሩትን ትምህርት ሁሉንም ከማስተማር ይልቅ መሰረታዊ የሚባሉ ትምህርቶችን በመምረጥ በጥሩ ሁኔታ ማስተማር እንደሚገባ አመላክተዋል። አክለውም ልዩ ድጋፍና ክትትል ለሚፈልጉና ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ማካካሻ በመስጠት ማብቃት ይገባል ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012



