በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በአንድም በሌላም ምክንያት ወደ ፍትህ ተቋማት ጎራ ብሎ ተገቢውን ግልጋሎት በማግኘት ረክቶ የተመለሰን ሰው ማግኘት እጅግ ከሚከብዱ የዓለማችን ስራዎች አንዱ ወደ መሆን እየተጠጋ እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በእስር እና በፍርድ ቤት ከክርክር ሒደት ላይ ሆኖ በአማካኝ መታሰር እና በኋላም ፍርድ ሒደቱ ሲጠናቀቅ እና የዕስራት ብይን ሲሰጥበት ዕጃቸው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚል ሲተላለፍ ግለሰቦቹ በማግስቱ ከእስር የሚለቀቁበት እና እስራቸውን በፍርድ ሒደት ክርክር የሚያጠናቅቁበት ጊዜ በግልጽ የሚስተዋል የእኛ አገር ተግባር ብቻ ወደ መሆን እየዞረ ነው።
በተለይም ደግሞ ከፖለቲካ እና ባላቸው የተለየ አቋም ወደ ዘብጥያ ወርደው ከተያዙበት ምክንያት ጋር የማይገናኝ እና ቀድሞ በከሳሽ በኩል ናቸው የተባሉትን እና የተገመቱትን ነገሮች እየተጠየቁ ረጃጅም የፍርድ ሒደቶች እንዲኖሩ ማድረግም የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ለመሆናቸው የማይታበል ሀቅ ነው። በለውጡ ምክንያ ደብዛው እየጠፋ የመጣው የቀድሞው ኢህአዴግ በዚህ በኩል በርካታ ግለሰቦችን ለአብዮታዊ ዲሞክራሲው ጸርናቸው ያላቸውን ሰዎች ጥርስ ይነክስባቸው እና ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ ወደ ዘብጥያ በማውረድ ከተከሰሱበት ምናልባትም የግብር ስወራ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ከተያዙበት ምክንያት ጋር ያልተገናኙ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት የክሱን ምዕራፍ በማዞር ዘለግ ላሉ ጊዜያት በዕስር ቤት እንዲቆዩ ማድረግ አንደኛው መለያው እስኪሆን ድረስ በስፋት የሚታይ ጉዳይ ነበር።
ይሁን እንጂ ታዲያ ይህ ጉዳይ አሁንም በለውጡ ዘመንም እያቆጠቆጠ ያለ ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ በመታዘቧ ጉዳዩ ስር ሳይሰድ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት ትጠይቃለች። ባለፈው ጊዜያት በርካቶች በፍትህ መዘግየት አንብተዋል፣ በመንግስት ተስፋ ቆርጠዋል፣ ምን ህግ አለ ፣ የሚሰማኝ መንግስትስ ከወዴት አለ በሚል በራቸውን ዘግተው አልቅሰዋል። ይህ የሆነው ታዲያ በመንግስት ችላ ባይነት እና በፍትህ ሒደቱ ላይ በሚታዩ መንጓተቶች ምክንያት እንደሆነም አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ይሁን እንጂ አሁንም ይህ ጉዳይ በአንዳንድ ሰዎች የፍርድ ሒደት እና በታላቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መዘግትን በመታዘብ አዲስ ማለዳ ሊቆም ይገባል፤ በየደረጃው ያ የፍትህ አካላት ስራቸውን በሚገባ አፋጥነው የፍርድ ሒደቱም እንዲፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል ትላለች። በለውጡ የመጀመሪያ ጊዜያት ጀምሮ በሚቃጡ እና በሚፈጠሩ አገራዊ አስደንጋጭ ጉዳዮች ጀምሮ መንግስት የፍርድ ሒደቱን አፋጥኖ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ሳይችል በመቅረቱ በየጎዳናው የደቦ ፍርዶች ተካሒደዋል፣ ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ፈራጅ ሆነው የሰዎችን ሕይወት በግፍ የነጠቁ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በለውጡ ዘመን መመልከት የተለመደ ለመሆን እየዳዳው በመሆኑ የፍርድ ሒደቱ በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ እና ሕዝብም በመንግስት እና በፍትህ አካላት እንዲሁም ተቋማት ላይ የሚኖረውን አመኔታ እንዲጨምር ያስፈልጋል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ሰኔ 16/2010 በወቅቱ ለአራት ኪሎው ቤተ መንግስት አዲስ የሆኑትን እና አዳዲስ ሀሳቦችን ይዘው ብቅ ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድን ለመደገፍ በተዘጋጀ ሰልፍ ላይ ቦንብ ፈንድቶ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ቢውሉም የፍርድ ሒደታቸው ግን በፍጥነት ተጠናቆ ይፋ ሲሆን አልታየም። በእርግጥ የነገሩን ውስብስብነት እና ጥልቀት ለመረዳት የሚያስቸግር ባይንም ቅሉ ኹለተኛ ዓመቱን የያዘው የፍርድ ሒደት ግን አሁንም አለመጠናቀቁ በሕዝብ ዘንድ ጥያቄን የሚፈጥር በመሆኑ ባአስቸኳይ ሊጠናቀቅ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ከዚህም በተጨማሪ የቦንብ ጥቃቱ ከተፈጠረ ከአንድ ዓመት በኋላ ሰኔ 15/2012 ከክልል እስከ ፌደራል ድረስ በተከሰተው አስደንጋጭ እና አገርን ለማናጋት ከፍተኛ ስራ የተሰራበት ከፍተኛ አመራሮች ግድያን በተመለከተ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሰዎች ለአንድ ዓመት ዘለቀው ፍርድ ሒደት አሁንም መቋጫ ባለማግኘቱ የዘገየ ፍርድ እንደቀረ ይቆጠራል በሚል በተጎጂ ቤተሰቦች እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ሀዘንን የሚጭር ከመሆኑም በላይ በአገረ መንግስቱ ላይ ዕምነት ለመጣል የማያስደፍር ሊሆን ስለሚችል የፍርድ ሒደቶች በአፋጣኝ ሊጠናቀቁ እና ለሕዝብም ይፋ ሊደረጉ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ይኸው ደግሞ በቅርቡ በድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ እና ግድያውንም ተከትሎ ለታሰቡ በርካታ ውዥንብሮች ዕጃቸው አለበት ተብለው በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ሒደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት በፖሊስ በኩል የሚደረገው ምርመራ እና በሌሎች የፍትህ አካላት የሚካሔደው ፍድ ሒደት በአስቸኳይ ተጣቆ ፍትህን በማስፈን ሒደት የበኩላቸው ድርሻ እንዲወጡ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በየጊዜው አዳዲስ አጀንዳዎች እየተፈጠሩ መንግስትም ትኩረት በሚሰረቅበት ወቅት ግን አሁንም ፍርድ ሒደቶችን የሚከታተሉ እና የመጨረሻውን ብያኔ የሚጠባበቁ ሰዎች መኖራቸውን ደግሞ ልብ ሊባል ይገባል። በጥርጣሬ ተይዘው ምርመራቸው ተጓቶ ነገር ግን በምርመራ ውጤት ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነጻ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችም መኖራቸው ታሳቢ ተደርጎ ዕድሜያቸው በአላስፈላጊ ጉዳይ እንዳይባክን መንግስት የበኩን ድርሻ እንዲወጣም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ወደፊት መንግስት ወደ ሕዝቡ በመቅረብ እና ለሕዝብ መቅረብም ግድ በመሆኑ ለሚኖረው መልካም ግንኙነት እና ጥሩ መስተጋብር በፍትህ ተቋማት ዘንድ የሚታየውን የአሰራርም ሆነ የአተገባበር መንጓተት ከወዲሁ በመፍታት የተጀመረውን ዲሞክራሲ ግንባታ በተሳለጠ መንገድ እንዲቀጥል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ከዚህም ባለፈ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች በራሳቸው ከመፍታት ይልቅ ወደ ሕግ ተቋማት ወይም በአቅራቢያቸው እና አካባቢያቸው ባሉ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስነ ስርዓቶች እንዲያመሩ ለማድረግም አይተኛ ምክንያት እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። በመሆኑም አገር ለመገንባት እና ትውልድን ለማነጽ ከአሁኑ የሕግ የበላይት እየተከበረ እና ፈጣን የፍርድ አሰጣጥ ከተሳለተ እና ከተናበበ አካሔድ ጋር ተግባራዊ ማድረጉ ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ በመገንዘብ አፋጣኝ እርምጃ በመንግስት ወገን ሊደረግ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ከመንግስትም ባለፈ ኹሉም ባለድርሻ አካል ሕዝብም ሆነ ሚዲያዎች በዚህ ረገድ ያለውን እንቅስቃሴ እና አካሔድ በመደገፍ እንዲሁም አግድም አካሔዶችን በመንቀፍ ትክክለኛ ሕግ የበላይት የሰፈነባትን አገር በመገንባት ረግድ በኩላቸውን እንዲወጡም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። በተለይም ደግሞ ሚዲያዎች እንደ አራተኛ መንግስትነታቸው በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን እና የፍርድ ሂደታቸውን ከስር ከስር በአንክሮ በመከታተል ትክክለኛ ዘገባዎችን በመስራት እና ለሕዝብ በማድረስ የተራዘሙ የፍርድ ሒደቶችንም ይፋ በማድረግ ተጠያቂነት የሰፈነበት የፍትህ ስርዓትን ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በመጨረሻም በመንግስት እና በሕዝብ መካከል ያለው እና እንደ ድልድይ ሚቆጠረው ሚዲያው ከወገንተኝነት እና ጎጠኝነት በመውጣት ፍትህ ለዘገየበት እና ለተጓተተበት ሁሉ በመቆም መጮህም እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ታስባለች። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የታለመችው ኢትዮጵያ፣ አሻግረን ተመለከትናት በዜጎች መከባበር እና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተችው፣ ፍትህ የማይጓደልባት፣ የፍርድ ሂደት የማይዛዛባት ለመኖር ምቹ ሆነችን አገር ከመፍጠር የሚያግደን እንቅፋት እንደማይኖር የታወቀ ሲሆን ይህ ከወዲሁ መጀመር ይኖርበታል ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትደመድማለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012


