የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በኢትዮጵያ

0
4556

መረጃ የታሪክ የጀርባ አጥንት ነው። ይህም የሚባለው ያለምክንያት አይደለም። ታሪክን በመረጃ ቋት ውስጥ በየዘመን እና ጊዜው እየከፋፈለ ሰድሮ የትናንቱን እውነት ከዛሬው ኩነት ጋር በማጋመድ ለቀጣዩ ትውልድ የማቆየት ልዩ አቅም ስላለው ነው።

የሰው ልጅ ሕይወቱን በተቃናና በቀለለ መንገድ ይመራ ዘንድ፤ በሚያደርገው የእለት ከእለት ሩጫ ውስጥ ከእርሱ ዘመን በፊት ስለነበሩ፣ በእርሱም ዘመን ላይ በዙሪያው እየተከናወኑ ስላሉ እንዲሁም ወደፊት ሊከናወኑ ስለሚችሉ ኹነቶች በቂ የሆነ እውቀት እና ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ አጥብቆ ይሻል።

ታዲያ እነዚህ በየዘመናቱ የተከናወኑ ታሪካዊ ክስተቶች እና ኹነቶች በዘመኑ በነበሩ የመረጃ መለዋወጫ ቋቶች ውስጥ በእልፍ ተሰድረው ከትውልድ ትውልድ በመተላለፋቸው፣ ትውልድ እነዚህን የመረጃ መዛግብት በማገላበጥ እና በመፈተሸ የሚፈልገውን መረጃ በአይነት እና በብዛት ለማግኘትም እለት ከእለት ይታትራል።
አሁን ባለንበት ዘመንና ጊዜ ታዲያ ከትውልዱ የሥልጣኔ እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰው ልጅ መረጃን ለማግኘትም ሆነ በዓለም ዙሪያ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያደርገውን ሩጫ ቀላልና ቀልጣፋ ያደርግለታል። በተጨማሪም ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበቱንም በአግባቡ እንዲጠቀም በመርዳት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህም ምክንያት ትውልድ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ከማኅበራዊ ሚድያዎች ጋር ያለው ትስስር እና ቁርኝት እጅግ እየጨመረ መምጣቱን በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ጉዳይ ሆንዋል።

አሁን ዘመኑ የደረሰበት የኢንተርኔት አገልግሎትን በመጠቀም ማንኛውም ሰው የፈለገውን መረጃ በፈለገው ሰዓት ከቤቱ ሆኖ ያገኛል። ከመደበኛ መገናኛ ብዙኀን ይልቅም የማኅበራዊ ሚዲያ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ሆነዋል። በተለይም ስማርት ስልኮች ከተፈጠሩ ወዲህ የማኅበራዊ ሚድያዎች አጠቃቀም በእጅጉን መጨመሩ የሚታይ እውነት ነው።

አጠቃቀማችን ምን ይመስላል?
በዓለማችን 4.57 ቢሊዮን ወይንም ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ሪፖርታል ዶት ኮም መረጃ ያመላክታል። እንደ ድረ ገፁ ዘገባ፣ በዓለም ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ባለፉት ዓመታት ከ10 በመቶ በላይ ጨምረዋል።

ይህም የተጠቃሚዎቹን ቁጥር እስካሳለፍነው የፈረንጆቹ የጁላይ ወር መጀመሪያ ድረስ 3.96 ቢሊዮን እንዳደረሰው ይጠቁማል። ይህም እድገት በአማካይ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በየቀኑ እንዲሁም ቢያንስ 12 አዳዲስ ሰዎች በየሰከንዱ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም እንደሚጀምሩ ይጠቁማል።

‹ስቴት ካውንተር› የተሰኘ ድረ ገፅ ደግሞ በሚያወጣው አመታዊ መረጃ ላይ ከፈረንጆቹ ጁላይ 2019 እስከ ጁላይ 2020 በዓለም ዙሪያ ካሉ ሰዎች 74.17 በመቶ የሚሆኑት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ናቸው ሲል፣ 6.78 በመቶ ትዊተር፣ 4.86 በመቶ ዩትዩብ እንዲሁም 1.35 በመቶ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ናቸው ይላል።
ከአፍሪካ ሕዝብ 10 በመቶ የሚሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እንደሆነ ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም እነዚህን የማኅበራዊ ሚድያዎች የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየተበራከተ ነው። በዚም መሠረት በኢትዮጵያ ፈረንጆቹ የ2020 በአጠቃላይ 2.14 ሚሊዮን ሰዎች የኢንተርኔት አገልግሎትን ሲጠቀሙ፣ ይህም ከባለፈው የ2019 ተጠቃሚ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲስተያይ በ534 ሺሕ ወይንም 26% ጭማሪ ማሳየቱን የዳታ ሪፖርታል ዶት ኮም መረጃ ያሳያል።

ዘገባው አያይዞም 6.20 ሚሊዮን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ሲጠቁም፣ ይህም ካለፈው የ2019 ዓመት ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ237 ሺሕ (+4.0%) ጭማሪ ማሳየቱን ያመለክታል። በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ 46.75 ሚሊዮን ሰዎች የሞባይል ስልክ ኢንተርኔት አገልግሎትን ይጠቀማሉ። ይህም ካለፈው 2019 የሞባይል ኢንትርኔት ተጠቃሚ ጋር ሲተያይ በ7.2 ሚሊየን (+18%) የጨመረ ነው።

‹ስቴት ካውንተር› የተባለ አውታር እስከ ሠኔ ድረስ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 23.9 በመቶ የፌስቡክ፣ 33.33 በመቶ የዩቲዩብ እንዲሁም 10.2 በመቶ የሚሆኑ የትዊተር ተጠቃሚዎች በኢትዮጵያ መኖራቸውን በገፁ አስፍሯል። ከፌስቡክ በተጨማሪ በኢትዮጵያ በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዩቲዩብ እና ትዊተር ሲሆኑ በአሁኑ ሰዓት ቴሌግራም የተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያም በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።

እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ፎቶግራፎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማጋራት፣ የግል መልእክቶችን ለማስተላለፍና የተለያዩ አስተያየቶችን ለማካፈል ማስቻላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚያቸውን ሊያበዛው ችሏል። በጊዜ ሂደት ግን እነዚህን አውዶች በመጠቀም የሚተላለፉ መልእክቶች ግለኝነትን የሚያንፀባርቁ የጥላቻ ንግግሮችን ማስተላለፊያ እና ሰዎችን ለጥፋት የማደራጃ መድረክ እየሆኑ መምጣታቸው እየተስተዋለ ነው።

‹‹ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ብዙ ጊዜ ወጣቶች ላይ የሚታየው የማኅበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ችግር የመሰዳደብ እና ሰውን የማዋረድ ነው።›› የሚለው የሪፖርተር ጋዜጠኛና በትዊተር ገፁ ወቅታዊ መረጃዎችን በመልቀቅ የሚታወቀው ሳሙኤል ጌታቸው ነው። ‹‹ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ጊዜ ስህተት አያለሁ›› የሚለው ሳሙኤል፣ ማኅበራዊ ሚዲያን በተከታታይ ባይመለከትም ነገር ግን ብዙ ጊዜ ከሰው ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚገለገልበት ሁነኛ መሣሪያው መሆኑን ይገልፃል።

‹‹ብዙ ጊዜ በገጼ ከምለቀው መረጃ ስር ብዙ ሰው ይሰድበኛል።›› የሚለው ሳሙኤል ‹‹ግን በመሳደብ ሳይሆን ቀስ ብዬ ምን ለማለት ፈልጋችሁ ነው። ከተሳሳትኩኝ ንገሩኝ በማለት በግል መስመር ለማናገር እሞክራለሁ። ብዙ ሰው ግን ሲመላለስ አያለሁ። ነገር ግን በአንጻሩ እንደራስ ፍላጎት ከሰዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ልንጠቀመው ይገባል ብዬ አምናለሁ›› ሲል ለአዲስ ማለዳ ሐሳቡን አጋርቷል።

ወንድወሰን ተሾመ የሥነልቦና ባለሙያ ሲሆኑ የአልታ ምርምር እና ሥልጠና ካውንስሊንግ በሚባል እና የማማከር ሥራን በሚሠራ ድርጅት ውስጥ ዋና ሥራ አሲኪያጅ ናቸው። እርሳቸውም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ‹‹በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ ነገሮች ይሠራሉ። ራስን ለማሳደግ፣ እውቀትን ለማግኘት፣ የብዙ ሰዎችን አስተሳሰብ እና አተያይ ለማወቅ ይረዳናል። ነገር ግን አብዛኛው ሰው ማኅበራዊ ሚዲያን ስርአት በሌለው መልክ ነው የሚጠቀመው ብዬ አስባለሁ›› ሲሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ይተቻሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያን እንደምን ተረዳነው?
በኢትዮጵያ እየታየ ከሚገኘው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለጠፉ ሐሳቦች ጥላቻ አዘል፣ ግለሰብን ወይንም ቡድንን በብሔር እና በሃይማኖት የሚፈርጁና ብጥብጥ እና ሁከትን የሚሰብኩ ናቸው። ሐሰተኛ መረጃዎችም እንደዛው።

ታድያ ማኅበረሰቡ በተለይም ወጣቱ የማኅበራዊ ሚዲያን ጥቅም የተረዳበት መንገድ ትክክለኛ ነው ማለት ይቻለላልን በማለት አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ፣ ሳሙኤል ሲመልስ፤ ‹‹አይደለም! ብዙዎቹ እየተጠቀሙት ያሉት ለመሰዳደብ፣ ለመኮራረጅ፣ አንዱ ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ብዙ ሰው ሲያንቀሳቅስ ሲያዩ እነሱም እንደዛ ለመሆን ለመሞከር ነው።›› ብሏል።

‹‹ስርአት ማለት›› ይላሉ የሥነልቦና ባለሙያው በበኩላቸው፣ ‹‹ስርአት የምንለው ነገር ለዘለቄታዊ ጥቅም ጊዜአዊ ፍላጎትን መግታት ነው። ስለዚህ ወጣቶች የትምህርት መጽሐፍቶችን ማንበብ ለዘለቄታ የሚሆን ነገርን መሥራት ሲገባቸው ከጠዋት እስከ ማታ አንዳንድ ጊዜ እንደውም እስከ ሌሊቱ 9 እና 10 ሰአት በዋይፋይ እየተጠቀሙ ቀን ላይ ደግሞ ስድስት ሰአት ሰባት ሰአት የሚነሱና ምግብ የሚጠይቁ ልጆች እንዳሉ በሥራ አጋጣሚ ማወቅ ችያለሁ።

ስለዚህ በአብዛኛው የማኅበራዊ ሚዲያን ዋጋ እና ጥቅም በማወቅ እና በማስተዋል ሳይሆን የጊዜያዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እና ለማርካት የሚጠቀሙ ይመስለኛል።›› በማለት ያስረዳሉ።

በጣም ጥቂት ጥቅሙን በማወቅ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ወጣቶች ይኖራሉ ብለው እንደሚያስቡ ገልፀው፤ ነገር ግን ‹‹በአብዛኛው ከሚያጋጥመኝም ጉዳዮች አንፃር የማኅበራዊ ሚዲያን ጥቅም እና ዋጋ ተገንዝበው የሚጠቀሙ ጥቂቶች ናቸው አብዛኞች ጥቅሙን አውቀው አይደለም የሚጠቀሙት›› ሲሉም ይገልፃሉ።

የማኅበራዊ ሚድያ ሱሰኛነት?
የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ወይንም በጠቅላላ ኢንተርኔት ሱሰኛነት የተለመደ ባይሆንም ነገር ግን ብዙ ጊዜ ገደብ የሌለው የበዛ የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት እና ይዘት አጠቃቀምን ‹የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት› ተብሎ ሊገለፅ እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ።

የሥነ ልቦና ማእከል መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጆን ኤም ግሮሆ በአንድ ጥናት ላይ እንደሚናገሩት የመረሳት ፍርሃት “FOMO” (fear of missing out) በኅብረተሰቡ ውስጥ ተስፋፍቷል። በዚህም ምክንያት ወጣቶች እና ጎልማሶች መኪና በሚያሽከረክሩበት ጊዜም ቢሆን የጽሑፍ መልእክት ይላላካሉ፣ ምክንያቱም የማኅበራዊ ትስስር ዕድል ከራሳቸው እና ከሕይወታቸው (እና የሌሎች ሕይወት) የበለጠ አስፈላጊ ነው። የበለጠ አስደሳች ወይም አዝናኝ የሆነ ነገር እየተከሰተ ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ ነው በማለትም የማኅበራዊ ሚዲያን አዘውትሮ የመጠቀምን ሱስ ይገልፁታል።

ይህም ችግር በአብዛኛው ጊዜ በወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ መታየቱ ብዙ የመሥራት አቅም ያለውን ኃይል እያንኮታኮተ ጊዜውን በአግባቡ እንዳይጠቀም ማድረጉ የማኅበራዊ ሚዲያን አሉታዊ ጎን አጉልቶ ያሳያል ሲሉ ብዙዎች ይተቻሉ።

‹‹የዛሬ ዐስር ዓመት ፌስቡክ በአገራችን እንዲህ ብዙ ተጠቃሚ ሳይኖረው እኔ አምስት ሺሕ ተከታይ ነበረኝ። ነገር ግን አንድ ቀን አቆምኩት፤ ስድቡ ሰለቸኝ። ሰዉ ሲሰዳደብ ሰለቸኝ። በተመሳሳይ ከትዊተርም ላቆም እችላለሁ። ምንም ያን ያህል ሱሰኛ ሆኛለሁ አልልም። ግን የሰዉን አስተያየት እያየሁ ነው እንጂ የምቀጥለው ከሰዉም ምንም አስተያየት ካላገኘሁና ለራሴም ሆነ ለምሠራው ነገር ጥቅም ካላገኘሁ በማንኛውም ሰዓት አቆመዋለው።›› ሲል ያስረዳል፤ ጋዜጠኛ ሳሙኤል።

ወንድወሰን በበኩላቸው በሥራቸው አንዳንዴ በማኅበራዊ ሚዲያ በጣም የተጠመዱ፣ ሰፊውን ጊዜያቸውን የሞባይል ስልካቸው ላይ ወይንም ኢንተርኔት ላይ የሚያሳልፉ ወጣቶች ያጋጥሙኛል ብለዋል። ‹‹እነኚህ ወጣቶች እኔ ጋር የሚመጡት በከፍተኛ ሁኔታ ከኢንተርኔት ጋር ቁርኝት ወይንም ሱሰኝነት እያጋጥማቸው ነው። በዛ ምክንያት የሚፈጠርባቸው ሥነልቦናዊ ጫና አለ። ይሄ ስነልቦናዊ ጫና ከስሜት፣ ከአስተሳሰብ መዛባት እንዲሁም ከድርጊት ጋርም የሚያያዝ ነው።›› ብለዋል።
‹‹ለምሳሌ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የሚሰሙ ክፉ ዜናዎችን ወይንም መጥፎ ቪዲዮዎችን በመመልከት የመረበሽ የመጨነቅ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ከዛም አልፎ ደግሞ ከ‹ፖርኖግራፊክ› ፊልሞች ጋር ተያይዞ ወጣቶች የበለጠ ሱሰኛ የመሆንና ከዛ የመላቀቅ ችግር አጋጥሟቸውም አያለሁ›› ሲሉም ያስረዳሉ።

‹‹በአብዛኛው በዚህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች መጽሐፍን ሆነ ቁም ነገር ያለው ነገር ለማንበብ የትኩረት ማጣት ችግር ያጋጥማቸዋል። በርካታ ጊዜ ፌስቡክ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች በተለይ በተንቀሳቃሽ ምስሎች በተገናኘ የሚወጡትን የሚከታተሉ ሰዎች የትኩረት ማጣት ችግር ያጋጥማቸዋል። ከዛም ጋር ተያይዞ በትምህርታቸው ላይ የመቀነስ እንዲሁም ማኅበራዊ ክህሎታቸው ከሰው ጋር የመነጋገር መግባባት ሁኔታ ሲቸግራቸው እመለከታለሁ›› በማለት የሥነ ልቦና ባለሙያው አክለዋል።

እነዚህ ነገሮች በቀላሉ የሚታዩ ነገሮች አይደሉም ያሉት ወንድወሰን፣ ‹‹ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚያሳልፉ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ የላቸውም የቀረበላቸውን ተመግበው በቶሎ ወደክፍላቸው የመሮጥ ነገር ማህበራዊ ክህሎታቸው በጣም ዝቅተኛ የሚያደርግና አዲስ ሰውን የመተዋወቅ ችሎታቸው የሚቀንስ ይሆናል›› በማለት ያመላክታሉ።

የማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት ከመከሰቱ በፊት እንዴት መቆጣጠር ይቻላል ስትል አዲስ ማለዳ ለሥነልቦና ባለሙያው ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ባለሙያው ሲመልሱ ‹‹በቤተሰብ ደረጃ ከሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ለልጆቻቸው የማስተማር የማሳወቅ ኃላፊነት ወላጆች አለባቸው። በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በአብዛኛው የማኅበረሰቡን ክብር፣ ባህል እና ወጉን ያልጣሰ እንዲሆን እንዲሁም ከጊዜም አንፃር የተወሰነ የጊዜ ገደብ እንዲኖር ማድረግ ይገባቸዋል። ›› ብለዋል።
ይህን መሰል አሠራር በአውሮፓ እና በአሜሪካ መታዘባቸውን በማውሳት፣ ‹‹እነርሱ ከልጆቻቸው ጋር መተማመን ውስጥ ይገባሉ። በቀን ውስጥ ከአንድ ሰዓት ወይንም ከሠላሳ ደቂቃ በላይ ልጆቻቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳያሳልፉ ይመክራሉ፣ ያሳውቃሉ።›› ብለዋል።

‹‹ነገር ግን›› ይላሉ ባለሙያው፤ ‹‹ነገር ግን በዚህ በማኅበራዊ ሳይንስ ውስጥ ‹who reforms the reformer› ወይንም ‹ለዋጩን ማን ይለውጠዋል› የሚል አስተሳሰብ አለ። ስለዚህ ልጆቹን ራሱ ለመምከርና አቅጣጫ ለማስያዝ ወላጆች ያ እውቀት እና ግንዛቤስ አላቸው ወይ ብሎ መጠየቅ ደግሞ ሌላ ነገር ነው።››
በመንግሥት ደረጃም ወጣቱን ማስተማር ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ለምን ብዙ ጊዜያቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሳልፋሉ፣ የሚፈጥርላቸው ነገር ምንድን ነው በማለት ከወጣቱ ሕይወት ጋር የተያያዘ ትምህርት ማስተማር፣ ያንን እውቀት የመፍጠር ኃላፊነት የሁሉም እንደሆነም አጽንዖት ሰጥተዋል።

‹‹ወጣቱ ከተማረ ይቀየራል ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም በሥልጠና አጋጣሚዎች የማውቃቸው ወጣቶች አሉ። አብረን ጥቂት ቀናትን ስናሳልፍ የነበራቸውን ነገር ትተው ወደ አዲስ ባህሪ እና እሴት ውስጥ ሲገቡ አይቻለሁ።›› ብለዋል።

የማህበራዊ ሚዲያን እንዴት እንጠቀም?
ሳሙኤል በዚህ ላይ ሐሳቡን ሲሰጥ፣ ‹‹ለምሳሌ ሥራ ስፈልግ እፅፍበታለሁ። እንደዚህ እንደዚህ አይነት ሥራ እፈልጋለሁ እላለሁ። ብዙ አምባሳደሮች በትዊተር የእኔን መረጃዎች እየተጠቀሙ ይፅፉልኛል። እኔ በማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም መረጃ ነው የምለዋወጥበት። እንጂ ዝም ብዬ ሁሌም አልቀልድም። ሥራዬንም እንደምሠራ ሰው ስለሚያይ ነው አክብሮት ሰጥቶ የሚከታተለው። ቀልድ ብቻ ቢሆን ኖሮ ይሰለቻል።›› ብሏል።

ወንድወሰን እንዳሉት ደግሞ ኢንተርኔት ውስጥ እውቀት በተለያየ መስክ እንደልብ አለ ሲሉ ያስረዳሉ። ነገር ግን ያንን እውቀት ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዘብ እና መፈተሽ ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ። ‹‹በርካታ የትምህርት የክህሎት ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ኢንተርኔት ውስጥ በብዛት ማግኘት ይቻላል። ስለዚህም ወጣቱ ከራሱ ዝንባሌ ወደፊት ከሚሆነው የሥራ ፍላጎቱ ጋር የተያያዙ በርካታ እውቀቶችን መርጦ የሚታመኑ ምንጮችን አውቆ እና መርጦ ኃላፊነት የሚሰማቸው የሚዲያ አካላት የሚያወጧቸው ዜናዎች፣ መጽሔቶች ጋዜጦች ስላሉ፣ እነሱን ቢፈትሽ እና ቢያተኩር እላለሁ።›› ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ለግሰዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here