ቴዲ አፍሮ በ‘‘ደሞ በአባይ (ከሞከሩንማ)’’

0
993

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28 በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ የነበረውና እስካሁንም አነጋጋሪነቱ ያልበረደው በብዙዎች በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የታዋቂው፣ አንዳንዶች ‘ምሉዕ በኩልሔ’ ሲሉ የሚያሞካሹት የቴዲ አፍሮ ነጠላ ዜማ መለቀቅ ጉዳይ ነው፤ ‘‘ደሞ በአባይ (ከሞከሩንማ)’’። ቴዲ አፍሮ ነጠላ ዜማውን ማዘጋጀቱ ከተሰማ ሰንበትበት ያለ ቢሆንም ከአንድ ወር በፊት ይለቀዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፤ ይሁንና የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እንዲሁም ግድያውን ተከትሎም በተፈጠረ ኹከት ሳቢያ ነጠላ ዜማው ሳይለቀቅ ቆርቷል።

የሆነው ሆኖ ግርግሩም ረግቦ፣ የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሊት በተሳካ ሁኔታ በተጠናቀቀበት ማግስት፥ ኢትዮጵያውያን ከድብታና ሐዘን በመጠኑ የተላቀቁበትን ቀን ጠብቆ የተለቀቀው ነጠላ ዜማ እንደ ሰደድ እሳት ከጫፍ እስከ ጫፍ የማኅበራዊውንም ሆነ መደበኛ መገናኛ ብዙኀንን አዳርሷል። ሙዚቃውን ከማዳመጥ ባሻገር ግጥሙ ገራሚ፣ እምቅ የመተንተን አቅም ያለው፣ ቅኔ መሳይ ድርሰት በማለት ብዙዎች ውዳሴያቸውን አዥጎድጉደዋል።

በዜማው ሕዝባዊውን ሽለላ ከልዩ ፈጠራው ጋር በማዋሃድ አቅርቦታል። ዜማው ደም ያሞቃል፣ ግጥሙ ወኔ ይቀሰቅሳል ሲሉም ብዙዎች ሳይሰስቱ አድንቀውታል። የሙዚቃውን ጥራት ለመጠበቅ ጃማይካ ድረስ የሔደበትን ርቀት፥ ቴዲ አፍሮ ጥራት ላይ እንደማይደራደር ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። በርግጥም በሙዚቃው ውስጥ ድምጹም ሆነ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ ኩልል ብለው ይሰማሉ።

ብዙዎች ስለቴዲ አፍሮ አዲሱ ነጠላ ዜማ ትንታኔ የሰጡ ሲሆን ታወቂው ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲው መለሰ ተሸመ ለአብነት ተጠቃሾች ናቸው። ኹለቱም ‘‘ደሞ በአባይ (ከሞከሩንማ)’’ ትልቅ የጥበብ ሥራ መሆኑን መስክረዋል። ዓለምነህ ዋሴ በዘሐበሻ የዩቲዩብ ቻናል ላይ የዐሥር ደቂቃ ፕሮግራም አዘጋጅቷል። ‘‘እነሆ ወደዚህ ብሔራዊ ቋት፣ ብሔራዊ መሻት [ሕዳሴ ግድብ ማለቱ ነው] የአገራችን ኪነ ጥበብ ልዩ ሥም ቴዲ አፍሮ የጭብጡን ይዞ ደርሷል። . . . ከታወቀ እርጋታው እና ትዕግስቱ ወጥቶ ተቆጥቷል፤ ‘ቼ በለው!’ ሲል ትውልዱን ተጣርቷል። . . . በርግጥም ከያኒው ማስደመሙን ቀጥሏል’’ ሲል ዓለምነህ ዋሴ በአስገምጋሚው ጆሮ ገብ ወፍራም ድምፁ አድናቆቱን ገልጿል። የጥበብ ሥራው የቴዲ አፍሮን የረቀቅ፣ የመጠቅና ጠሊቅ የጥበብ ተሰጥዖ በድጋሜ አሳይቷል፤ ከፍታውንም ጨምሯል በማለትም ደምድሟል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲው መለሰ ተሸመ የጂጂን ‘‘አባይ’’ እንዲሁም የቀደሙትን የቴዲ አፍሮን ‘‘ኦ አፍሪካዬ’’ እና ‘‘አባይ’’ መነሻ አድርገው በነጠላ ዜማ ውስጥ ስላሉት እያንዳንዱ ሐረግ እና አንጓ ትርጉም እና ትዕምርት ጥልቅና ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል። መለሰ በማጠቃለያቸው ቴዲ አፍሮ ከፈጣሪ የጥበብ ፀጋን የተቸረ መሆኑን በመጥቀስ እስካሁን የሠራቸውን አምስት አልበሞች፣ በርካታ ያለስስት የሚለቃቸው ነጠላ ዜማዎች እንዲሁም ትሩፋቱ ለብዙዎች የተትረፈረፈ ሥራዎቹን በማስታወስ ‘‘እንዴት አንዱ እንኳን መጥፎ አይሆንም?’’ ሲሉ አግራሞት በፈጠረባቸው ጥያቄ ትችታቸውን አጠቃልለዋል።

በነገራችን ላይ የነጠላ ዜማው ግጥም በቴዲ አፍሮ እውቅና ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ በይፋ የተለቀቀ ሲሆን በፈረንሳይኛ እና አረቢኛ ቋንቋዎችም እንደሚተደጎም ታውቋል።

የሆነው ሆኖ ነጠላ ዜማውን በየትኛውም ቦታና ሰዓት ግን አለመስማት አይቻልም። በዩቲዩብ ቻናል የኢትዮጵያ ሙዚቃ አድማጭ ወተመልካች ብዛት ሪከርድ ሰብሯል ሲሉ ብዙዎች ተናግረዋል። ‘‘ደሞ በአባይ (ከሞከሩንማ)’’ በተለቀቀ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከአንድ ሚሊዩን ሰዎች በላይ የታየና የተደመጠ ሲሆን እስከ ትላንትና ዓርብ፣ ነሐሴ 1 ድረስ ከኹለት ሚሊዩን በላይ ተመልካቾች ሙዚቃውን አድምጠውታል። በዚሁ ቻናል ላይ 85 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ሙዚቃውን መውደዳቸውን ሲገልፁ፤ 18 ሺሕ ደግሞ አለመውደዳቸውን አስታውቀዋል። አንዳንዶች በግልጽ ስለአባይ ከጂጂ ወዲያ ማንም ቢመጣ አይጥመንም ሲሉ የቴዲ አፍሮን ነጠላ ዜማ አጣጥለውታል፤ ሌሎችም ደግሞ ‘‘የጦርነት አዋጅ ነጋሪ’’ ሲሉ ነቅፈውታል።ይህም ቴዲ አፍሮ በሥራዎቹ በብዙዎች የመወደዱን ያክል ቀላል የማይባሉት ነቃፊዎች እንዳሉት ያሳያል።
ለቴዲ አፍሮ ግን አወዛጋቢነቱ የጠቀመው ይመስላል፤ ምክንያቱም ሙዚቃዎቹ የበለጠ ተደማጭ እንዲሆኑ ጉልበት በመስጠት ሰበብ ሳይሆኑ አልቀሩምና።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here