የማኅበረሰብ ጋዜጦች ውድቀትና የዴሞክራሲ ፈተና

0
890

የዴሞክራሲ መታያ፣ ማረፊያና ማደሪያ የሚባልላት አሜሪካ የዚህ መልኳ አንደኛ መገለጫ የሆነውን የሚድያ አሠራር በሚመለከት የተለያዩ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ ይሰማል። በቁጥር እጅግ በርካታ የነበሩ የማኅበረሰብ ጋዜጦችም ከአንባብያን ዐይን በተለያየ ምክንያት በመሰወራቸው፣ አሜሪካ የቀደመ የዴሞክራሲ መገኛነቷን ይፈትናል እየተባለ ነው። አብረሐም ፀሐዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት የጋዜጦቹን ውድቀት ምክንያቶችና የሚያሳድሩትንም ተጽእኖ በዝርዝር አንስተዋል።

ዘ ጋርዳያን ይዞት የወጣው ጽሑፍ ስለጋዜጠኝነት በተለይም እንደማኅበረሰብ ሬዲዮ ሁሉ ስለአካባቢያቸው የሚዘግቡ የማኅበረሰብ ጋዜጦች በአሜሪካ አደጋ ላይ እየወደቁ ስለመሆናቸው አትቷል። በዚህም አገሪቷ ዴሞክራሲዋ እየነፈሰበት ነው የሚሉ ባለሙያዎች ተበራክተዋል። ምክንያቱም የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ የመረጃዎች ወደ ማኅበረሰቡ መድረስና ማንቃት መቻል መሆኑን ራሳቸው አሜሪካውያን የሚኩራሩበትና የሚያምኑበት በመሆኑ ነው።

‹የእነዚህ ጋዜጦች አቅም መዳከም ዴሞክራሲን አደጋ ውስጥ እየከተተ ነውና ማን ያድናቸው?› ይላል የዘጋርድያን ጽሑፍ ርዕስ። (Local journalism is on its knees – endangering democracy. Who will save it?) የኮሮና ወረርሽኝን እየታከከ ከጨዋታ ውጭ ካደረጋቸው ዘርፎች አንዱና አስገራሚው ስለራሱ መረጃ የሚያሰራጩትን የሚዲያ አውታሮች መሆኑ ነው።

በቅርቡ የጋዜጠኞች ለቫይረሱ ያላቸው ተጋላጭነት መጨመሩ፣ በሥራ ላይ ብዙዎችም ለህልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው ሲዘገብ ቆይቷል። አሁን ደግሞ መረጃው የሚሰራጭባቸው ጋዜጦች በገቢ እጦትና በሌሎች ምክንያቶች እየከሰሙ ይገኛሉ። ‹‹ጋዜጦች ሠራተኞቻቸውን እየቀነሱ ነው። በስተመጨረሻም ይህ ዘርፍ ወደመክሰሙ እየተጓዘ ይገኛል።›› ብለዋል የዘርፉ አጥኚዎች።

‹Ghosting the News› የተሰኘ መጽሐፍ ያበረከተችው የዋሽንግተን ፖስት አምደኛዋ ማርጋሬት ሱሊቫን (Margaret Sullivan) እንደምትለው በአሜሪካ የማኅበረሰብ ጋዜጦች አደጋ ውስጥ ከገቡባቸው ምክንያቶች አንዱ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ደጋፊዎቻቸው አወዛጋቢ መረጃና ከዚህ ጋር ተያይዥ የሆነ ጉዳይ ነው።

እርሷ እንዳለችው ትላልቅ የብዙኀን መገናኛዎች በፕሬዝዳንቱ ዙሪያ የተባሉና የተሰጡ መረጃዎችን እንዲሁም ሐሰተኛ ዜናዎች (ፌክ ኒውስ) የተባሉት ላይ የሚሰጡት የዜና ሽፋን ጋዜጣ ተከታታይ የነበረውን የማኅበረሰብ ክፍል ቀልብ እየወሰደ ይገኛል። በዚህም የተነሳ በአግባቡ መረጃ ተተንትኖ የሚቀርብባቸው ጋዜጦችን ለማንበብ ችላ በማለታቸው የመጣ ነው።

ጋዜጦች በይበልጥ ታማኝ የሚባሉ የዜና ምንጮች ናቸው። በተለይ ስለማኅበረሰብ ጉዳዮች ላይ በእውነተኛ ምንጭነት የሚያገለግሉ ሲሆኑ ዜጎች ስለዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የሚገነዘቡት እንዲህ ባሉ ጋዜጦች በጥንቃቄ የሚጻፉ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን በማንበብ ነው። በሐቅ ላይ የተመሠረቱ እውነተኛ ዘገባዎች ደግሞ የአንድ አገር ዜጎች የተስተካከለና ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።

አሁን ግን የዘርፉ ህልውና አደጋ ውስጥ በመግባቱና ጭራሹኑ እየሞተ በመምጣቱ የተነሳ ዴሞክራሲ ቀይ መብራት እያሳየ ይገኛል ተብሏል። በሚዲያው ዘርፍ ላይ ያሉ የኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርስቲ ምሁራን ለዘጋርዳይን እንደተናገሩት፣ ‹‹በአሜሪካ ላለፉት አራት ወራት የጋዜጦች ትርፍ በማሽቆልቆሉና ለኪሳራ በመዳረጋቸው የተነሳ ተቋማቱ ሠራተኞቻቸውን በመቀነስ እንዲሁም ድረ ገጾቻቸውን ጭምር በመዝጋት ላይ ይገኛሉ። ሙሉ ለሙሉ የዘጉም አሉ። ይህ ቁጥር ደግሞ በደርዘን ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች ላይ የታየ እውነት ነው።›› ብለዋል።

ጸሐፊዋ ሱሊቫን እንደገለጸችው፣ ይህ ጋዜጦች ላይ እየተከሰተ ያለው የመዘጋት አደጋ በቅርብ ጊዜ የሆነ ሳይሆን ቀስ በቀስ የተፈጠረ ችግር ስለመሆኑ ትገልጻለች፦
‹‹በአሜሪካ ከ2004 ጀምሮ 2000 ጋዜጦች ከሥራ ውጪ ሆነዋል›› ብላለች። ከዚሁ ጋር አያይዛ ‹ፌስ ቡክና ጎግል ለዚህ የጋዜጦች መቀጨጭና ከገበያ መውጣት ትልቁን ድርሻ ይዘዋል።›› ስትል ምክንያት ብላ ያመነችውን ታስቀምጣለች። ‹‹ከዚህ ቀደም ጋዜጦች ያገኙት የነበረውን ማስታወቂያ እነዚህ የኢንተርኔት መረቦች ከተከታዮቻቸው ብዛት አንጻር አስተዋዋቂ ድርጅቶች ምርጫቸው ስለሚያደርጓቸው እንደተሻሟቸውና ለጋዜጦቹ መዘጋትም ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል።›› በማለትም አስረድታለች።

የዴሞክራሲ ባህል ከአካባቢ የሚመነጭ ነው። ሥልጡን የመረጃ አሰረጫጨትን የሚከተሉት የማኅበረሰብ ሚዲያዎች አደጋ ውስጥ በወደቁ ቁጥር ሥልጡን አስተሳሰቦችም አብረው ይወድቃሉ። በዚህ የተነሳ ዴሞክራሲ ኪሳራ ውስጥ ይገባል። በአሜሪካ እየታየ ያለው ስጋትም ይህ እንደሆነ የተለያዩ የዘርፉ አጥኚዎች እየገለጹ ነው።

የማኅበረሰብ ጋዜጦቹ በስፖንሰር እጦት ለሠራተኞቻቸው መክፈል እስካለመቻል ደርሰዋል። ‹ሥራችንና ሕይወታችን ነው።› በሚል ይሠሩ የነበሩ የየሚዲያዎቹ ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሙያዎች ሥራ እጥ ለመሆን ተገደዋል። በሥራ ላይ ያሉት ጥቂት ጋዜጦች ላይ ይሠሩ የነበሩ ኤዲተሮችም ሥራቸውን በመልቀቃቸው የተነሳ የጋዜጦቹ ጥራት እንደቀድሞው ለመሆን አልቻለም። ይህ ሁናቴ ማኅበረሰቡን ለተባራሪ መረጃ በማጋለጥ ኃላፊነትን ለማይሸከሙ የድረ ገጽ ዜና አመንጪዎችም ሰለባ ማድረጉ አይቀሬ እንደሆነ ግልጽ ነው።

አበርናቲ (Abernathy) የተባሉት የኖርዝ ካሮሊና ዩኒቨርስቲ ምሁር በ2018 ባጠኑት ጥናት በአሜሪካ ውስጥ ወደ 1300 የሚሆኑ አካባቢዎች፣ ስለአካባቢያቸው መረጃ ይዘው ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች ከሥራ በመውጣታቸው የተነሳ መረጃ አልባ ማኅበረሰብ ለመሆን ተገደዋል ብለዋል።

ሱሊቫን እንደገለጸችው ደግሞ የኮምዩኒቲ ጋዜጦች ሥራ በማቆማቸው የተነሳ የየአካባቢው የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት ጥራታቸው ወርዷል። ‹‹የማዘጋጃ ቤቶቹ ወጪዎች ከፍ እያሉ መጥተዋል፤ ከብድር ጋር ተያይዞ የአሠራር ብልሹነት ታይቷል፤ የሙስና ምልክቶችም ተከስተዋል። ይህ የሆነው የእነዚህን አካላት መደበኛ እንቅስቃሴ ይከታተሉ የነበሩ ሚዲያዎች በመዘጋታቸው ነው።›› ስትል ጸሐፊዋ አክላለች።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ጋዜጦች በአጠቃላይ ሚዲያዎች የማኅበረሰብ ዘብ ናቸው። ተራው ሕዝብ ውስብስብ ለሆኑ የመንግሥት አሠራሮች ያለው መረጃ እምብዛም ነው ወይም ጠለቅ ባለ መልኩ ላይረዳ ይችላል። ገንዘቡን ከፍሎ ማግኘት ለሚሻው አገልግሎት ከጊዜና ከወጪ አንጻር ብልሹ አሠራር እንዳይገጥመውና በዚህ የተነሳ መብቱን እንዳያጣ ጠባቂዎቹ ሚዲያዎች ናቸው።

ሚዲያዎች ጥቆማ በመስጠትና የማኅበረሰብ መብትና ግዴታን በማሳወቅ ጭምር እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምን ያህል ኃላፊነታቸውን ከተቀመጠላቸው መስፈርት አንጻር እየተወጡ እንደሆነ በቂ መረጃ በመስጠት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ትልቁን ድርሻ የሚወጡ ናቸው።

አዳጊ አገራት ላይ የሚታየው ትልቁ የሀብት ብክነትና በሥልጣን መባለግ መነሻ ምክንያቶች አንዱ ሚዲያዎች እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር ነው። በተያያዘም ያሉትንም ሚዲያዎችም የራሳቸው ልሳን በማድረግ ወይም በጥቅም በመደለል ከሕዝብ ልሳንነት ወደራሳቸው አገልጋይነት በማዛወር መረጃ በበቂ ሁኔታ እንዳይተላለፍ በማድረግ ነው። የኢ-ዴሞክራሲያዊነት መገለጫ አንዱ የመረጃ ሳንካ መሆን ነው።

ሚዲያ ማኅበረሰብን በማንቃት መብቱን እንዲያውቅ፣ እንዲጠይቅና እንዲያስከብር የሚገፋ ትልቅ ኃይል ነው። ግዴታንም ያሳውቃል። በሌላ መልኩ ሚዲያ አዳዲስና ወቅታዊ መረጃዎችን በወቅቱ በማቅረብ የዕውቀት ሽግግር ያደርጋል።

ሚዲያ የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴን በእውነተኛ መረጃዎች ላይ የተመረኮዘ በማድረግ የተስተካከለ አሠራር እንዲኖር በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አውታር ነው። ፍርድ እንዳይዛባ፣ አገልግሎት እንዳይስተጓጎል፣ ኢ-ፍትሃዊነትና አድሎ እንዳይፈጠር በንቃት በመጠበቅ በአገር ደረጃ የነቃ ማኅበረሰብና ሥራቸውን በአግባቡ የሚከውኑ መንግሥትና የግል ተቋማት እንዲፈጠሩ በማድረግ በኩል ትልቅ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
በአጠቃላይ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሚዲያ መሠረት ነው። ሚዲያ ዴሞክራሲን የሚገነባ የመረጃ ኃይል ነው።

በአሜሪካ የኮምዩኒቲ ጋዜጦች መዳከም እንደትልቅ ጉዳት እየታየ ነው። በቂ መረጃ በማጣት ማኅበረሰቡ መብቱንና ኃላፊነቱን እየሳተ በመሄድ ላይ ነው እየተባለ ነው። በምርጫ ደረጃ እንኳን ሕዝቦች መረጃ አልባ በሆኑ ቁጥር የነሱ ወካይ ወይም ቅን አገልጋይ ያልሆኑትን እጩ ሊመርጡ ይችላሉ።

በአሁን ጊዜ እንደስጋት እየታየ ላለው የጽንፈኝነትና ቀለም ተኮር እንቅስቃሴና ዘርን የለየ አመለካከት እንዲስፋፋና እንዲባባስ በማድረግ በኩል ከዚህ ቀደም በመቻቻል ላይ የተመሠረተ አሜሪካዊነትን ይጽፉ የነበሩ ጋዜጦች በመጥፋታቸው ጭምር እንደሆነም መላምት እየተሰጠ ነው። ሕዝብ አጠገቡ አንቂ የሆነ ሚዲያን ባጣ ቁጥር እንደማኅበረሰብ መወጣት ያለበትን ኃላፊነት በመተው ኋላ ቀር ማንነትን እየያዘ መምጣቱ አይቀሬ እንደሚሆንም ምሁራኑ እያሳሰቡ ነው።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሚዲያዎች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ በመግባት ይታወቃሉ። የእርሳቸው ከሚዲያ ጋር ያላቸው ፈር የለቀቀ ግንኙነት ሚዲያዎቹንና ጋዜጠኞችን በማጣጣል የሚሰጡት አስተያየት በደጋፊዎቻቸው ዘንድም ስለሚዲያ ተገቢ ያልሆነ አመለካከት እንዲኖራቸው እያደረገ ነው። ጋዜጠኞች ልክ እንዳልሆኑ በተነገረ ቁጥር ማኅበረሰቡ ለሚዲያና ባለሙያ የሚሰጠውን ክብር እየተወ ስለሚመጣ ከአብሮነት ይልቅ ለጥቂት ቡድኖችና ትናንሽ ሐሳቦች ተገዢ መሆንን ያስከትላል።

ሱሊቫን ይህን ጉዳይ ስታጠናክረው ‹‹ትራምፕ ለሚዲያ ያላቸው አመለካከት በሚዲያው ላይ ለተከሰተው አሉታዊ ውጤት አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህም መጥፎ ነገር ፈጥሯል። እሳቸው የሚዲያውን ዘርፍ ጎድተውታል። እከሌ የሚባለው ሚዲያ ስህተት ነው፤ እከሌ የተባለው ጋዜጠኛ አይረባም ብለው ባንጓጠጡ ቁጥር ለማኅበረሰቡ ስለሚዲያ የሚያስተላልፉት መልዕክት ለዘርፉ በጣም ጎጂ ሆኗል። ማኅበረሰቡም ለሚዲያ ያለው እይታ የወረደ እንዲሆን ድጋፍ እያደረጉ ነው።›› ስትል ትከሳቸዋለች።
የአሜሪካ ዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ መረጃ በግልጽነት ወደማኅበረቡ ተደራሽ መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻርም ነው የመረጃ ምንጮች ሲደርቁ ከዴሞክራሲ መቀጨጭ ጋር የሚያያዘው። ይህን የጋዜጦች ህልውና ከገባበት አደጋ ለማዳን አስተያየት የሚሰጡ ምሁራን አሉ፦

‹‹ጋዜጦች መረጃዎቻቸውን ከዲጂታል ጋር በአግባቡ በማያያዝና የአባሎቻቸውን ቁጥር በመጨመር ህልውናውን ማስመለስ ይችላሉ።›› የሚል ነው። ሱሊቫንም እንደምትለው የአሜሪካ ዴሞክራሲ የተገነባው አግባብ ባለው መረጃ የነቃ ሕዝብን በመፍጠር ነው። ስለሆነም መረጃዎች እንዳይቋረጡ ገቢን በመፍጠር የመረጃ ምንጭ የሆኑትን ጋዜጦች ማዳን ይገባል።›› ትላለች።

በስተመጨረሻ ዘ ጋርዲያንም ለአንባቢዎቹን የሚናገረውን መልዕክት አይተን ንባባችንን እንቋጭ፦
‹‹ሚዲያችን ለእውነተኛ መረጃዎችና ዜናዎች ይተጋል። ማስታወቂያቸውን በሚያስነግሩ ድርጅቶች ስር መሆንን አንሻም። እነሱም ለዓለማቸው እኛም ለጋዜጠኝነቱ! ከፖለቲከኞችና ከባለጸጋዎች የራቀ ነጻ ጋዜጠኝነትን ለማራመድ እንድንችል እናንተ አንባቢዎች በድጋፍ ከጎናችን ቁሙ። የራሳችንን አጀንዳ ፈጥረን፣ ነጻ ሐሳብ አራምደን ወደ ሕዝብ የተሻለና በሐቅ ላይ የተመሠረተ ጥራት ባለው ጋዜጠኝነት መረጃ እናደርሳለን። ለሁሉም ሰው ሚዛናዊ ዜናዎችን ለማምጣት ራሳችንን በአቅም ማጠናከር አለብንና የገንዘብ ምንጫችን እናንተም ልትሆኑ ይገባል።›› ይላል።

ጋዜጠኝነት እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ባሉ ስለጋዜጠኝነት ብዙ በሚያውቁ የበለጸጉ አገራት ውስጥ እንዲህ ያለ ፈተና ላይ ነው። እንደኛ ባሉ አዳጊ አገራት ውስጥ ያለውን መገመት ደግሞ ቀላል ነው። የገንዘብና የፖለቲካ ጉልበት ያላቸው አካላት እስከዛሬ ድረስ ተጭነውት የቻሉትን የራሳቸው በቀቀን፣ ያልቻሉትን ደሞ በተለያዩ ጫናዎች በማስወገድ ሕዝቡ ልዩነት አልባ መረጃዎች እየተጋተ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና በማኅበረሰባዊ እሴቶቹ ላይ ልዩነት ማምጣት እንዳይችል እየተደረገ ነው። ያም ሆነ ይህ ጋዜጠኝነት ያለበትን ጭነት የሚያነሳለት የለም፤ ከራሱ በስተቀር!

አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here