በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር)
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አባል ከሆኑት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሌላኛው የድርጅቱ አባል ፓርቲ ከሆነው ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጋር በተፈጠረ የአቋም ልዩነት በመድረክ ውስጥ መቀጠል እንደሚቸገር አስታወቀ።
ኢሶዴፓ ለአዲስ ማለዳ አንዳስታወቀው በመድረክ ግንባር ውስጥ ወደፊት ላለመቀጠል ምክንያት ነው ያለው ኦፌኮ ከመድረክ ውጪ ኢሶዴፓ ባልተስማማበት ጉዳይ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የትብብር ፊርማ በመፈራረሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ተናግረዋል።
እንደ ፕሮፌሰር በየነ ገለፃ ኢሶዴፓ በተለይ ከኦፌኮ ጋር አሁን እየተንቀሳቀሰበት ባለው ሁኔታ ወደፊት ቀጥሎ መሥራት እንደማይችል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ነገር ግን የመድረክ ግንባር አባላት የሆኑ ፓርቲዎች ከኢሶዴፓ ጋር በጋራ ጉዳይ ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆኑ ወደፊት በአገራዊ ጉዳይ ላይ አብረው ሊሠሩ እንዲሚችሉ ጠቁመዋል።
አክለውም ኦፌኮ ከመድረክ አባል ድርጅቶች ውጪ በሆነ አቋም በመድረክ ሥምና የመድረክ አባል ድርጅቶች ከማያውቋቸው ድርጅቶች ጋር ቅንጅትና ትብብር ፈጠርኩ በሚልበት ሁኔታ አብረው ለመሥራት መቸገራቸውን አመላክተዋል።
የመድረክ ስብስብ ዋና አጀንዳ አገራዊ ትኩረት መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ኦፌኮ አሁን እየተንቀሳቀሰ ያለበት አካሄድ ከአገራዊ አጀንዳ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን በመድረክ ግንባር ውስጥ ከኦፌኮ ጋር እንድንቀጥል አልፈለጉም።›› ሲሉ አብራርተዋል። በመሆኑም ደጋፊዎቻችን የሚያስተጋቡትን አቋም እንከተላለን ሲሉ ጠቁመዋል።
መድረክ ባሳለፍነው እሁድ ሐምሌ 26/2012 ባካሄደው ስብሰባ ላይ የግንባሩ አባል የሆኑት የኦፌኮ፣ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዓረና) እና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ሲገኙ ኢሶዴፓ በስብሰባው ላይ እንዳልተሳተፈ ፕሮፌሰር በየነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የመድረክ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) በበኩላቸው ኢሶደፓ በስብሰባው ላይ እንዳልተሳተፈ ገልጸው፣ ሌሎች አባል ድርጅቶች ጋር ስብሰባውን እንዳይካሄዱ ተናግረዋል። እንደ መረራ ገለፃ በተባለው ቀን መድረክ ያካሄደው ስብሰባ አሁን ባሉት አገራዊ ጉዳዮች ላይ መሆኑን አመላክተዋል። በተይም በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ችግር ስላለ ኦፌኮ እንዲሁም በትግራይ ስላለው ኹነት ዓረና ስላሉ ምን ይደረግ በሚል መምከራቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።
በመድረክ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት በተራዘመው አገራዊ ምርጫ ጭምር የነበረ መሆኑን ፕሮፌሰር በየነ አስታውሰዋል።
የተራዘመውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ የኢሶዴፓ አቋም ባልሆነና ባልተሳተፈበት ሁኔታ በመድረክ ስም የፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲራዘም የወሰነውን አገራዊ ምርጫ እንቃወማለን የሚል መግለጫ ማውጣታቸው ከቀደሙት ልዩነቶች ውስጥ መሆኑን የኢሶዴፓ ሊቀመንበር ጠቁመዋል።
አገራዊ ምርጫን በተመለከተ የኢሶዴፓ አቋም የምርጫውን መራዘምና ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ ይሰጠው የሚለውን ሐሳብ ደግፈው እንደነበር ሊቀመንበሩ አስታውሰዋል።
የመድረክ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ኢሶደፓ ከመድረክ ጋር ወደፊት ላለመቀጠል የፈለገበት ምክንያት መድረክ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር ለመፍጠር በመንቀሳቀሱ እና የትብብር ሥራ በመሥራቱ እንደሆነ ጠቁመዋል። እንደ መረራ ጥቆማ የልዩነቱ ዋና ምክንያት መድረክ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር መፍጠሩ ቢሆንም ሌሎች የልዩነት ነጥቦችን መናገር አልፈልግም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መድረክ ከ10 ዓመት በፊት በስምንት የፖለቲካ ድርጅቶች የተመሰረተ፣ በአገራዊ አጀንዳ ላይ የሚሠራ ግንባር መሆኑን ያስታወሱት በየነ ጴጥሮስ፣ ግንባሩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በብዙ ውጣ ውረድ ማለፉን ጠቁመዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012



