በ2012 አገር አቀፍ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ የሚገኙ ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ተገቢውን የኮምፕዩተር ሥልጠና ሳናገኝ ፈተና ላይ ልንቀርብ በመሆናችን ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀናል ሲሉ አስታወቁ።
በዘንድሮው ዓመት የሚሰጠው የአገር ዐቀፍ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ የፈተና አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸው ችግር ውስጥ እንደከተታቸው አስታውቀዋል። እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም በተገቢው እና ኃላፊነት በተሞላው መንገድ እየተሰጠን አይደለም ሲሉ ዐይነ ስውራን ተፈታኝ ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (አምስት ኪሎ ካምፓስ) ቅጥር ጊቢ ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉት ዐይነ ስውራን ተማሪዎች፣ ከተለያየ አቅጣጫ የመጣን መሆናችን እየታወቀ ነገር ግን የኮቪድ 19 ምርመራ ሳይደረግልን ብሎም እንደማንኛውም መሥርያ ቤት ሙቀት ልኬት እንኳን ሳይደረግ መግባታችን ከተባለው በላይ እያስፈራን ይገኛል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
‹‹በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ግን ምርመራ ተደርጎልን እና የንፅህና መጠበቂያዎች ተሟልተውልን እንደገባን እየተናገሩ መሆኑን እያስተዋልን ነው።›› በማለትም ሐሰት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዛም በተጨማሪ አሁን በሚገኙበት ቅጥር ጊቢ ውስጥ (አምስት ኪሎ ካምፓስ) ሥልጠናውን ለመውሰድ ሲገቡ ማንም አካል ቁጥጥር እንዳላደረገላቸው እና ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነው ተማሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
ከዛም ባለፈ የሥልጠና ጊዜው አጭር ቢሆንም አዳራሽ ውስጥ ያለን ቆይታ አይገደብም ብለዋል።
‹‹የሥልጠናው ጊዜ አጭር ከመሆኑ አኳያም ለትምህርት ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናነሳም ምንም ምላሽ አላገኘንም።›› በማለት ጠቁመዋል። ነገር ግን ሥልጠናውን ከሚሰጣቸው አካል የተመለሰላቸው መልስ ‹‹በእናንተ ችሎታ ላይ ተመሥርቶ ነው በዚህ መልኩ እንድትፈተኑ የሚደረገው እንጂ ችሎታው ከሌላችሁ እና ልምዱን ካላገኛችሁ ከዚህ ቀደም በነበረው አፈታተን ሂደት መፈተን ትችላላችሁ›› መባላቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።
‹‹አሠልጣኛችን ይሄን ይበሉ እንጂ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ምላሽ አላገኘንም።›› በማለት ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
በተያያዘም ኮሮናን ለመከላከል በሚል ሥልጠናው በፈረቃ ይሰጥ ተብሎ የፕሮግራም ምድብ ይውጣ እንጂ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነም አክለው ተናግረዋል። ‹‹በአንድ ክፍል ውስጥ በፈረቃው ምክንያት ከተመደበው ቁጥር በላይ ነው ተሰብስበን ሥልጠናውን የምንከታተለው። ምክንያቱም የከሰዓት ፈረቃው ስለማይከበር አንድ ላይ ገብተን እንዲሰጠን ይደረጋል።›› ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁን እና አንዴ ሥልጠና ስለተባለ እንጂ ቀድሞ የገባ እና ኮምፕዩተር ቀድሞ ያገኘ ሠልጣኝ ነው ተጠቃሚ የሚሆነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ተማሪዎቹ እንዳነሱት ከሆነ ለሚመጣው አጠቃላይ ፈተናም ሆነ ካለው ወቅት ጋር የሚነሳውን ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነባቸው እና ትምህርት ሚኒስቴርም በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይየን በማለት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀረጓ ማሞ፣ ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ሥልጠናን በተመለከተ አምስት ሳምንታት የሚቆይ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው አውስተዋል። ‹‹ሥልጠናው ምንም አይነት ኮምፕዩተር ነክተው ለማያውቁ ዐይነ ስውራን ተማሪዎች እድል ያመቻቸ ነው።›› በማለት ተናግረዋል።
እርሳቸው እንዳነሱቱ የሥልጠናው ዋና ዓላማ አቀላጥፈው እንዲችሉ ታስቦ ሳይሆን ዋና እና መሠረታዊ የኮምፕዩተር ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ብለዋል። አያይዘውም ሥልጠናው ከተጀመረ አንድ ሳምንት ያስቆጠረ ቢሆንም ቀላል የማይባል ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል። ሥልጠናው የሚሰጠውም ዐይነ ስውራን በሆኑ መምህራን መሆኑ ደግም በቀላሉ ልምድ ለመለዋወጥ ይረዳል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ጉብኝት አድርጎ ጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል፡፡ የፈተና አሰጣጡ ላይም ለሚነሳው ቅሬታ ሥልጠናው ካበቃ እና ግምገማ ከተደረገ በኋላ የሚወሰን ውሳኔ ይኖራል በማለት ጠቁመዋል። ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ደግሞ ከሚደረገው ጥንቃቄ ባለፈ የሥልጠና አሰጣጡ በፈረቃ እንዲሆን አድርገናል። እሱም እየተተገበረ ነው በማለት በተማሪዎች በኩል የተነሳውን አቤቱታ አስተባብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012


