የኩላሊት ዕጥበት ተጠቃሚዎች በሆስፒታሎች ውስጥ በኮሮና እየተጠቁ መሆናቸው ተገለጸ

0
889

ከፍተኛ የኩላሊት ሕመምተኞች ሆነው በተለያዩ ሆስፒታሎች የኩላሊት ዕጥበት የሚያከናውኑ ሕመምተኞች ለሕክምና በሚሔዱባቸው ሆስፒታሎች ውስጥ በኮቪድ 19 እየተያዙ መሆናቸው ተገለጸ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በኮሮና ቫይረስ ሂወታቸው ከሚያልፉት ተጠቂዎች ውስጥ የኩላሊት ህሙማኖች ሆነው ዕጥበት የሚያከናውኑ እንደሆኑ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አስታውቀዋል።

ምንጮቻችን እንዳነሱት ከሆነ በኢትዮጲያ ካሉት የኩላሊት ህሙማኖች ( እጥበት ከሚያከናውኑት) አብዛኞቹ በኮሮና ቫይረስ እየተያዙ መሆናቸውን እና ፅኑ ህሙማን ውስጥ እነምደሚገኙ ጠቅሰውልናል::

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘም ያነጋገርናቸው የኩላሊት ህሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አሲኪያጅ ሰላሞን አሰፋ እንዳሉት ከሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኩላሊት ህሙማኖች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ያረጋገጡልን ሲሆን ፤ ነገር ግን እያገገተሙ ያሉትም ከፍተኛ ናቸው በማለት አንስተዋል ።

ከዚህ በተጨማሪ ሰለሞን እንዳነሱት ከሆነ የሟቾች ቁጥር በውል እንደማያውቁት እና ስነልቦና ላይ በሚፈጥረው ጫና ምክንያት ባይጠቀስ መልካም ነው ብለው እንደሚስቡም ተናግረዋል። ነገር ግን የስርጭቱ መጠን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራት ይኖርበታል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

ከዛ በተጨማሪም የኩላሊት ህሙማኖቹ አብዛኞቹን ለኩላሊት ሕክምና በሔዱበት ሆስፒታል ውስጥ ይዟቸዋል ብለው እንደሚያስቡ አንስተው ፤ ይህም የሆነው አብዛኘውን የኩላሊት ህመም ተጠቂዎች እና በመሃበሩ ያሉ እጥበት የሚያከናውኑ አካላት ዘለግ ላለ ጊዜ ከመተዋወቃቸው አኳያ እንደ ቤተሰብ ነው የሚተያዩት። ‹‹ምግብን ከአንዱ ቤት መቶ አብሮ ተሰብስቦ መብላት እና በአንድ እጥበት ማከናወኛ ከፍል ውስጥ ሰብሰብ ብሎ የመገኘቱ›› ነገር ልምድ ሆኖ በመቀጠሉ ምክንያት ነው ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ አንዳንዶቹ ለብቻቸው( በግል ትራንስፖርት ተጠንቅቀው ሲመጡ ፤ ሌላው ደግሞ በህዝብ ትራንስፖርት ይመጣል፤ ከዛም ቫይረሱ ከየት እንደተነሳ ሳይታወቅ እየተሰራጨባቸው እንደሆነ አንስተዋል።

በተያያዘም በጤና ሚኒስቴር ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆኑት ዮርዳኖስ አለባቸው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ ኩላሊት ህሙማን ብቻ በኮሮና ቫይረስ እየሞቱ ነው ተብሎ መለየት ባይቻልም አጠቃላይ ተጓዳኝ ያለባቸው ሰዎች ግን በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባችወ መሆኑን ተናግረዋል፤ ኩላሊት ህሙማንም እዚሁ ላይ ነው የሚካተቱት ብለዋል።

በአሁኑ ሰአት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ ፤ በበሽታው ላይ ያለው መዘናጋት ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውም ሰዎች ላይም ይሁን ተጓዳኝ በሽታ የሌለባቸውም ሰዎች ላይ እየታየ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ በላይ ከፈተኛ ዋጋ ሊያስከፍለንም ይችላል በማለት አንስተዋል።

እንደሚታወቀው አዲስ ማለዳ በ83 ተኛ እትሟ ላይ የኩላሊት ህመምተኞች ለኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ከመሆናቸው ባለፈ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸው ተነስቶ ነበር።
በዚህም የበሽታው ስርጭት እነርሱ ላይ ከመበርታቱ በፊት ለቅድመ ጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ ምልክቱን ከማሳየታቸው በፊት የኩላሊት ህሙማኖች የኮሮና ቫይረስ ምርምራ ሊደረግላቸው ይገባል በማለት ከጤና ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን የተጠቀሰበት ሁኔታ ነበር ። ምክንያቱም በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ቫይረሱም ቢይዛቸው ቅድመ ምልክት ምንለውን ትኩሳት ማሳየት እንደማይችሉ እና በዛም የግድ ለሁሉም ተጠቂዎች (በተለይም የኩላሊት እጥበት የሚያከናውኑ) ምርመራ እንዲደረግላቸው እየተደረገ ነው” ሲሉ ሰለሞን አሰፋ ለአዲስ ማለዳ አንስተው እንደነበር የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here