ለግድቡ ግንባታም እስካሁን በአጠቃላይ 13 ቢሊዮን 680 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል
ባሳለፍነው የሀምሌ ወር ላይ የተከናወነውን የመጀመሪያው ዙር የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌትን ተከትሎ በተፈጠረው ከፍተኛ የህዝብ መነቃቃት ምክንያት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ መቻሉን የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
በተለይም በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የግድቡን ስራ ለማጠናቀቅ የሚውል ገቢን ለማሰባሰብ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ኃላፊው አስታውቀው ይህም ገቢ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በዲያስፖራ ኤጀንሲ በኩል ለጽህፈት ቤቱ እየደረሰ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 አንስቶ እስከአለፈው ሰኔ 2012 ድረስ 13 ቢሊየን 680 ሚሊየን ብር ለግድቡ ግንባታ መሰባሰብ መቻሉንም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
እንደ ኃይሉ ገለፃ ከተሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 1 ቢሊየን 6 ሚሊየን (1.006) ብር የሚሆነው ከአገር ውጪ ከሚገኘው የዲያስፖራ ማህበረሰብ በቦንድ ሽያጭ እና በስጦታ የተገኘ ነው። የተቀረውም ከ12 ቢለየን ብር በላይ የሚሆነው ገቢ በአገር ውስጥ ከሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በ8100 A እንዲሁም የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት በሚያዘጋጃቸው የማህበረሰብ አሳታፊ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች አማካኝነት የተሰበሰበ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም እየተገባደደ ባለው የ2012 ብቻ እስከ አንድ ነጥብ ኹለት ቢሊየን ብር ድረስ ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የእቅዱን 62 በመቶ በማሳካት 745 ሚሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ኃይሉ አስታውቀዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን ከፍተኛ ስጋት እየሆነ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሺን ከተከሰተበት ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ባለው ጊዜ ውስጥም 266 ሚሊየን ብር በቦንድ፣ በስጦታ እንዲሁም በ8100 A አማካኝነት የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በአራት ወራት ከ8100 A ብቻ ከ29 ሚሊየን ብር በላይ መገኘቱንም ኃላፊው ጨምረው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ሰአት የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በአዲስ አበባ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች እየተዘዋወረና ገቢ እየተሰበሰበበት እንደሚገኝ ኃይሉ የጠቆሙ ሲሆን፤ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ዋንጫው ተዘዋውሮ 47 ሚሊየን ብር እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ ደግሞ በ45 ቀናት ውስጥ 101 ሚሊየን ብር (81 ሚሊየን በጥሬ ገንዘብ የተሰጠ እንዲሁም ቀሪው 20 ሚሊየን ብር ሊሰጥ ቃል የተገባ) በቦንድ እና ቃል በመግባት መሰብሰቡን አስታውቀዋል። በአሁኑ ሰአት ሁሉም ቃል የተገቡት ገንዘቦች እየተሰጡ እንደሚገኙ መረጃው እንደደረሳቸውም ለአዲስ ማለዳ ጨምረው አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ኹለት ክፍለ ከተሞች ብቻ የህዳሴ ግድብ ዋንጫን በማዘዋወር 148 ሚሊየን ብር በገንዘብ እና ቃል በመግባት መሰብሰብ መቻሉን የገለፁት ኃላፊው፤ በአሁኑ ሰአትም ዋንጫው በልደታ ክፍለ ከተማ እንደሚገኝና በቀጣይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች የማዘዋወር ገቢ የመሰብሰብ እቅድ እንዳለም ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እየተዘጋጁ በሚከናወኑ መርሃ ግብሮች አማካኝነት ማለትም ከ8100፣ ከወረቀት ሎተሪ፣ ከቶንቦላ ሎተሪ፣ ከሩጫ ቲሸርቶች ሽያጭ፣ ከእግር ኳስ ጨዋታዎች፣ ከሙዚቃ ክሊፖች እንዲሁም ሙዚቃዊ ድራማና መሰል ክንውኖች በአጠቃላይ ከ244 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘት መቻሉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
የ8100 A ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚያበቃ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ህዝብን መቀስቀስና ማህበረሰቡን የሚያሳትፉ መድረኮችን ማዘጋጀት ካልተቻለ ይኸው መርሃ ግብር የሚቀጥል እንደሚሆንም ኃይሉ ገልፀዋል።
በዚህም መሰረት እስከአሁን ያለው የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ የሚያበረታታ ነው ያሉት ኃይሉ የጥበብ ባለሙያዎች በዚህ ባለንበት ወር ብቻ ከ10 በላይ የሚሆኑ የቪዲዮ ምስሎችን ሰርተው ይተላለፍ በማለት ለህዳሴው ግድብ በስጦታ መልክ መስጠታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም በዚህ መልኩ የተለያዩ ጥበባዊ ስራዎች፣ ማስታወቂያዎች እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ የሚሰሩ ማንኛውም አይነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በሁሉም አማራጭ ሚዲያዎች በመጠቀምና በማስተላለፍ ህብረተሰቡን የማነቃቃትና ብሄራዊ ንቅናቄን የመፍጠር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስታወቅ በመጪው ዓመትም የኮቪድ 19 ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከንክኪ የፀዱ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በእቅድ ደረጃ መያዛቸውን በመግለፅ እነዚህም መርሃ ግብሮች በስራ አስፈፃሚው ሲፀድቁ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ኃላፊው ጠቁመዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012



