በኹለት ሳምንት የኮሮና ምርመራ ዘመቻ 8ሺሕ ሰዎች በሽታው ተገኝቶባቸዋል

0
808

በኹለት ሳምንታት ውስጥ ለ200 ሺህ ሰዎች ምርመራ ለማድረግ ታስቦ በተካሔደው ዘመቻ ከተደረገው 182ሺህ 497 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 8 ሽሕ የሚሆኑ ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተገለጸ። መያዛቸው የጤና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በሁሉም አካላት በተደረገው ጥረት በማህበረሰቡ ዘንድ በሽታውን የመከላከል ግንዛቤ ያደገ ቢሆንም በተግባር የመከላከል ስራው አሁንም በተፈለገው መጠን ባለመሆኑ በሽታው እየተስፋፋ፣ በፍጥነት እየጨመረ እና የታማሚዎች ቁጥርና የሚሞቱ ሰዎች መጠን እያደገ መምጣቱን ተናግሯል፡፡

ነሐሴ 1 ቀን 2012 የተጀመረው በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎችን የመመርመር መርሃ ግብር እስከ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ድረስ 182 ሺህ 497 የምርመራ ናሙና ዎችን መሰብሰብ ተችሏል፤ ይህ ማለት የዕቅዱን 92 በመቶ ማሳካት ተችሏል ተብሏል፡፡

ይህ ዘመቻ ከተጀመረ በኃላ የመመርመር አቅሙ በቀን በአማካኝ 15 ሺህ ደርሷል የተባለ ሲሆን የማህበረሰብ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻው ከመጀመሩ 7ቀን በፊት ከነበረው የምርመራ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር ዘመቻው ከጀመረ ከ7 ቀን ወዲህ የምርመራ አቅሙ በ78 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ተብሏል፡፡

ከዛም በተጨማሪ ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ በ7 ቀናት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 80 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አዲስ ማለዳ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ የኮሮና ቫይረስ በምርመራ የሚገኝባቸው ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በማኅበረሰብ ቅኝት እና ዳሰሳ የተገኙ ሲሆን በለይቶ ማቆያ ከገቡት ውስጥ በሽታው መኖሩ የተረጋገጠባቸው ሰዎች ከ10 በመቶ በታች መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡ በዚህ ምርመራ የተገኙ 27 ሺህ 60 ታማሚዎች ወደ ህክምና ማዕከላት የገቡ ሲሆን 25 ሺህ 51 ደግሞ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል ተብሏል ፡፡ የተቀሩት ታማሚዎች በመኖሪያ ቤታቸው እራሳቸውን እየለዩ እንዲቆዩ እየተደረገ የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዮርዳኖስ አለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

እንደሚታወሰው ከሁለት ሳምንት በፊት አዲስ ማለዳ የጤና ሚኒስቴርንን ዘመቻውን ተከትሎ ባነጋገረች ሰዓት በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ከነሐሴ 1/2012 ጀምሮ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ቀናት (ኹለት ሳምንት ) ውስጥ 200 ሺሕ ለሚደርሱ ሰዎች የኮቪድ 19 ምርመራ ለማድረግ እንደታቀደ እና በዚህም 10 ሺህ የሚጠጉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ይገኛሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ የጤና ሚኒስቴር ገልፀዋልን ነበር፡፡ በተያያዘም በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሚጀመረው እንቅስቃሴም 80 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በኹለት ሳምንት ውስጥ የሙቀት ልየታ እንደሚደረግ የጤና ሚኒስቴር ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

እንደ ዮርዳኖስ ገለፃ አገር ዐቀፍ ንቅናቄው ያስፈለገበት ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን መዘናጋት ተከትሎ እየመጣ ያለውን የስርጭቱን መጨመር ለመቆጣጠር፣ ከመመርመር ባሻገር ደግሞ ማስተማር እና ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ነው ብለዋል።

ከዛም ባሻገር በምርመራው የተለዩትን ተጠቂዎች ከዚህ ቀደም በወጣው መመርያ መሰረት በከባድ ሁኔታ ቫይረሱ እየጎዳቸው ያሉትን ማለትም ፅኑ ታማሚ የሆኑትን አፋጣኝ ሕክምና እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው። የተቀሩትን እና የቫይረሱ ተፅእኖ ያልጎላባቸው እንዲሁም ምልክት የማያሳዩትን ደግሞ ቫይረሱ እንዳለባቸው በማመላከት እራሳቸውን አግልለው እንክብካቤ እንዲያደርጉ ለማድረግ መሆኑን ተናግረው ነበር።

የጤና ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ በጀመረው ዘመቻ በ ኹለት ሳምንታት ውስጥ ለ80 ሚሊዮን ዜጎችን የሙቀት ልየታ ለማድረግ ያቀደ ቢሆንም አዲስ ማለዳ ለሕትመት እስከ በቃችበት ድረስ የሙቀት ልየታ የተደረገላቸው ዜጎች ቁጥር በውል ለማወቅ አልተቻለም

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here