የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር 43 ሺሕ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ማንሳቱን አስታወቀ

0
791

የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ 43 ሺህ ዜጎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከላከልና ለማቋቋም ከጎዳና ላይ ማንሳት መቻሉን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ኑሮና አዳራቸው ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከላከልና ለማቋቋም ከጎዳና ላይ የተነሱ 43 ሺህ 396 ዜጎች ከአዲስ አበባ ከተማ 1 ሸህ 59፣ ከኦሮሚያ 17 ሺህ 522፣ ከአማራ 16 ሺህ 954፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 4 ሺህ 033፣ ከትግራይ 3 ሺህ 125፣ ከድሬደዋ ከተማ 297፣ ከሐረር 406 ዜጎችን ከጎዳና ላይ እንዲነሱ መደረጉን ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በተጨማሪም በቀጣይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 269 ዜጎችን ለማንሳት ቅድመ ዝግጅቱ መደረጉም ተጠቁሟል።እንዲሁም ጋምቤላ 500 ዜጎች በመለየት ምዝገባ መካሄዱንና ሶማሌ ክልል 700 ዜጎችን ለማንሳት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል ተብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጎዳና ላይ ካነሳቸው ዜጎች መካከል ከ43 ሺህ ዜጎች 18 ሺህ 861 ዜጎችን በተዘጋጀ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላት አስፈላጊ አገልግሎት በመስጠት ከወረርሽኙ እንዲጠበቁ ተደርጓል ማድረጉን አመላክቷል።በማዕከላት አገልግሎት እንዳገኙ ከተደረጉት ውጭ ያሉ 23 ሺህ 832 ጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ መደረጉ የተመላከተ ሲሆን፣ ወደ ቤሰቦቻቸው ከተቀላቀሉ ዜጎች ውስጥ 16 ሺ 273 ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሺህ 721 ከአማራ ክልልና ከደቡብ ክልል መሆናቸውን የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደረጀ ታየ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢፌዲሪ ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የሥራ ቦታ ምላሽ የሚሰጥ ፕሮቶኮል (workplace response Protocol) አዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ ክትትልና ቁጥጥር እያደረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ መሰረት 336 ድርጅቶች ላይ የተለያዩ አቤቱታዎች(የሠራተኛ መቀነስ፣ ክፍያ መከልከል፣ ደመወዝ መቀነስ እና ሌሎችም) ቅሬታዎች መቅረባቸወን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ336 ድርጅቶች ላይ የቀረቡትን ቅሬታዎች በመቀበል ከድርጅቶች ጋር የስምምነት ስራ በመስራት 12 ሺህ ሠራተኞችን ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።በተጨማሪም የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ በድምሩ 22 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት (በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ሀብት) በማሰባሰብ ለተመላሾች ድጋፍ ማድረጉን ተጠቁሟል፡፡

ከዓለም ፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በተገኘ 75 ሺህ ዶላር ድጋፍ የስደት ተመላሽ የመረጃ ማዕከል (Resource Center) በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ለማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።ከዚህ በተጨማሪ ከዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) 40 ሺህ ዶላር በተገኘው ድጋፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሥራ ቦታ ለመከላከል የንጽህና መጠበቂያና መከላከያ ቁሳቁሶች ግዥ በሂደት ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚግዝ ከተለያዩ ድርጅቶች ሀብት የማሰባሰብ ስራ በመሰራት ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ17 ሺህ ነፍሰ ጡር እናቶችና የሚያጠቡ እናቶች የሚውል 20 ሚሊዮን ብረ፣ ከ በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ለወረርሽኙ እንዳይጋለጡ ለማገዝ 116 ሚሊዮን ብር፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ በድምሩ 22 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ለተመላሾች ድጋፍ እንደተደረገም ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here