ፊሽካው ተነፍቷል! “አገራዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል”

0
902

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ትናንት መስከረም 08/2013 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባት ስብሰባ ላይ በመገኘት አገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል አስታወቁ። ሚኒስትሯ ኮሮና መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ስነምግባር፣ ደንብና ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኝ ስርጭት ከተከሰተ በተለየ ሁኔታ ችግሩን ማየት ሊያስፈልገው እንደሚችል ከወዲሁ ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ምርጫው ሊካሄድ ይችላል መባሉን አስመልክቶ የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፤ ‹‹ውሳኔው እንቆቅልሽ ነው፤ ከዚህ ቀደም ወረርሽኙ አሁን የደረሰበት የስርጭት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ምርጫው ይራዘም ካሉ በኋላ አሁን በሽታው ይበልጥ በተስፋፋበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ማለታቸው ግራ የሚያጋባ ነው።›› ብለዋል።

የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አዳነ ታደሰ በበኩላቸው ውሳኔው የሚጠበቅ ነው፤ ገዢው ፓርቲ ዝግጅት ያረገበት እንደሆነ እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የአገራችን ችግር በምርጫ የሚፈታ ነው ብለን አናምንም። ምርጫው ካለፉት አምስት ምርጫዎች የተሻለ ይሆናል ብለው እንደማያምኑም አስታውቀዋል። አገሪቱን አስከፊ ውጥረት ውስጥ ሊከታት ይችላል ብለን እንሰጋለን ብለዋል።

የአብን ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ በበኩላቸው የጤና ሚኒስቴር ያቀረበውን ሪፖርት የባለሙያ ሃሳብ አድርገው እንደሚወስዱት፣ ቢሆንም ግን ምርጫ ከማሰብ በፊት መንግስት ያለስማቸው ሀሰተኛ ስም በመስጠት እና ባልሰሩት ወልጀል ወንጀለኛ ናቸሁ ብሎ ያሰራቸውን ሳይፈታ ምርጫ ማድረግ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ ቢገልፁም ምርጫው የሚደረግ ከሆነ በሚገባ እንሳተፋለን ብለዋል።

በሌላ በኩል ምርጫው መቼ እንደሚደረግ በይፋ ሳይነገር በጉዳዩ ላይ ሐሳብ መስጠት እንደማይችል ኢዜማ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here