ትጥቃቸውን የፈቱ ወታደሮችን ለማቋቋም የተደረገው እርዳታ ከመንግስት አልተለቀቀም

0
726

‹‹የኦነግ ወታደሮች በድብቅ ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው›› አበበ አካሉ

የጀርመን መንግስት በትጥቅ ትግል ውስጥ ለነበሩ ታጋዮች እና ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ የወሰኑ ወታደሮችን ለማቋቋም የሰጠው ድጋፍ አለመሰጠቱ ተገለፀ።

ከወራት በፊት የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ አምስት ለሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ይደረግ ዘንድ የለቀቀው 10 ሚሊዮን ዩሮ እንዳልተሰጣቸው እና እስከ አሁንም በመንግስት እጅ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ለወታደሮቹ ገንዘቡ ድጋፍ እንዲደረግ የተሰጠው በመንግስት ደረጃ በፌደራል አደጋ መከላከል እና ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል እንደሚሆን እንደተገለፀላቸው የተጠቆመ ሲሆን አስካሁ ግን አምስት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ከተቀረፁ በኋላ የትኛው ወደ ትግበራ ይገባ በሚለው ላይ ውይይት እየተደረገ ነው በማለት እንዳዘገዩት እንደተገለፀላቸው የኢትዮጲያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (የኢዜማ) ዋና ፀሃፊ የሆኑት አበበ አካሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አበበ እንደሚሉ በትጥቅ ትግል ውስጥ ቆይተው በኢትዮጵያ በተፈጠረው የለውጥ ሒደት በተደረገላቸው ጥሪ ወደ አገር ወስጥ የገቡት እና በአገር ውስጥ ትግል ሲያደርጉ የቆዩትን ጨምሮ አምስት ለሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ድጋፉ መታሰቡን ማለትም የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ( ኦነግ) ፣ (ደምህት) ዲሞክራሲ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ ፣የአማራ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ንቅናቄ (አዴህን) ፣ ኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም እስካሁን ባለው የዕርዳታ አሰጣጡ በተመለከተ ከፌደራል አደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ተገቢውን እርዳታ እንዲያደርግላቸው እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አበበ ። ከምግባቸው እና ከሚያርፉበት መኝታ ውጪ በየወሩ 3000 ሺህ ብር እየተደጎሙ እንደነበር እና መልሶ ማቋቋሙ እስኪሳካ ድረስ በዚሁ መልክ ነው መቆየታቸውን እየተከታተልን ያለነው ብለዋል ።

አበበ እንዳነሱት በመጀመርያው ዙር እርዳታው ( መልሶ መቋቋሙ) ይደረጋል የተባለው 3950 ለሚደርሱ ከሁሉም ትጥቅ ትግል ውስጥ ከነበሩ አባላት ዝርዝር ተወስዶ የሚደረግ መሆኑን ከአደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና ፅህፈት ቤት እንደተነገራቸው ጠቅሰው፤ በቀጣዩ ዙር ግን ምን ያህል ወታደሮች ይሳተፋሉ ሚለው እንዳልተነገራቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ነገር ግን እንደ ቅሬታ ያነሱት እና መግስት በትኩረት አይቶት ሁሉንም በትጥቅ ትግል ውስጥ ሲታገሉ የነበሩትን አባላት ወደ መልሶ ማቋቋሙ መመለስ አለበት አለበለዚያ ግን አመኔታውን ያሳጣዋል በማለት ያነሱት አበበ ‹‹ ከሌሎች ወታደሮች በተለየ የኦነግ ወታደር የነበሩ ታጋዮች በስውር ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው›› የሚሉት አበበ ይህንንም መታዘባቸውን አንስተው ነገር ግን ሌሎቹ አሁንም እርዳታ በመጠበቅ ላይ ናቸው ሲሉ ያነሳሉ።

ከዚህም ባለፈ መንግስት ለወታደሮቹ የተሰጠውን እርዳታ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲያስገባውም ኢዜማ ጠይቋል። ምክንያቱም ይህ ካልሆነ አጠቃላይ እርዳታው 25 ሚሊየን ዩሮ ሲሆን ነገር ግን የጀርመን መንግስት ቅድሚያ 10 ሚሊየን ዩሮውን ከለቀቀ በኋላ ቀጣይ አፈፃፀሙን ከተመለከተ በኋላ ነው ለመልቀቅ ፍቃደኛ የሚሆነው በማለት የሚናገሩት አበበ ይህ እንዲሆን ደግሞ መንግስት የጎላ ሚና መጫወት አለበት በማለት አሳስበዋል።

አበበ እንደሚሉረት ኢዜማ ይህንን ክትትል በኃፊነት እያደረገ ያለው ጉዳዩ በግሉ የሚመለከተው ሆኖ ሳይሆን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎችን የመከታተል ሃላፊነት አለብኝ ብሎ ስለሚያስብ እንደሆነ አንስተዋል።ይሄ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ መንግስትና መንግስትን ነው የሚመለከተው በማለት ተናግረዋል።

በተያያዘም የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ዋና ፀሃፊ የነበሩት ሃሰን አሊ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ከእርሳቸው ፓርቲ ውስጥ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ አባላት አራ ሺኅ በላይ የሚጠጉ እንደነበሩ ያነሱ ሲሆን መንግስት የመልሶ ማቋቋም ስራውን በተገቢው እየሰራ አይደለም ቃሉንም እያከበረ አይደለም በማለት ወቅሰዋል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ አደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ዘሪሁን ዘውዴ ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here