በአማራ – ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ከብር ለውጡ ወዲህ የ4 ሺህ ብር በግ እስከ 10 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው

0
773

በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከመስከረም 5/2013 ጀምሮ የአዳዲስ የብር ኖቶችን ይፋ መደረግ ተከትሎ በአንዳንድ የአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ ገንዘብን በአይነት የመቀየር እንቅስቃሴዎች እየተስዋሉ መሆኑ የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ አስታወቁ።

‹‹አንዳንድ ግለሰቦች ነባሩን ገንዘብ በርከት አድርገው ከሚገባው በላይ ይዘው ስለነበረ አዳዲሶቹ የብር ኖቶች ይፋ ሲደረጉ በነባሩ ብር ንብረቶችን በውድ ዋጋ የመግዛት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል›› የሚሉት ኃላፊው፣ አንድ በግ እስከ 10 ሺሕ እና 15 ሺሕ ብር ድረስ እገዛለው ብሎ ለማጭበርበር መሞከር እና ይህን መሰል እንቅስቃሴዎች በተለያዩ አካባቢዎች መስተዋላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ኃላፊው እንዳስታወቁት ነባሩን ገንዘብን በአይነት የመለወጥ እንቅስቃሴዎቹ እየተስተዋሉ ያሉት በወሰን አካባቢዎች ሲሆን፣ ክልሉ ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው በሰሜን ወሎ፣ ራያና ቆቦ አካባቢዎች እና በሌሎች የክልሉ ጫፍ አዋሳኝ አካባቢዎች መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ ክልል የአዳዲስ ብር ኖቶቹ ስርጭት ዘግየት ብሎ መጀመሩን የሚገልጹት ግዛቸው፣ ካሳለፍነው ሰኞ መስከረም 10/2013 ጀምሮ እንደ ክልል ከሁሉም የከተማ ባንኮች ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ስርጭቱ እንዲከናወን ይፋዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯልም ብለዋል።

ነዋሪዎች በተሳሳቱ የብር ኖቶች እንዳይጭበረበሩ የማሳወቅ እንቅስቃሴ የክልሉ ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ለማድረግ ተሞክሯል የሚሉት ኃላፊው፣ የብር ኖቶቹን በተመሳሳይ መልኩ ሠርቶ በማምጣት ደረጃ እስካሁን የተገለፀ ነገር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።

እየተሠራ የሚገኘው ግብይቱ ውስጥ የብር ኖቶቹ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ በተለይ አርሶ አደሮች አካባቢ አዲስ ብር ሲሆን ቁጥርም የማያነብ ሰው ሊኖር ስለሚችል የብር ኖቶቹን ቀለም በደንብ አውቆ ከመገበያየት አንፃር ቀለሞችን የማሳወቅ ሥራ ሊሠራ ይገባል። ስለዚህም ይሄንን ከግምት ውስጥ ያስገባ ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው በማለት አስታውቀዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን የቀጠናው በተለይ በመመሪያው መሰረት የብር ኖቶች እንዲዳረሱ ከማድረግ አኳያ ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ከግምት ውስጥ ያስገባ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ለፀጥታ አካሉ እና ለሚመለከታቸው የአመራር አካላት በሙሉ አቅጣጫ መቀመጡን ግዛቸው ገልጸው፤ በዚህም መሠረት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ አልፎ አልፎ ኻያ ሺሕም፣ ሠላሳ ሺሕም የያዘውን ሰው ለመቀየር ሲመጣ ልክ አይደለም ብሎ የመያዝ እንቅስቃሴ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ከኃላፊው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ግዛቸው ይህን በሚመለከትም ትክክል እንዳልሆነና በተቀመጠው መመሪያ መሠረት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በክልሉም አሁን ጎላ ብሎ እየተስተዋለ ያለው ችግር ሰዉ አስቀምጦት የነበረውን ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ በአይነት የመለወጥ ነው የሚሉት ግዛቸው፣ ለምሳሌም የበግና የከብት ግዢ ወደ አጎራባች ክልል እና አገራት የመውሰድ ወደ ሱዳንም ወደ ትግራይም እንዲገቡ የማድረግ ችግር እየተስተዋለ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ይህ ሁኔታ ቀላል አይደለም ያሉት ግዛቸው፣ ከፍተኛ ብር ሰብስቦ ቆይቶ በተለያየ መንገድ በአይነት ለመቀየር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ማኅበረሰቡን ለከፍተኛ ኪሳራ የሚያጋልጡ ናቸው። ነገር ግን መንግሥት በጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ስለሰጠበት እና የንብረት ዝውውሩ የተወሰነ ጊዜ እንዲገደብ ስለተደረገ በዚህ እንቅስቃሴውን እየገታነው እንገኛለን ብለዋል።

በቀጣይም መሰል ሕገወጥ የንብረት ግዢ እንቅስቃሴዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ የቁጥጥር ስምሪቱን ከፍ በማድረግ እና በመጨመር ጥብቅ ክትትል በማድረግ ምንጫቸው ምንድን ነው የሚለውን በማጣራት ይሄን ተግባር ለማስቆም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here