የብር ቅየራው በትኩረት ቢጤን መልካም ነው

0
853

የገንዘብ ቅየራው የተለያዩ ስያሜዎች እና ትርጓሜዎች እየተሰጡት የተጀመረውን ጉዳይ ከዳር እንዲደርስም በተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት አማካኝነት ዕርዳታ እየተደረገለት እና የማስፈጸም ስራም እየተሰራ ይገኛል። ከወጣበት ገንዘብ አንጻር እና ከታቀደለት አላማ አንጻርም ጉዳዩ በሚገባ እንዲተገበርም እና በአፈጻጸምም በኩል እንዲሰምር የአገር ሀብት ነው እና በግል መልካም ምኞት አለን።

ከዚህም ባለፈ ብሩ ከታሰበለት አላማ አንጻር በተለይም ደግሞ ከባንክ ውጪ እየተዘዘዋወረ የሚገኝ እና 113 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተባለለት ከባንክ ዕውቀት ውጭ ያለውን ገንዘብ ለመቆጣጠርም የተነሳው ነጥብ እጅግ የሚደገፍ እና የሚበረታታ ሀሳብ በመሆኑ እንዲሰምር እና የታሰበውን ያ113 ቢሊዮን ብር በመቆጣጠር የአገሪቷን ምጣኔ ሀብት እና ገንዘብ ዝውውርን መከታተል የሚቻልበትን ደረጃ ላይ መገኘትም እጅግ ግሩም ሀሳብ ነው። ይህ የገንዘብ ቅየራ ጠቅላይ ሚንስትሩም እንደተናገሩት አገሪቱን የምጣኔ ሃብት ስበራት ለመጠገን የሚል ሀሳብ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

ገንዘብ ከመገበያያነቱ እና በአገር ኢኮኖሚ ካለው ጉልህ ጠቀሜታ ባለፈ የባህል አምባሳደር በመሆንም በዘመናዊው ዘመን እንደሚያገለግልም ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። አገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት፣ ዕምቅ እና ስብጥር ባህል፣ አገራት ሚወከሉበት የእንስሳ አይነት እና መሰል አርማዎች በገንዘቦቻቸው ላይ ይታተማል በቀላሉም ለመለየት የሚቻልበት ጉዳይ ይኖራል።

ከሰሞኑ ታዲያ ጉዳይ ተከስቶ ነበር እርሱም ድንገተኛው የኢትዮያ መገበያያ ገንዘብ የመቀየር ጉዳይ እና አዲስ ባለ 200 ብር ኖት ወደ ገበያ መግባቱ ነው። ከኹለት አመት ከመንፈቅ አካባቢ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግስት ወደ መንበሩ በመጣበት ወቅት ከሕዝብ ዘንድ የተዘረፈው ገንዘብ ማስመለስ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ባላመሆናችን የመገበያያው ገንዘብ ተቀይሮ ዘራፊዎቹም ጉድ ይሰሩ የሚል ሙግት እና አስተያየት የተቀላቀለበት ጉዳይ ሲሰማ ነበር። በወቅቱ ታዲያ በርካታ ተደራራቢ ችግሮች እንዲሁም ታፍኖም ነበረ ሀሳብ ሲንሸራሸር ስለነበር ወደ አስፈጻሚው አካል የሚደርሰው ሀሳብ እጅግ የበዛ ነበር። ይነሱ ከነበሩት ሃሳቦች አንዱ ታዲያ ሕገ መንግስት እና መገበያያ ገንዘብ ይቀየር የሚል ነበር።

በሙስና እና በስርቆት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እና መንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በጆንያ እና በፌስታል ገንዘብ እየተቀባበሉ ግብይት የሚፈጽሙትን ሰዎች ጉዳይ ለመቆጣጠር እና እንደ ጠቅላይ መሚንስትሩ አባባል ‹‹ሌቦች ኢንቨስት ስለማያደርጉ›› ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚዘዋወር ይህን ሁሉ ለመቆጣጠር እና ኢትዮያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ስብራት የምታገገምበትን ጉዳይ እንዲፋጠን በምስጢር የተያዘው ብር ቅየራው ጉዳይ መፋጠኑን ተናግረዋል።

‹‹ኮቪድ ባያዘገየን ኖሮ እና ሕትመት ስራው ባይጓተት ኖሮ ከዚህ ቀደም ብለን መቀየር እንችል ነበር›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስጢር ገንዘብ የመቀየር ሒደቱ ከኮቪድ በፊት ማለትም ከመንፈቅ እድሜ በላይ ምናልባትም ወደ አንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ መውሰዱን አመላካች ነው። የብር ለውጡን ለማድረግ ዋናው ምክንያት ከሁለት ዓመታት ወዲህ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመለወጥ እየተሞከረ ያለውን የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከለውጡ በኋላ በተደረገ ዳሰሳ ኢኮኖሚው ከፍተኛ የሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ማዛባት እንዳለበት በመረጋገጡ ቁልቁል ሲሄድ የነበረውን ኢኮኖሚ ማስቆም ዋናው ዓላማ ነው ብለዋል፡፡

የብር ኖቶቹን መቀየር አስፈላጊነት አክለው ያስረዱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኖቶቹን መቀየር ያስፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያው ምክንያት በርካታ ገንዘብ ከባንክ ውጪ በመኖሩ ሕገወጥ ተግባራት፣ ሙስናና ኮንትሮባንድ ስለተስፋፉ ያንን ለመከላከል ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ባንኩና ውጪ ያለ ገንዘብ ሲበራከት የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ያንን ለመከላከል ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ባለ 10፣ 50፣ 100 እና አዲስ ደግሞ ባለ 200 ብር ኖትን ያካተተው አዲሱ የብር ኖት አገሪቱ ለ23 ዓመታት ከ1990 ጀምሮ የተጠቀመችባቸው ገንዘቦች እንደተቀየሩ ታውቋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይናገር ደሴ እንደሚሉት በ1996 አካባቢ የተወሰነ ማሻሻያ የተደረገበት የተወሰኑ የብር ኖቶች መኖራቸውን አውስተው ነገር ግን በዚህ ወቅት የተደረገው የብር ቅራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተደረገ እንደሆነ እና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

አሁኑን የብር ለውጥ ልዩ የሚያደርገው ከዘመኑ ጋር አብሮ የዘመነ መሆኑ እና በተለይም ደግሞ ገንዘቡ ውስጥ የተቀበሩት የመጠበቂያ እና ትክክለኛነት ማረጋገቻዎቹ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የተሰሩ መሆናቸው እና ለሐሰተኛ የብር ኖት ሕትመት እንዳይጋለጡ ሆነው መሰራታቸው አዳዲሶቹን ብሮች ዘመናዊነት በእጅጉ የሚገልጹ ናቸው። በተጓዳኝም ከዚህ በፊት ያለነበሩ እና ማየት ለማይችሉ ወገኖችም ታሳቢ ተደርገው ተሰሩ ሲሆን ይህም በተለይም ደግሞ በብሮች ዳር እና ዳር ላይ በእጅ ሲዳሰሱ የሚጎረብጡ መስመሮች እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በዚህ ጉዳይ ወቅት ታዲያ የገንዘብ ቅየራው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እተካሔደ ነው ብላ አዲስ ማለዳ አታምንም። በግል እና በመንግስት ባንኮች አዲሱ ብር ኖት መግባቱ እና አገልግሎት ላይ መዋሉ ቢነገርም ተገልጋዮች ግን ማግኘት እንዳልቻሉ እና አሮጌው ገንዘብ አሁንም ከባንክ እያወጡ መሆናቸው በተባለለት ጊዜ ገደብ እንዳይጨረስ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም መንግስት ይህን ጉዳይ በትከኩረት በማጤን አዲሱን ብር በሰው አልባ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች እና በግል እና በመንግስት ባንኮች ውስጥ በበቂ ሁኔታ በማሰራጨት ከስር ከስር ገንዘብ ቅየራውን እንዲሳለጥ ቢደረግ መልካም ነው ትላለች።

በዚህ ብቻ ሳይበቃ መንግስት ከባንክ ውጪ 113 ቢሊዮን ብር ይዘዋወራል በሚል ገንዘብ መቀየሩ እምብዛም ክፋት ባይኖረውም የባንክ እና የዘመናዊ ገንዘብ ተቋማት በማይዳረስባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ሕብረተሰብ ክፍሎች አሁንም ብራቸውን በቤታቸው የሚያስቀምጡትን ገንዘባቸውን ቀይረው የዘመናዊ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሚሆኑበትንም ጉዳይ መንግስት ሊያረጋግጥ ግዴታ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትሰነዝራለች።

የብር ቅየራው ሒደትም በተራዘመ ቁጥር የሐሰተኛ የብር ኖቶች ለመመረት ጊዜ ስለሚያገኙ አዲሱ የገንዘብ ቅየራም የታሰበለትን አላማ ሳይመታ ተጨማሪ ወጪ እንዳይወጣም አዲስ ማለዳ መንግስት ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግ ከወዲሁ ምክረ ሀሳቧን ታስቀምጣለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here