የሕክምና ባለሙያዎቹ የአበል ክፍያ መከልከላቸውን ገለጹ

0
602

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ በኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ማዕከላት በቀጥታ በህክምና ተሰማርተው ሲያገለግሉ የነበሩ የህክምና ባለሙዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው የማበረታቻ ልዩ አበል ክፍያ መከልከላቸወን ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና ህክምና አገልግሎት በመስጠት በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ዘርፍ ሰራተኞች የማበረታቻ ልዩ አበል ከፍያን ለመወሰን የወጣውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ግንቦት 18/2012 ለኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ተግባራዊ አንዲሆን ሲል በደብዳቤ እንዳሳወቀ ለማወቅ ተችሏል። መመሪያው ተግባራዊ አንዲሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢወስንም ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁ ባለሙያዎች ግን ለሰባት ወራት በኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ህሙማንን የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ ቢቆዩም ልዩ ጥቅማጥቅምና አበል አንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል።

ለ ሰባት ወራት በአዲስ አበባ በሚገኝ የኮቪድ-19 ማቆያ ማዕከል ሲያገለግሉ የነበሩ ስማቸው አንዳይጠቀስ የፈለጉ ቅሬታ አቅራቢ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በሚያገለግሉበት የለይቶ ማቆያ ማዕከል የአምስት ወር የትርፍ ሥዓት ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያጋጠማቸወን ሁኔታ ባለሙያው ሲገልጹ “ህዝብ ለማዳን ብለን ህይወታችንን ገብረን ትንሽ እስር ቤት በሚባል ሁኔታ ለሰባት ወር ያክል ከቤተሰብ ተነጥለን ቆይተን የሙያ እና የሥራ ሞራላችንን ገድለውታል” ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚሉት መንግስት የካደን በመመሪያ ያጸደቀውን የልዩ አበል ከፍያ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በየካቲት 12 ሆስፒታል ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሲገለግሉ የነበሩ የጤና ባለሙያ የሆኑት ከድር ሳሊም ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ለህክምና ባለሙያዎች የሆናችሁ ቤት ይሰጣችኋል ተብለን አሁን ላይ የሚሰጥ ቤት የለም ተብለናል ብለዋል።

የጤና ባለሙያው እንደሚሉት መንግስት ለህክምና ባለሙዎች ቤት አንደምሰጥ በወቅቱ ገለጾ የህክምና ባለሙያዎች ከወረዳ ወይም ከቀበሌ ማስረጃ አምጡ ተብለን በአጭር ጉዜ ውስጥ ተሯሩጠን ማስረጃ እንድናቀርብ ከተደረግን ብኋላ መንግስት ቤት እንዳማይሰጥ እንዳሳወቃቸው ጠቁመዋል።

የህክምና ባለሙየዎቹ ቅሬታቸውን ይዘው ለጤና ሚኒስቴርና ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ቢያሳውቁም “ ቤት እንዲሰጣችሁ ማስረጃ አቅርቡ ያልናችሁ ቤት ለመስጠት ሳይሆን ምን ያክል የህክምና ባለሙያዎች ቤት እንደሌላቸው ለማወቅ ነው።” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል።

የባለሙያዎቹ ሌላኛው ጥያቄ በኮቪድ-19 ህክምና ላይ ተሰማርተው ህይወታቸወን ላጡ የህክምና ባለሙያዎች የጤና መድን ለቤተሰቦቻቸው እንዲሰጥ የሚል ነው። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል በማገልገል ላይ እያሉ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የጤና መድን ዋስትና መሰጠት አለበት ብለዋል።

አዲስ ማለዳ የህክምና ባለሙያዎቹን ቅሬታ ይዛ ለኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ለዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ምላሽ ብትጠይቅም ዶ/ር ተገኔ ጥያቄውን ከዳመጡ ብኋላ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በኹለተኛ ደረጃ አዲስ ማለዳ ጥያቄዋን ያቀረበችው ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ለዶ/ር ዮሀንስ ሞላ ቢሆንም በተደጋጋሚ ለኹለት ቀናት ስልክ ቢደወልላቸውም ስልካቸውን አንስተው ምላሽ ለመስጠት አልቻሉም።

የሚኒስትሮች ምክረ ቤት ግንቦት 14/2012 ባጸደቀው በኮቪድ-19 ህክመና ላይ በቀጥታ ለሚሳተፉ ባለሙዎች የእለት ክፍያ በየደረጃው መወሰኑ የሚታወስ ነው። በዚሁመ መሰረት በአንድ ቀን ከፍተኛው ተከፋይ 1150 ብር ዝቅተኛ ተከፋይ 300 ብር እንዲከፈላቸው በመመሪያው ላይ ተደንግጓል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here