«በባንዲራ!! በባንዲራ!! በባንዲራችን!! በሕግ ቁም ብዬሃለሁ!!» ትለዋለች፤ እየተከተለች አዲስ አበባ ውስጥ፣ ወደ ቀጨኔ መድኃኔዓለም በሚወስደው መንገድ፣ ድልድዩ አጠገብ፣ ከአባ ሀብቴ ቤት አጠገብ ነው ሴትየዋ ጠላ ሻጭ ናት ሰውዬው እግረ መንገዱን ሲያልፍ ጠላ ሊጠጣ ይገባና ሳይከፍል ይወጣል እሷ እንዳለችው ኹለት «ምኒልክ» ነው የጠጣው(«ምኒልክ» የጠላ መጠጫ ዋንጫ ነው) እሱ ደግሞ «የለም አንድ ብቻ ነው» ይላል። የጎረቤት ሰው ጠርቷት ወጣ ብላ ተነጋግራ እስክትመጣ ድረስ ሰውዬው ከእንስራው ውስጥ ቀድቶ ኹለተኛውን «ምኒልክ» እሷ ሳታየው ጠጥቷል፤ እሷ ግን ኹለተኛ መጠጣቱን ደርሳበታለች።ሲወጣ የአንድ ምኒልክ ሒሳብ ከፍሎ ይወጣል ፣ ሰውነቱ ዘለግ ያለ ጎረምሳ ነበር። ሴትዮዋ ደግሞ ቀጭን፣ ኮሳሳ ድሀ ነች ጥንካሬዋ ግን ባንዲራ ነበር።
«በባንዲራ!! ወድቃ በተነሳችው!!» ብላ በጮኸች ቁጥር ኩራት እና ጥንካሬ ይሰማታል በሌላ በኩል እየተከተለች «በባንዲራ!» ባለችው ቁጥር ሰውዬው እያነሰ፣ እየኮሰሰ ሄደ።መንገደኛው ሁሉ «ምንድነው ይህ ሰውዬ፣ በባንዲራ ሲባል አይሰማህም እንዴ?» እያለ ሰውየውን ትኩር ብሎ ያየው ጀመር።ሰውዬው ግራ ገባው «ይህች ኮሳሳ ደሃ እንዲህ ታዋርደኝ?» ይላል በልቡ የወንድነት ወኔው፣የጎረምሳ ኩራት እያሸነፈው ለመቆም በጣም አመነታ ዝም ብሎ ቢሄድ የሚያስከትለውን ነገር ባለማወቁ መሀል መንገድ ላይ ቀጥ ብሎ ቆሞ ከኪሱ ስሙኒ ፈልጐ ወረወረላትና መንገዱን ቀጠለ ፤ባንዲራዋ አሸነፈች።
ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲነሳ፣ ሲወሳ ከተመዘገቡት ትዝታዎችና ገጠመኞች አንዱ ነው፡ ከላይ የተጠቀሰው ገጠመኝ በመስከረም 1999 በአሜሪካ ከታተመው የሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ‹‹ክህደት በደም መሬት›› መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሯል።
በንጉሱ ዘመን አንድ ሰው መብት ሲጥስ ወይም ያልሆነ ነገር ሲያደርግ ወድቃ በተነሳችው ባንዲራ (በባንዲራዋ) ከተባለ ቀጥ ብሎ ይቆማል ማጥፋቱንም ያቆማል ሲሉ አሰፋ ገ/ማርያም የሚባሉ እድሜ ባለ ፀጋ ለአዲስ ማለዳ ዘጋቢ አጫውተዋታል።
የሰንደቅ ዓላማ ሌላው ስሙ ከጣሊያንኛ የተወሰደው ባንዲራ ነው። ሰንደቅ ዓላማ ወይም የአገር ባንዲራ የ አገር ትልቅ ክብር የነበረው እና ያለው ባለ ትልቅ ግርማ ሞገስ በአንድ ሉአላዊ አገር የሚኖሩ ሰዎች ምልክት ነው።
ሰንደቅ ዓላማችን በንጉሳዊው ዘመነ መንግሥት ትልቅ ክብር እንደነበረው እና የበአል ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ከትምህርት ቤቶች እና ከትልልቅ ተቋማት ውጪ ተሰቅሎ የማይታይ ውድ ንብረት እንደነበረ እንሰማለን።
በመስሪያ ቤቶች እና በትምህርት ቤቶች የሚሰቀሉት ሰንደቅ ዓላማዎች የሚሰቀሉበት እና የሚወርዱበት ሰዓት ተመድቦላቸው በሚሰቀሉበትም ሆነ በሚወርዱ ሰዓት ሁሉም ሰው በታላቅ ሥነ ስርዓት ይቆም ነበር ።የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስርዓት በሚሰቀሉበት ሰአት መኪና የሚያሽከረክር ሰው እንኳን ቢኖር ከመኪናው ወርዶ ለባንዲራው ያለውን ክብር ይገልፅ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያነሳሉ።
ተፈሪ አለሙ በአንድ ወቅት ስለ ባንዲራ እንዲህ ብሎ ነበር።በደርግ ዘመን የባንዲራ ፍቅር በኃይል ዘልቆንም ይሆን? በየመጠጥ ቤቱ ደጃፍ፣ በየመደብር ቤቶች በየከሰል መሸጫው በየ ጫት ቤቶች ሳይቀር ይሰቀል ነበር።
ከዚያ በኋላ የልብስ ጥለት፣ የኮፍያ፣ የቁሳቁስ እጄታ ፣ማጌጫ ፣የጋዜጣ እና መፅሄት ማሻሻጫ ፣የመንገድ ዳር ዛፎችና የስልክ እንጨቶችም ላይ ሳይቀር አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ይቀቡ ጀመር አንዳንዴም ባንዲራን በመንገድ ላይ ያሉ ዛፎች ላይ ማልበስ ይስተዋላል።
ዛሬ ለባንዲራ የነበረው ያ ሁሉ ክብር ያለ አይመስልም በየ ቀበሌው እና ስብሰባ ባለበት የስብሰባ ማጀቢያ ይመስል በየ ጠረጴዛው ላይ ተሸርጦ በየቦታው እንደ ተራ ነገር ተይዞ የሚዞር ሆኗል ይባስ ብሎ አሁን አሁን መነታረኪያ እና መደባደቢያችን እየሆነ የአንድነታችን ምልክት መሆኑ ቀርቶ የልዩነታችን ምክንያት እየሆነ ይመስላል ይላል ተፈሪ።
በ1898 «የኢትዮጵያ ትእምርተ መንግሥት» በሚል ርእስ ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚናገር በሚለው ምዕራፍ በገጽ 18 ላይ እንደሚከተለው ጽፈዋል።
ሰንደቅ ዓላማ ማለት የንጉሥና የሕዝብ ምልክት ነው የዓለም ነገሥታትና ሕዝብ እጅግ ብዙ ናቸው ስለዚህ የወዴት አገር ንጉሥ ነው? ይህ የወዴት አገር ሕዝብ ነው እንዳይባል ልዩ ልዩ ሰንደቅ ዓላማ ያስይዛሉ፤ በበዓል ቀንም በየደጃቸው ይሰቅላሉ።ይህንንም ያየ ሰው ሁሉ የእገሌ አገር ንጉሥ ነው። ይህ የእገሌ አገር ሕዝብ ነው ብሎ በሰንደቅ ዓላማው ያውቀዋል ሰንደቅ ዓላማውም እጅግ ይከበር ነበር። ሲሰቀል እና ሲወርድም በዜማና አና በሰላምታ ነው። ሰንደቅ ዓላማውን ያየ ሰው ሁሉ ቆቡን ወይም ባርኔጣውን ያወርዳል። አለቆችም ሰይፍ ይመዛሉ በሰልፍ እና በጦርነት በጸሎት እና በፍሥሐ ቀንም ያለ ሰንደቅ ዓላማ አይሆንም ።የክብር ሁሉ መሠረት ነውና።
በጦርነት ጊዜም ንጉሡ ራሱ ሰንደቅ ዓላማውን በእጁ ይዞ ለጦር አበጋዙ አደራ ይሰጠዋል፣ እንዲህ ሲል በርታ አደራህን ሰንደቅ ዓላማችን በጠላት እጅ እንዳይገባ እኛና ሕዝባችን እንዳንዋረድክብራችን እንዳይጠፋ የጠላት መሳለቂያ እንዳንሆን አደራህን ይለዋል።
በፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የሰንደቅ አዋጅ ላይ እንደተገለጸው አረንጓዴው የሥራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት ነው ዓላማ ቢጫው ደግሞ የተስፋ፣የፍትሕና የእኩልነት ምልክት ሲሆን ቀዩ ለነጻነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋዕትነትና የጀግንነት ምልክት ።
በቀድሞጊዜ የዚሁ ሰንደቅ ዓላማ ኅብረ ቀለማት ምሳሌያቸው አረንጓዴው ተስፋ ልምላሜና ሀብት፤ ቢጫው ሃይማኖት አበባና ፍሬ፣ቀዩ ፍቅር ፣መሥዋዕትነት እና ጀግንነት ነበር።
በሰንደቅ ዓላማው ላይ በአገሪቱ በተከሰቱ መንግሥታት ባሕርይ ዓርማ ሲጠለፍበት ኖሯል። በዘውዳዊው ሥርዓት የአንበሳ ምልክት፣ በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥታት የየራሳቸው ዓርማዎች ነበሯቸውየአሁኑ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዓርማ ባለ አምስት ኮከብ ሰማያዊ ቀለም ከዓላማው ጋር ተቀናጅቶ አካሉ ሆኗል።
በቀደመው ጊዜ ከሰንደቅ ዓላማ ክብር ጋር አብሮ ተያይዞ የሚገኘው የሕዝብ መዝሙር (ብሔራዊ መዝሙር) እና የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ነው። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ መዝሙር ያገኘችው በ20ኛው ምዕተ ዓመት ሲሆን በሦስት ሥርዓቶች ሦስት የተለያዩ መዝሙሮችን አስተናግዳለች።
የመጀመሪያው መዝሙር በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923¬-1967)የሚል መንደርደርያ ያለውና በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ግጥም ደራሲነት፣በነርሲስ ናልባንዲያን ዜማ አቀናባሪነት የተዘጋጀ ነበር።
በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ሰንደቅ ዓላማው የአከባበር ሥርዓት ነበረው። በመንግሥት ተቋማት በወታደራዊ ክፍሎች እና በትምህርት ቤቶች የመስቀልና የማውረድ ሥርዓቱ ከሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ጋር የተጣመረ ነበር። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ የክብር ሰላምታውን የደረሱት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ሲሆኑ ዜማውን ያወጡት አቶ እሸቴ መኰንን ናቸው። ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣ (ሲሰቀል) «ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ›› የሚለው፣ ሲወርድ ደግሞ «ተጣማጅ አርበኛ›› ይዘመር ነበር።
የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ከዘውዳዊው ሥርዓት በኋላ አልቀጠለም የኹለተኛው ብሔራዊ መዝሙር ደራሲ አሰፋ ገብረማርያም ለሰንደቅ ዓላማው ማውጪያና ማውረጃ ግጥም ቢደርሱም ሶሻሊስት አገሮች የባንዲራ መዝሙር የላቸውም በሚል ፈሊጥ ሥርዓት ሳይበጅለት እንደቀረ ይወሳል።
ሁለተኛው መዝሙር ሆኖ የመጣው ‹‹ኢትዮጵያ ቅደሚ›› የሚለው ሲሆን በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ (1967-1979) ቀጥሎም በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (1980-1983) በአገልግሎት ላይ ውሏል።
ብሔራዊ መዝሙር በአሰፋ ገብረማርያም ተሰማ ደራሲነት፣ በዳንኤል ዮሐንስ ዜማ ቀማሪነት አዲስ መዝሙር ቀርቦ እስከ 1983 ቆይቷል።
በ1984 ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ አዲሱን ሥርዓት የሚያንፀባርቅ አዲስ የሕዝብ መዝሙር በደረጀ መላኩ ገጣሚነት፣ በሰሎሞን ሉሉ ዜማ ደራሲነት የወጣው «የዜግነት ክብር›› የተኘው መዝሙር ነው።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጥንታዊ፣ ዘመን ተሻጋሪና የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ካላቸው አገሮች ጋር የሚመደብ ነው ። ማዕከላዊ መንግሥት ከመመሥረቱ በፊትና ከተመሠረተም በኋላ በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋለ እስከአሁን ዘልቋል።
የተረሳውን የሰንደቅ ዓላማ ክብርን የአገር ፍቅርን ከማነቃቃት አኳያ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት ሁሉም ሠራተኛ በተሰበሰበበት የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስረዓት ማክናወኑ ለማወቅ ተችሏል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን የሰጡት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደገና ደሳለኝ እንደተናገሩት የሰንደቅ ዓላማ ክብረ በዓል አንደተረሳ እና ለዚህም እንደ ባህልና ቱሪዝም ይህን የሰንደቅ ዓላማ አከባበር እንደ ባህል ለማስቀጠል ታስቦ እንደተጀመረና ይህንንም ለማስቀጠል ባህልና ቱሪዝም ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው ብለዋል።
በአብዛኛው አገራችን ላይ ያሉ ተቋማት የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስርዓት አከባበር እንደሌላቸው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሲያወርዱትና ሲሰቅሉት ይስተዋለላል አንዳንዴም ሳይወርድ እዛው ላይ እያለ ሰንደቅ ዓለማው ሲቆሽሽ ሲበጣጠስ ይስተዋላል ብለዋል።
ባለፉት ዘመናት የነበረ የሰንደቅ ዓላማ ክብር አሁን ካለው ጋር በጣም ልዩነት አለው ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ያለው ክብር እየቀነሰ መምጣቱ የሚታይ እውነት ነው። የነበረው የአገር ፍቅር ስሜት የተለየ ነበር በአሁኑ ጊዜ ግን ለሰንደቅ ዓላማ ክብር የሚሰጥ ትውልድ ለማግኘት የማይቻል በሚመስል ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ትርጉም የማያውቅ ትውልድ እንዳለ ይስተዋላለል ብለዋል።
እንደ አለፈው ዘመን ለሰንደቅ ዓላማዬ እሞታለሁ የሚል ሰው ጠፍቶ የመከፋፈል ስሜትን የሚፈጠር ይህ ባንዲራ እኔን አይወክሉም የሚሉ ድምፆችም ሲበራከቱ ይስተዋላላል።
ሰንደቅ ዓላማ መከበር ያለበት ብዙ መስዋትነት የተከፈለበት ሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው የአገር መገለጫ የአገር መለያ ነው። የአከባበር ሥነ ስርዓቱም ምን መምሰል እንዳለበት በተለያዩ ተዛማጅ በሆኑ በሕገ መንግሥቱ በተቀዱ ሕጎች ላይ ተቀምጧል። ነገር ግን ሕጉ በሚያዘው መልኩ ሲተገበር አይስተዋልም።
የተረሳውን የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስረዓት ከፍ ለማድረግ የአገር ፍቅርንም ከመቀስቀስ አንፃር ሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስርዓትን ማክበር የአገር ፍቅርን ከመመለስ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረው ይህንንም ለማስቀጠል ዘለቄታ እንዲኖረው አድርገው ለመሥራት እንደታሰበም እነደገና አስረድተዋል።
እየጠፋ የሚመስለውን የሀገር ፍቅር ለመመለስ ሰንደቅ ዓላማ ሥነ ስርዓትን ማክበር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ምክንያቱም ሰንደቅ ዓላማ በውጪ አገራት ላይ በኦሎምፒክ ሲውለበለብ ኢትዮጵያውያን የሚሰማን ደስታ የአንድነት ስሜት እጅግ ከፍ ያለ ነው። ይህ አንድ እንድንሆን ሰንደቅ አለማችንን አብረን ማስከበር ይገባናል ብለዋል።
ስለ ሰንደቅ ዓላማ ሁሉም ይመለከተዋል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ይህን ዘለቄታ እንዲኖረው ሁሉም የኢትዮጵያ ነዋሪ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፣ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያን የመበታተን አገርን የመጥላትን ስሜት ያጠፋል ለዚህም ሚዲያው ሊረዳን ይገባል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገራቻችው የኢትዮጵያ እስካውት ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚሽነር ብሩክ መሰለ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ የአንድ አገር ባህል ታሪክ ቅርሶቻቸውን የሚገልፁበት የአንድ አገር መለያ አርማ ነው።
እንደ እስካውት ሰንደቅ ዓላማውን የሚወድ ትውልድ ለማፍራት በትጋት እየሰሩ እንዳሉ ጠቅሰው ለአብነትም ምንም አይነት ፕሮግራም ከመጀመራችን በፊት በማንኛውም ጊዜ ሰንደቅ ዓላማ እንደሚሰቀል ስንጨርስም እንደዛው በክብር ሰንድቅ ዓላማችንን እናወርዳለን ይህ ነገር እስካውት ላይ ባህል ነው ሲሉ ብሩክ ተናግረዋል፡፤
ስለዚህ ይህ ባህል በሌሎች ተቋማትም መኖሩ ለአገር ክብር ፍቅር ያለው ዜጋ እንዲፈጠር አስተፅኦ አለው ብለዋል።
ይህ በኢትዮጵያ ባህልና ሚኒስቴር የተጀመረው ሥራ ዘላቂነት ሊኖረው እንደሚገባና በዘላቂነት ከተሠራበት የአገር ፍቅር ስሜትን ያነሳሳል ነገር ግን ይህ ውጤታማ እንዲሆንና ጥሩ አሠራር እንዲኖር ከተፈለገ ወጣቶች ታዳጊዎች እና ህፃናት ላይ በይበልጥ መሠራት እንደሚያስፈልግ በዚህም የሚመለከተው አካል ሁሉ በትብብር ሊሠራ ይገባዋል ከፍተኛ ሥራም ይፈልጋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በዚህም ላይ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሥራ መስራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው አገርን ለመሥራት ትውልድ ላይ መሥራት ነው የሚያስፈልገው ምክንያቱም ዛሬ ላይ የሠራነው ትውልድ ነው ነገ የአገር መሪም አጥፊም የሚሆነው በማለት ያላቸውን ሐሳብ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



