በሰሜን ዕዝ ላይ አስቃቂ እና አሳዛኝ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ከሕወሓት ጋር ወደ ሕግ ማስከበር የገባው የፌደራል መንግሥት በርካታ አውደ ውጊያዎች ላይአመርቂ ድሎችን ማስመዝገቡን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲገልጽ ሰንብቷል። በዚህም ታዲያ የትግራይ ክልል ዋና ዋና ከተሞችን በዋናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ይህ ጽሑፍ በተጠናቀረበት ወቅትም የኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐብይ አሕመድ የሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍን አስጀምረዋል። ይህ ምዕራፍም የትግራይን ክልል መዲና መቐለን በቁጥጥር ስር በማዋል አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ የመጨረሻው ዕቅድ ነው። ታዲያ ባለፉት የሕግ ማስከበር ቀናት ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገራት ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ምን አሉ? በሚል አዲስ ማለዳ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ዜና አውታሮች በመዳሰስ ለጋዜጣ እንዲመጥን በማድረግ እንደሚከተለው አቅርባለች። የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች እና የአገር መሪዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይም ከፍተኛ የሆነ አስተያየት እና ምከረ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተነሰሳውን ብዥታንም ለማጥራት ሞክረዋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሕወሓት አመራር በሞራል ልዕልና ዕኩል አይደሉም”
የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ፎሪን ፖሊሲ በተባለ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከታተመው ጽሑፋቸው የተወሰደ።
በዚህ ሰፋ ባለው ጽሑፋቸው ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሕወሓት አመራሮች ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ለማሳመን እና ስልጣንን በማጋራት ውስጥ ያሳለፉትን የወንጀል ተግባራት በመነሳት እንዳይከሰሱ ለማድረግ የሚሞክሩት ሙከራ መሆኑን ያስቀምጣሉ። ‹‹በርካታ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ሰፊ ትንተና በመስጠት የሚታወቁ እና በቀጠናው ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት አላቸው የሚባሉ ግለሰቦች በሰሞኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ብሔራዊ ውይይት መደረግ ይኖርታል በሚል ተጠምደዋል›› ይላሉ ኃይለማሪያም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባስነበቡት ጽሑፍ።
ራሳቸው ተሳታፊ የሆኑበትን የደቡብ ሱዳን ስምምነትን እንደ ምሳሌ ያነሱት አቶ ኃይለማርያም፣ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት አፈንግጦ በወጣው ኃይል እና በአገሪቱ መንግሥት መካከል የተደረገው ድርድር በሥልጣን መጋራት እንዳበቃ፣ በዚህ መሃል ግን በግጭቱ ወቅት የተፈፀመው ጅምላ ጭፍጨፋ እንደተረሳ አንስተዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በደቡብ ሱዳን ላይ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ የተከተለው መንገድ ትልቁ ችግርም መንግሥታት ከአፈንጋጭ ኃይሎች ጋር እኩል ደረጃ ላይ እንዳሉ አድርገው እንዲቀበሉ ማድረጋቸው ነው ሲሉም አስምረውበታል።
በእንደዚህ ዓይነት መንገድ የሚፈፀሙ ድርድሮች ግን መጨረሻቸው ድርድሮቹ በተፈረሙ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈርሱ መሆናቸውን ነው ያወሱት።
የሕወሓት አመራሮች አሁን ላይ እየተማመኑበት ያሉትም ይህንኑ የተለመደ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የችግር አፈታት ሥልትን መጠቀም እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም ተነሳስተው ከፌዴራል መንግሥት ጋር ግጭት በመፍጠር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብቶ እንዲያደራድራቸው ለማድረግ እና በሥልጣን ዘመናቸው የሠሩት ጥፋት ተድበስብሶ እንዲያልፍላቸው ለማድረግ ሞክረዋል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ድርድር የሚባለው ጉዳይ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የማይሆን መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በአስቸኳይ መፈፀም እንዳለበት ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል። ሕግ የማስከበሩ እርምጃ የትግራይ ክልል ሕዝብ በማይጎዳበት መልኩ ተጠናቅቆ የሕወሓት አመራሮችን ለሕግ ማቅረብ ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነም ገልጸዋል።
‹‹እኔ በሕወሓት ዘመን የነበረውን የስልጣን ጊዜየን በፍቃዴ የለቀኩት በስፋት እየተስተጋባ የመጣውን የሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ነው። በዚህም ደግሞ የምጣኔ ሀብታዊ እና የፖለቲካዊ መልካም አስተዳደር አለመኖር ዋነኛው ምክንያት ነበር›› ሲሉ ኃይለማሪያም የመጨረሻ የሥልጣን ዘመናቸውን ጊዜያት በጽሑፋቸው አስነብበዋል። የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን መጠቀሚያ ለማድረግ እና ማኅበረሰቡን እንዴት መያዝ እንዳለባቸውም ያውቃሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ድርድር እና ውይይት የሚባለው ጉዳይም ሕወሓት በሦስት ጉዳዮች ላይ ሀሳብ የጣለባቸው መሆኑንም የሚናገሩት ኃይለማሪያም ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከአንገት በላይ የሆነ ውይይት እንዲኖር በማድረግ እና አጥፊው ሕወሓት ከፌደራል መንግስቱ ጋር ስልጣን ተጋርቶ የመኖር ሀሳብን ከወዲሁ ወጥኖ ነው ይላሉ።
በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ የሕወሓት ጉልበት የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንደሚቋቋም ወይም ደግሞ እንደሚደመመስስ በሙሑር ነን ባዮች ሲተነተን የሚኖራቸው የኃይል ሚዛን ወደ እነርሱ መድፋት እምነት ነው። ይህ ደግሞ ሕወሓትን አግዝፎ ቀሪውን የኢትዮጵያዊያንን የሚንኳስስ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ለጦርነት አዲስ አለመሆናቸው እና የቆየ ልምድም ያላቸው መሆኑ ነው ሲሉም ኃይለማሪያም ሐሳባቸውን ያሰፍራሉ።
በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጡት ደግሞ በሕወሓት ውሰጥ የሚታየው ድርቅና እና ግትርነት ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመር ላይ እና በሰራዊቱ ውስጥ ተፈጠረው መከፋፈል ነው። ይህ ደግሞ ከፌደራል መንግሥት ጋር በሚኖራቸው የጦር መማዘዝ ላይ ጫና እንደሚኖረው እና ድል እንደሚቀዳጁ ተስፋ ሳይሰጣቸው እንዳልቀረ ኃይለማሪያም በጽሑፋቸው ለመዳሰስ ሞክረዋል።
“ዐብይ አሕመድ ኢትዮጵያን ሊበታትኑ የሚፈልጉትን መቅጣት ይኖርበታል”
የጅቡቲ ፕሬዘዳንት እስማኤል ዑመር ጌሌ
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የጎረቤት አገራት መሪዎች መካከል የጅቡቲው ፕሬዘዳንት እስማኤል ዑመርጌሌ ቀዳሚው ናቸው። ‹‹ኢትዮጵያ ኹለተኛዋ ቤቴ ናት›› ሲሉ በተደጋጋሚ ሚደመጡት ዑመርጌሌ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አንድ መልዕክት ማስተላለፋቸው አፍሪካ ሪፖርት አስነብቧል።
ዑመርጊሌ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በሕወሓት ላይ ጦር ማዝመቱን እና ጦርነት መፍትሔ ይሆናል ወይ ተብለው ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። በዚህም ወቅታ ታዲያ ምላሻቸውን ሲሰጡ ‹‹እስኪ ሁላችንም በዐብይ አሕመድ ጫማ ላይ ራሳችንን ከተን እንመልከት›› ሲሉ ይጀምራሉ። አያይዘውም ኢትዮጵያ ከባድ ችግር እንደተጋረጠባት እና ሕወሓት የሚባለው ፖለቲካ ድርጅት ስልጣኑ ቢገፈፍም የፌደራል መንግስቱን ለማንበርከክ ግን ራሱን እንደ አዲስ ማደራጀቱን ጠቅሰዋል። ዑመር ጊሌ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኹለት ምርጫዎች እንዳሉት ያስቀምጣሉ። በዚህም መሰረት አንደኛው ከሕወሓት ጋር ዕኩል ዕውቅና ሰጥቶ መደራደር ነው ይህ ደግሞ በየቦታው ያሉ ቡድኖች ተመሳሳይ የመገንጠል እና የራስ ገዝነት እና እምቢባይነት ሀሳባቸውን ሊያንጸባርቁ ይችላሉ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ወደ መከፋፈል እና መሰነጣጠቅ የሚመራት መንገድ ነው ብለው ያምናሉ።
በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ እንደ ፌደራል መንግሥትነት ሕግ እና ስርዓትን በማስከበር እና በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ለለመከፋፈል ሚፈልጉ አካላትን መቅጣት እንደሆነ ፕሬዘዳንት እስማኤል ይናገራሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ታዲያ እስማኤል በአሁኑ ሰዓት ዐብይ አሕመድ ኹለተኛውን መንገድ እየተከተለም ይመስለኛል ሲሉ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ተናግረዋል። ይህም ደግሞ ሕዝቡ የራሱን መሪ እንዲመርጥ የሚያደርግ ከማድረጉም ባለፈ የክልሉን ምክር ቤት መበተኑንም አስቀምጠዋል። ዑመር ጌሌ ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር የምትጋራ አገር መሪ እንደመሆናቸው መጠን በጎረቤታቸው በኢትዮጵያ ያለው ሰላም ዕጦት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገራቸው ጅቡቲን ስለሚጎዳት ሰላም በኢትዮጵያ እንዲኖር ፍላጎታቸው መሆኑንም አስቀምጠዋል። ከመንግሥቱ ኃይለማሪያም ወዲህ በተለይም ደግሞ በመነለስ ዜናዊ ዘመን አብሮነት የሚባል ነገር ሳይሆን አገዛዝ ነው የነበረው በዚህም ረገድ አንዱ ወገን በሌላው ላይ በላይ ሲሆን ነው የኖረው የሚሉት ዑመርጌሌ፤ ‹‹ዐብይ አሕመድ ቅን ከመጀመሪያውም ቅን አሳቢ እና ከመጀመሪያው ጀምሮ ከዚህ በፊት የነበረውን ትክክል ያልሆነ ጉዳይ ለማሻሻል የሚተጋ እና ጥብቅ የወንጌላዊያን አማኝ ክርስቲያንም ነው ›› ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ከሕወሓት ወገን ከባድ የሆነ ተቃውሞ ሲደርስበት እንደነበርም ኡመርጌሌ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ተናግረዋል።
“ሕግ የማስከበር ዘመቻው የተራዘመው ለንፁሃን ዜጎች ቅድሚያ በመስጠታችን ነው”
ማሞ ምህረቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ
በጠቅላይ ሚንስትሩ ዘንድ ካሉ ከፍተኛ አማካሪዎች ዘንድ አንዱ የሆኑት ማሞ ምህረቱ የፌደራሉ መንግሥት እየወሰደ ባለው ሕግን የማስከበር እርምጃ በኩል ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቀጣዩን ንግግር አድርገዋል። ማሞ ምህረቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹‹በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፤ በማንነታቸው ብቻ ለእስር ተዳርገዋል እየተባለ ነው። አንዳንዶቹም ያሉበት አይታወቅም። ከዚህም በተጨማሪ በማንነታቸው ቤቶቻቸው እንደተፈተሹ፤ እንዲሁም በብሔራቸው እየተነጠሉ እየተጠቁ እንደሆኑ ሪፖርቶች እየወጡ ነው። ይህ አንድ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም የምትሉ ከሆነ፤ እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበረ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ምላሽ ሲሰጡ ፤
‹‹ይህ መንግሥት መቼም ቢሆን በብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን አይሰነዝርም። በብሔር አይነጥልም። በጣም የሚገርም ነው። ህወሓት ነው ብሔርን መሰረት ያደረገ ሥርዓት የፈጠረው። መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር ማኅበረሰቡ እኩል በሆነ መንገድ የሚተሳሰርበትን ራዕይን የመፍጠር ሥራ ነው እየሰራ ያለው። በምንም መንገድ ቢሆን መንግሥት ዜጎችን ትግራዋይ በመሆናቸው ኢላማ አያደርግም›› ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥደለውም ማሞ ‹‹የትኛውም የሕግ ማስከበር እየሰራን ያለነው መረጃን በተመረኮዘ መልኩ ነው፤ ግለሰቦቹ ያላቸውንም ግንኙነትም በማየት የተጠና ነው። ግን ያው ግጭት እንደመሆኑ መጠን ወንጀል ተፈፅሞ ሊሆን ይችላል የሚሉ መረጃዎች ሊወጡ ይችላሉ። ሕዝቡ የተጠራጠሯቸውን ወንጀሎች ሊያሳውቅ ይችላል። በዚህ አጋጣሚ የፀጥታ ኃይሎች ተጨማሪ እርምጃዎችን ይወስዳሉ። እነዚህን እርምጃዎችንም በምንወስድበት ወቅት በተገቢውና በተጠና መልኩ ለማድረግ እንሞክራለን።
ህወሓት ብሔርን መሰረት ያደረገ ፓርቲ ከመሆኑ አንፃር በርካታ አባላቶቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ከውጭ ሲታይ መንግሥት አንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ ወይም ኢላማ ያደረገ ይመስላል። ነገር ግን ከፀጥታ ኃይሉ አባላት መካከል ክፍተት ካለ ማስተካከያዎችን እንወስዳለን። ከሕዝቡ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን እያደረግን ነው። ሕዝቡ ቅሬታውን የሚያሰማበትን ማዕከላት እያቋቋምን ነው። ቅሬታዎችን ስንሰማም ማስተካከያዎችን እናደርጋለን።
ኢ-መደበኛ በሆኑ መልኩ የሚገኙ መረጃዎችንም የማጣራት ሥራም እንሰራለን። ችግሮች ካሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንወስዳለን። ነገር ግን በእርግጠኝነት የምናገረው መንግሥት በተቀናጀ መልኩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ እርምጃዎችን አይወስድም። ይህ ዘመቻ በተወሰኑ የህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ ነው እንጂ በሕዝቡ ላይ አይደለም። ሲሉም ማሞ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። በደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አሸማጋዮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩ የተሰማውን ወሬ እና ይህንንም የኢትዮጰያ መንግሥት ድርድሩ እንደሌለ ገልጿል በሚልም ለቀረበላቸው ጥያቄ ማሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ሰዎች በግንባር ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር ለመገናኘት እና ስለአለው ወቅታዊ ጉዳይም መግለጫ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸው ‹‹ነገር ግን ለአህጉራዊ ድርጅታችን እንዲሁም ለሊቀ መንበሩ ካለን ክብር አንፃር ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ልዑካኑን በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ እናስረዳቸዋለን፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርድሩን አይቀበሉትም›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
“ባለፉት ኹለት እና ኹለት ተኩል ዓታት ሕወሓት ሲሰራው የነበረውን ጉዳይ ለተመለከተ ይህ አከራካሪ ጉዳይ አይደለም”
ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) የኤትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ ከቢቢ የእንግሊዘኛው ዝግጅት
ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ በአገር ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በርካታ ጉዳዮችን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ሕወሓት ያሳይ የነበረው የጠባጫሪነት እና የጦርነት ቀስቃሽ ሁኔታዎች እንዲሁም በተለያዩ ኢትዮጵያ ክፍሎች በርካታ አለመረጋጋቶችን ሲፈጥሩ እንደነበር ብርሀኑ ነጋ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በአገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ለመቀበል ካለመፈለጋቸው የተነሳ እንደሆነም የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ሕወሓት ይህን ግጭት በአሳዛኝ ሁኔታ ለመፍጠሩ ምንም ጥያቄ የማያሻው ጉዳይ እንደሆነም አስታውቀዋል። አያይዘውም ‹‹እንደ እኔ ሀሳብ ለዐብይ አሕመድ ኢትዮጵያን ወደ ፊት እንዲያራምዳት ምንም አይነት ዕድል ይሰጡታል የሚል ግምትም አልነበረኝም›› ሲሉም የግል አስተያየታቸውን ይናገራሉ።
በመጀመሪያ ሕግ መነግስታዊ ያልሆነ ምርጫ ከማካሔድ ጀምሮ ፌደራል መንግስት የሚባል ለም እስከ ማለት እና አለፍ ሲልም ደግሞ በስተመጨረሻ ለረጅም ዓመታት ድንበር ሲጠብቅ ነኖረውን የሰሜን ዕዝ ሰራዊት ላይ አባላት በተኙበት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የሚናገሩት ብርሀኑ ይህ ደግሞ ከፌደራሉ መንግሥት ይህን አይነት ስርዓት አልበኝነት በዝምታ አለማለፉን ደግፈው የመከላከያ ሰራዊት እየወሰደ ያለውን ጉዳይ በተመለከተም ጥንቃቄ የተሞላበት እና ንጹሐን ሰዎች እንዳይጎዱ በታለመ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል።
በተፈጠረው ጉዳይ የሚፈጠረውን ሞት በተመለከተም ለቀረበላቸው ጥያቄ ከላይ የመለሱትን ከደገሙ በኋላ በእርግጥም ሕወሓት በማይካድራ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እና ጥቃት ማድረሱን አስታውቀዋል። ይህም ደግሞ ሕወሓት ሲያደርገው የቆየው ተግባር ነውም ሲሉ ተድመጠዋል። አያይዘውም የመከላከያ ሰራዊት በተቻለው መጠን ጥንቃቄ እያደረገ ነገር ግን ደግሞ ይህን አጥፊ ቡደፍን ግን መፋለም እንዳለበትም በአጽንኦት አስቀምጠዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013


