በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ተይዘው ከነበሩ በግንባታ ላይ ከሚገኙ 100 ከሚሆኑ መንገዶች መሀከል 20 የሚሆኑትን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እንዳቀደ አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳች ዳይሬክተር ጥኡማይ ወ/ገብርኤል ለማወቅ ችላለች።
በፕሮጀክት ተይዘው ይሠሩ ከነበሩ በግንባታ ላይ ካሉት መንገዶች መሀከል በዚህ ዓመት 65 የሚሆኑትን 80 በመቶ ማድረስና 20 የሚሆኑትን ደግሞ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚያስገባም ታውቋል።
የመንገድ ግንባታውም በተያዘለት ወቅት ለማጠናቀቅ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እየሠራ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ አንዳንድ ግንባታዎች ላይ ግን መጓተት ይስተዋላል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ቦታዎቹ ላይ በሕግ የተያዙ ጉዳዮች ስላሉ እንደሆነ ለአብነትም ገርጂ ሮባ ዳቦ አካባቢ አንድ ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ በግንባታ ላይ እንደነበር ግንባታው ግን ወደ አንድ ዓመት ገደማ እንደተጓተተ ይታወቃል ብለዋል ይህም የሆነው ቦታው አካባቢ ያሉ በሕግ እገዳ ያለባቸው አራት የሚሆኑ ቤቶች እንዳሉ እና የሕግ እገዳው ሳይነሳ የመንገድ ሥራውን መሥራት ስለማይቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሚይዛችው ፕሮጀከክቶች በአብዛኛው የሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ እንዳላቸው ነግረውናል። በተያዘው በጀት ዓመትም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አጠቃላይ ስድስት ነትብ ሦስት ቢሊዮን የሚሆን በጀት እንዳለው እና ከዚህም ላይ አምስት ቢሊየን የሚሆነውን ለመንገድ እንደተበጀተ ለጥገና ደግሞ 800 ሚሊየን የተበጀተ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ሰአትም አዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን 7000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ እያስተዳደረ እንደሆነ ከዚህም መሀል 3000 የሚሆነው ደግሞ የአስፓልት መንገድ መሆኑን ነግረውናል።በዚህ ዓመትም 500 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ እየጠገኑ እንዳሉ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
መንገድን በኔቶርክ እንከፍለዋለን ያሉት ዳይሬክተሩ አንደኛው የአስፓልት ኹለተኛው የኮብልስቶን ሦስተኛው ደግሞ የጠጠር ወይም ኬር መንገዶች ብለው እንደሚከፍሏቸው ለማወቅ ተችሏል።በዚህም ከሚታደሱት መንገዶች አካባቢ የሦስቱም አይነት ኔትወርክ ሥራዎች እንደሚሠሩም አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች ።
የመንገድ ግንባታው ላይ ያሉ ችግሮች በተለይም የሚሠሩትን መንገዶች ተሰርተው ካለቁ በኋላ የሌሎች መሰረተ ልማት ድርጅቶች እንደ ውሀ ልማት እና መብራት ሀይል ያሉ ተቋማት የመሠረተ ልማት ለመሥራት ሲሉ ውሀ መስመር የሚሰሩ ተቋማት የውሀ መስመር ለመዘርጋት እና መብራት ሀይል የእንጨት ምሰሶዎችን ለመትከል በሚል ምክንያት የተሰራውን መንገድ ያበላሹታል።
ይህም የተቋማት አለመናበብ የተስተካከለ የመንገድ ሥራ እንዳይሠራ ችግር ሆኖ ይታያል በተጨማሪም በመንገድ ዳር ላይ ያሉ ነጋዴዎች የእግረኛ መንገዱን አጥብበው እግረኛ በተሽከርካሪ መንገድ እየገባ እንዲሄድ እያደረጉት እናዳሉም የሚታይ ነው ብለዋል።
መንገድ ባለሥልጣኑ ሥራ መንገድን ከንድፍ ጀምሮ ፣የመንገዱ የጥራት ደረጃ በመሠራት ላይ እያለ ተሰርቶም ካለቀ በኋላ ያለውን የጥራት ሁኔታ፣በታሰበለት ጊዜ መጠናቀቁን ጨምሮ ወደ ሥራ ገብቶም ያለውን ሂደት እንደሚከታተል እና መንገዱን ሰርቶ ሁኔታውን አጣርቶ ከጨረሰ እና ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኃላፊነት ወስዶ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በያዝነው በጀት ዓመትም 16 የሚሆኑ አዳዲስ ግንባታዎችን ለመሥራት እንዳቀዱ እና ከነዚህም መካከል አምስት የሚሆኑት ኹለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የተመደበላቸውን ፕሮጀክቶች በቅርቡ ክቡር ከንቲባዋ አዳነች አበቤ በይፋ ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
እነዚህ የሚሰሩት ፕሮጀክቶችም የመንገድ ተጠዋሚዎችን ያማከሉ ተደርገው እየተሠሩ እንዳሉ ለፕሮጀክቱ በአጠቃላይ አምስት ቢሊየን ብር እንደተመደበለት ለማወቅ ችለናል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



