በኮንስትራክሽን ሥራዎች የቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል የግንባታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት 25 ከሚሆኑ ተቋማት ጋር ሥራ መጀመሩን በኮንስትራክሽን ሥራዎች የቁጥጥር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት የሆኑት ሲሳይ ደርብ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ባለድርሻ አካላት ከሆኑ የፌዴራል ልዩ ልዩ ተቋማት እንዲሁም ከክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሥራ ተገብቷል።
እንደ ሲሳይ ገለፃ የግንባታ ሥራው በብቃትና በውጤታማነት ለማከናወን የተስተካከለ እና ጥሩ አሠራር እንዲኖረው ከተፈለገ ከክልልም ከፌደራልም የኮንስትክሽን ቢሮ በተጨማሪም ሁሉም የግንባታን ሥራዎች የሚመለከታቸው ሁሉ የጋራ ትብብርና ቅንጅትን በመፍጠር መሠራት አለበት በዚህም ምክንያት ነው ከ25ቱ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት የተጀመረው።
በአዋጅ ቁጥር 1097 /2011 የመቆጣጠር ሥራን በተገቢው መልኩ ለመሥራት የተቋቋመ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ከተቋቋመ ኹለት ዓመት እንደሞላው አስረድተዋል ።
የግንባታ ሥራው ትኩረትን የሚፈልግ እንደሆነም ተናግረው በዚህም የኮንስትራክሽን ሥራዎች የቁጥጥር ባለሥልጣን ከባለ ድርሻ አካለት ጋር ሥራ መጀመሩ አበረታች እንደሆነ የተሳለጠ የግንባታን ሥራን ለመሥራት በዋናነት የግንባታ ሥራውን ከመቆጣጠር አንፃር ጥቅም አለው ተብሎ ታምኖበት እንደሆነም ተናገረዋል።
የቁጥጥር ሥራው ዓይነት በተለይም የመንግሥት ግንባታ ሥራዎች ሲሆኑ የግንባታ ሥራው በታሰበለት ጊዜ መሠራቱን፣ በተያዘለት የጥራቱን ደረጃ በመሰራት ላይ እና ተሰርቶ ካለቀ በኋላም፣ በተበጀተለት በጀት መሠራቱን፣ በዋናነትም ከኢንዱስትሪው ግብአት ጥራት እና ከአካባቢ ደህንነት አንፃር ከየተቋማቱ ጋር በቁርኝት እንደሚሠሩም ገልፀወል።
በግለሰብ ግንባታዎች ደግሞ ጥራታቸውን፣ የግንባታ አካካባቢውን ሁኔታ ይቆጣተራል ተብሏል።
በዋናነትም ግንባታዎች በተያዘላቸው በጀት፣ በታቀደላቸው ጊዜ፣ የጥራት ደረጃቸውን በጠበቀ እንዲሁም የማኅበረሰብን እና የአካባቢን ደህንነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲፈፀሙ ብሎም የግንባታ ኢንዱስትሪው ለአገራዊ ማኅበረ-ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና መጫወት እንዲችል ለማድረግ በሚካሄደው ጥረት የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።
የግንባታ ኢንዱስትሪው እንዲጎለብት የቁጥጥር ሥራውን በትብብር እየተናበቡ መሥራት ግልፅነትን በመፍጠር ውጤታማ እንደሚያደርግ በተጨማሪም በጋራ መሥራቱ በኢንዱስትሪው ሂደት ውስጥ የጊዜና የሀብት ብክነትን ለመታደግ እንደሚረዳም ገልፀዋል፡፡
የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥነው የግንባታ ኢንዱስትሪው የቁጥጥር ሥራ እንዲሳለጥ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካል በጋራ ርብርብ ሲያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ከ10 ዓመት በላይ በግንባታ ሙያ ልምድ ያላቸው አብነት እንዳልካቸው ኢንጂነር እንደተናገሩት የግንባታ ሥራው ብዙ ችግሮች እንዳሉትና ይህንንም ችግር ለመፍታት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል በተለይም ብልሹ አሰራር እንዳለ እና በስፋት ሊሰራበት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የግንባታ ሥራዎች በጣም ትኩረት የሚፈልግ ሥራ እንደሆነ የጠቀሱት ኢንጂነሩ የአንድ ህንፃ ጥራት አለመጠበቅ ከተሰራ በኋላ ችግር ቢፈጠር የብዙ ሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላልም ነው ያሉት።
የግንባታ ሥራዎች ላይ ያሉ ችግሮች ግንባታ እያከናወንን እያለ የሚመጡ እና የቁጥጥር ባለሙያዎች ነን የሚሉ ብዙ እንደሆኑና ሥራውንም ለመሥራት አዳጋች ያደርግባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።
የግንባታ ቁጥጥር ጥሩ ሆኖ ሳለ ከቀድሞው የተሻለ ግን ምንም ነገር የለም አሁንም እንደ ድሮው ከወረዳ ከቀበሌ ይመጡና ተቆጣጣሪዎች ነን በማለት ብልሹ አሰራር ጉቦ መጠየቅ አለ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የግንባታ ዘርፉ ዋነኛ ችግሮች መካከል ብልሹ አሰራር፣ ጥራት፣በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ፣በተያዘለት ዋጋ አለመጠናወቅ እንደሆነ ይህንን ለማስቀረት በመንግስት የሚወሰዱት እርምጃዎች የሆነ ተቋም አቋቁሞ ይቆጣጠራል ማለት ብቻ ነው የግንባታ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ የቁጥጥር ሥራን ነው የሚሰራው ተቋም ከማብዛት ውጪ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ ግን አሁንም ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል።
የስልጣን ክፍፍል ላይ ችግር አለ ያሉት መሀንዲሱ ኮንስትራክሽን ሥራዎች የቁጥጥር ባለሥልጣን ሲባል የማን የበላይ እንደሆነ ማን የበታች ተጠሪዎቹ እንደሆኑ አያታወቅም ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ግንባታ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ያሉት አብነት በተለይም የግንባታ ህግጋቶቹም ከጊዜው ጋር ተከትሎ መሻሻል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



