“የማይካድራ ጭፍጨፋ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጥልቅ ሀዘን ያስከተለ ነው” ዶክተር ዳንኤል በቀለ ኢሰመኮ ኮሚሽነር

0
785

በህወሓት ጁንታ ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር ዘመቻ መጀመርን ተከትሎ በማይካድራ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመው እልቂት በነዋሪዎች እና በተመልካች ላይ አስከፊ የሥነ ልቦና ቀወስ ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር (ኢሰመኮ) ዶክተር ዳንኤል በቀለ አስታወቀዋል።
ዶክተር ዳንኤል የማይካድራ ጭፍጨፋ አስመልክቶ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፣ በማይካድራ የተፈጸሙ ግፍ በቁጥር ከሚገለጸው ሪፖርት ባሻገር በነዋሪዎች ላይ ሰብዓዊ እና ስነልቦናዊ ቀውስ እንዲሁም ጥልቅ ሀዘን አስከትሏል።

በማይካድራ አማራ እና በወልቃይት ተወላጆች ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ተከትሎ ቤተሰቦች መበታተናቸውንና ሕፃናት ለሥነልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል፤ የጭፍጨፋው ሰለባ ቤተሰቦች ሕይወታቸውን እንደቀድሞ ለማስቀጠል አዳጋች እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል። በመሆኑም ኢኮኖሚያቸው እዲያንሠራራ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስን መቋቋም እንዲችሉ ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ተጎጂዎቹ አስቸኳይ ድጋፍና እንክብካቤ የሚፈልጉ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአካባቢው የሚገኙ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል

የማይካድራ ጥቃት ቀላል የወንጀል ድርጊት አይደለም ፣ አስቀድሞ የታቀደ እና በጥንቃቄ የተቀናጀ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው ያሉት ዳንኤል፤ የአካባቢው የፀጥታ መዋቅር ለጥቃቱ ተጠያቂ ከሆነው ሳምሪ ከሚባለው ቡድን ጋር ተባብሮ ንጹሃንን ከጉዳት ከመጠበቅ ይልቅ ጥቃቱን መደገፉንና በጥቃቱ መሳተፉን አስረድተዋል።
ወንጀሉ በአካባቢው በነበረው ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ድጋፍና ተሳትፎ የተፈጸመ ነው ያሉት ዳንኤል፤ ለወንጀለኞች ድጋፍ ያደረጉ እና የተሳተፉ የአካባቢው የፖሊስ እና ሚሊሻ አባላት በሕግ ፊት ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል ።

ኮሚሽነሩ አክለውም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም ተፈጽሞ የማይታወቅ አይነት ጭካኔ የተሞላበት የወንጀል ድርጊት እንዴት እንደተፈጸመና እንደተቀነባበረ ተጨማሪ ምርመራዎችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የቅድሚያ ሪፖርቱ በቁጥር እና በጉዳት መጠን ላይ ትኩረት ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ዳንኤል፤ ጭፍጨፋው ያስከተለው የሥነልቦና-ማኅበራዊ ተፅእኖው እንዲሁም ወንድም ወንድም ላይ እንዴት እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ሊፈጽም እንደቻለ የዘርፉን ባለሙያዎች ትንታኔ እና አካታች ጥናት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here