የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ምስጋና ኢንጂፈታ እንደተናገሩት በመተከል ዞን የሚገኙ የጥፋት ቡድኖች ለክልሉ መንግሥት እጅ እንዲሰጡ በቀረበው ጥሪ መሰረት እስከ ትናንት ድረስ ዳንጉር ወረዳ ላይ ይንቀሳቀሱ የነበሩ 43 ፀረ-ሰላም ሀይሎች እጅ የሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን የሚመሩ ግለሰቦች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ በመሪዎቹና በተላላኪዎቹ መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ በተበታተነ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ለማወቅ መቻሉን ገልፀዋል።
እስከ አሁን ድረስ እጃቸውን ለመንግሥት የሰጡት 43 ፀረ-ሰላም ኃይሎች በዚሁ የአሳብ ልዩነት እጅ ሊሰጡ እንደተገደዱ መረጃዎች አግኝተናል ብለዋል።
እነዚህ ኃይሎች በዳንጉር ወረዳ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሲሆኑ በሌሎችም ወረዳዎች የሚገኙ የጥፋት ቡድኑ ርዝራዦች እጅ በመስጠት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ለኢትዮ-ኤፍ ኤም እንዳሉት ለጥፋት ቡድኑ ጥሪ የቀረበው የሕዝብና የአገር አንድነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ጠቁመው የጥፋት ኃይሎች ጥሪውን ተቀብለው ለመንግሥት እጅ እንዲሰጡ ጠይቀው እጅ በማይሰጡት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013



