የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤት ውሎና ሕወሓት

0
862

ሰኞ፣ ኅዳር 21 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሐመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለይ የፌደራል መንግሥት በሕወሓት ላይ እየወሰደ ስለሚገኘው ሕግን የማስከበር እርምጃ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽና ማብራሪያ ከከዚህ ቀደሞቹ ምላሾች እና ማብራሪያዎች የተለየ የሚያደርገው ከኹለት ሰዐታት በላይ መፍጀቱ እና ከለውጡ ጥቂት ወራት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ጉዳዮች በዝርዝር እና በጥልቀት መዳሰሱም ጭምር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዳሰሷቸው ጉዳዮች ባልተናነሰ እጅግ በጣም መሳጭ፣ ገላጭና ቀልብ ሳቢ በሆነ አቀራረባቸው የተነሳ ከዚህ ቀደም ከሰጡት ተመሳሳይ ማብራሪያዎች በተለየ የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል፤ ብዙዎችም በመንግሥታቸው ሆነ በእርሳቸው ላይ ያላቸውን አቋም እንዲለውጡ አስገድዷቸዋል።
ዐቢይ ለውጡን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር መንበረ ሥልጣንን ከመቆናጠጣቸው ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ እንዲሁም ከተቆናጠጡም በኋላ በተለይ በደኅንነት ዋና ኀላፊ በነበሩት ጌታቸው አሰፋ ተጽዕኖ ሥር እንደነበሩ የገለጹት የብዙዎችን ቀልብ ሰቧል፤ አሳዝኗልም። በሌላ በኩል ደግሞ በምንም ዓይነት ሁኔታ የውጪ አገራት ተጽዕኖም ሆነ ጣልቃ ገብነት መንግሥታቸው እንደማይቀበል ከቀደመ የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር በግልጽ የመንግሥታቸውን አቋም የገለጹት ከፍተኛ ከበሬታን አሰጥቷቸዋል።

በማኅበራዊ ትስስር መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያዎች ለብዙዎች መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን ድጋፍ አሰባስቦላቸው አልፏል። በጦር ሜዳ ለተሳተፉ የጦር አመራሮችን ጀግንነት የገለጹበት ቃላቶች በተለየ ልዩ ትኩረትም ተችሯቸዋል፤ በማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ላይ በሰፊው ተጋርተዋል። “ጅግና ማወደስ ሲችሉበት!” አሰኝቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በተመለከተ የሕወሓት ቃል አቀባዮች በቀጥታ ምላሽ የሰጡ ባይሆንም መቀሌን ጨምሮ አብዛኛውን የትግራይ ክልል ከተሞች መቆጣጠራቸውን የተመለከተውን የድል ዜና ግን ባለመቀበል አጣጥለውታል። የአብዬን ለእምዬ በማለት ድሉ የኛ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ጦርነቱ ዐቢይ እንደሚሉት አለማብቃቱን፣ ትግሉም ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን አበክረው ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ኀሙስ አመሻሽ ላይ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ብቅ ያሉት የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ከፍተኛ አማካሪና የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ድካም በተጫነው መግለጫቸው “መቀሌን ለቀናል፤ ግን ተሸንፈን አይደለም። ካለን ውስን አቅም አንጻር በሁሉም ቦታ አጥቂ፣ ተከላካይና ደምሳሽ ሆነን የምንቀጥልበት ሁኔታ በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ የተጠቀምነው ስልት ጠላት በሁሉም ቦታ ከባድ ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረግ ነው” ብለዋል።

ጌታቸው መቀሌን የለቀቁበት ዋና ምክንያት ያደረጉት በከተማ ውስጥ የሚካሄድን ጦርነት ለማስወገድና የፌደራል መንግሥቱ ከኤርትራ ጦር ጋር በማበር ግልጽ የዘረፋና የማውደም ሂደት ውስጥ እጃችንን ላለማስገባት መሆኑን ጠቅሰው፥ “ኀላፊነት ስለሚሰማን ነው” ብለዋል። በተጨማሪም የሕዝብ እልቂትንም ለመከላከል መሆኑንም አስታውቀዋል።

ብዙ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች ከመግለጫው ይልቅ የጌታቸውን የድካም ገጽታ፣ ጉስቁልና እና ደካማ ድምጸት መነጋገሪያ አድርገታል። ወኔ የከዳቸው መሆኑና የነበራቸው በራስ መተማማን መጥፋት ብዙዎች ጌታቸው የሰጡትን መግለጫ በቁም ነገር ከመውሰድ ይልቅ ተሳልቀውበታል፤ አጣጥለውታል።

ከጌታቸው ቀደም ብሎ የትግራይ መከላከያ ኀይል ቃል አቀባይ የሆኑትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይ ቴሌቪዥን ብቅ በማለት መግለጫ የሚሰጡት ታጋይ ገብረ ገብረጻድቃን ሦስት ዋና ዋና ግንባሮች ድል ማስመዝገባቸውን ከመጥቀስ ባሻገር መቐለንም የለቀቁት ለስልት መሆኑን አስታውቀዋል። ብዙዎች የታጋይ ገብረን መግለጫ እንደ ቀልድ በመቁጠር በሰፊው ሲጋሩት የከረሙ ሲሆን ጥቂቶችም ቢሆኑ ድሉን በቁም ነገር የወሰዱት ግን አልታጡም።

በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጦር ዘመቻው በይፋ መጠናቀቁን በመግለጽ፥ የቀረው ጉዳይ ቢኖር ወንጀለኞችን ከተሸሸጉበት በመልቀም ለፍርድ ማቅረብ ነው ሲሉ ትኩረታቸው ትግራይን መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል። የሆነው ሆኖ ጦርነቱ በአራት ሳምንታት ተጠናቋል የተባለው ዘመቻ በምን ምልኩ ዘላቂ መቋጫ ያገኛል የሚለው እስካሁን ብዙዎችን በማነጋገር ላይ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here