በየትኛውም የዓለም ክፍል በጦር መማዘዝ ምክንያት በቀጥተኛ ከሚሳተፈው ይልቅ በማያገባው እና በማይመለከተው ምናልባትም ባልመረተው ምክንያት የሚጎዳው እና የሚሰቃው ንጹሐኑ ነው። ይህ ታዲያ ጦርነት በባህሪው ይዞት ሚመጣው አስከፊው እና አፍራሹ ባህሪው ዋነኛው ነው ። ከአንድ ቦታ ወደ በአንጻራዊነት ወደ ሰላም ወደ ሚባለው አካባቢ ጨርቄን ማቄን ሳይል ነብሱን ለማዳን የሚጓዘው እልፍ ነው። በተደጋጋሚም እንደሚባለው ጦርነት ሰው አይመርጥም፣ ያጠፋል፣ ያፈናቅላል፣ አገር ያፈርሳል፣ ዜጎችን ለእንግልት እና ለችግር ይዳርጋል።
በምንም አይነት ሁኔታ ጦርነትን እና ወደ ጦርነት የሚመሩ ጉዳዮች ምክንያታቸው ምንም ቢሆን እንኳን እንደ አማራጭ ሊወሰዱ ሚገቡ አይሆኑም መሆንም የለባቸውም። ከአረቡ አብዮት በኋላ እንደቀደመው ያልሆኑት አገራትን ማንሳት በቂ ሳይሆን አይቀርም። ለአይን የሚያሳሳ ከተሞች ያሏቸው እና ጥንታዊነታቸውን ጠብቀው የኖሩ አገራት ዳግመኛ ይነሳሉ ተብሎ ለመናገር በማያስደፍር ሁኔታ ከአፈር ተደባልቀው እና ዜጎቻቸውን ለቸነፈር ዳርገው እንዲያም ሲል በተለያዩ አገራት ለስደት ዳርገው መመልከት የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ለመስበክ ከበቂ በላይ ሊሆን ይችላል።
በእኛም አገር ከሶሪያ ተሰደው ዓለም የድህነት ጭራ ተብላ በምትጠራው ኢትዮጵያ ለመሸሸግ እና ሕይወታቸውን ለመምራት ወሰኑበት እንዴት ያለ የጭንቅ ስፍራ ላይ ኖረው እንደነበር ያመላክታል። በባህል፣ በቋንቋ በቀለም በማይመስላቸው ሕዝብ መሀል መገኘትን ከእነርሱ በላይ ሰቀቀኑን የሚረዳው እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከሶሪያም ባለፈ በጥንታዊቷ የመንም ሕጻናትን በሙሉ አይን መመልከት እስከሚያሳቅቅ ድረስ ሰብዓዊ እርዳታ ተነፍገው እና በጦርነት ምክንያት ዕርዳታውን ማድረስ ሳይቻል ቀርቶ በየደቂቃው ጮርቃ ሕጻናት ይረግፋሉ። ገና ተወልደው ዓለምን በሙሉ አይናቸው ሳይመለከቱ ከዕናቶቻቸው ጉያ ሳይላቀቁ በዛው የሚያሸልቡት ሕጻናት ዓለምን በችግሯብቻ እንድንረዳት የሚያደርጉ ቢሆንም የጦርነትን አስከፊ ጎን ደግሞ አጉልቶ የሚሳይም ጉዳይ ነው።
‹‹የተረሳው ጦርነት›› እስከመባል የደረሰው የየመን የዕርስ በርስ ጦርነት በርካቶችን ለሕልፈት፣ ገሚሉን በባህር ለመሰደድ እና ባህር አውሬ እራት እንዲሆኑ ያደረገ ክፉ እና የክፉ ጥግ ጦርነት መሆኑን ምስክር የማያሻው ጉዳይ ነው። ጦርነት ታዲያ እነድ ጊዜ ከተደረገ በኋላ እና ዙጎች በቶርነት ሳቢያ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ሲስተጓጎል እና እሱነብም ተከትሎ ለዕለት ጉርስ ሲቸገሩ አሰብዓዊ ዕርዳታ ሊያገኙ ይገባል። በቅርቡ በኢትዮጵያ በፌፈራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የነበረው እስጥ አገባ ወደ ለየለት ጦርነት ተገብ በርካቶችን ለስደት እና ለእንግልት ዳርጎ በቴሌቪዥን እናየው የነበረው የሩቅ አገራት ታሪክ በአፍንጫችን ስር ሲከናወንም ተስተውሏል። በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሕግ ማስከበር እርምጃ ነው በተባለለት በዚህ ጦርነት አማካኝነት ሕጻናት እና ሴቶች እንዲሁም አረጋዊያን ቀያቸውን ትተው ወደ ጎረቤት አገራት ባዕድን ምድር ሊሸሸጉበት ሽተው ሔደዋል። ታዲያ በፌደራል መንግሥት በኩል ተልዕኮው መጠናቀቁን ይፋ ተደርጎ ባለበት ሁኔታ ሰብዓዊ ዕርዳታው ጉዳይ ግን በአጥጋቢ ሁኔታ እየተሰጠ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች። ይህ ታዲያ ከጦርነት አምልጦ በየጢሻው እና በየሜዳው ለተበተነው ሕዝብ የጥይት አረር ሳይመታው ቢተርፍም በረሐብ እንዲያልቅ ግን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም። ቀን እና ጊዜ የማይሰጠው ረሀብ በየሰዓቱ ከሚተይቀው የምግብ ፍላጎት ሊገላገሉ የሚችሉትም በምግብ እና ምግብ ብቻ እንደሆነ እየታወቀ ሰብዓዊ ዕርዳታው ጉዳይ ቸል ተባለ እስኪመስል ድረስ ሲከናወን እየታየ አይደለም። ይህ ታዲያ ጦርነቱ ንጹሐንን ላለመጉዳት በጥንቃቄ ነው የተደረገው በሚባልበት ሁኔታ በአንጻሩ ደግሞ ንጹሀን እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ደግሞ አለመድረስ ችግሩን ከጦርነቱ በባሰ ሁኔታ እንደሚያገነው አዲስ ማለዳ ታምናለች። ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ለጋሽ ድርጅቶች እንዲሁም በሰብዓዊ ዕርዳታ በኩል ሰፊ ስራ በመስራት የሚገኙ ተቋማት በአስቸኳይ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎችን ሊደርስላቸው ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ከዚህ ጋር በተጓዳኝም በጦርነቱ ምክንያት ድንበር ተሸግረው ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የሸሹ ዜጎችንም ጉዳይ በሚመለከት መንግሥት መመለስ ሥራዎችን እንደሚሰራ በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል የተገለጸ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ዙጎችን ወደ አገራቸው እና ቀያቸው ለመመለስ የሚሰራ ስራ እንደሌለ አዲስ ማለዳ ከስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጎዳዮች ኤጀንሲ ያገነችው መረጃ ያመላክታል። በአካባቢው ተፈላቅለዋል የተባሉ ሰዎችን በሚመለከት አካባቢው የዕርሻ እና ምርታማ በመሆኑ የተፈናቀሉት ዜጎችም በአንዛኛው በእርሻ ስራ የተሰማሩ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ ተመልሰው ወደ ቀደመው ኑሯቸው የማይመለሱ ከሆነ እና የምርት ዘመናቸው ካለፈ በኋላ ከተመለሱ ለተጨማሪ የዕርዳታ ጠባቂነት እንደሚዳረጉም ሊታሰብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረግ ለመንግሥት እና ለዚህ ዓላማ ብለው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ግዴታ ሲሆን ለዜጎች እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ደግሞ በአንጻሩ ሰብዓዊ መብታቸው እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። የትኛውም ታዳጊ ከወላጆቹ ጋር የመኖር መብቱ እንዳለው በሕግ የተቀመጠ ጉዳይ ቢሆንም በተፈተረው አስገዳጅ ሁኔታ ወላጆች እና ልጆች የተጠፋፉበት እና ልጆችም ደኅንነት አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ጉዳዩን ችላ በማለት ከፋ ጉዳት ሲከሰት ዕጅን አጣጥፎ መመልከት አይገባም ስትል አዲስ ማለዳ አቋማን ትገልጻለች። በተደጋጋሚ እንደሚነገረው ከትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች አሁንም በከፋ እና በአሰቃቂ ሁኔታ ላይ እንደሚገኑ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተቀባበሉት ይገኛል። ይህ ታዲያ መንግሥትን ሊያስደነግጠው እና በሙሉ አቅም የትኛውንም አማራጭ በመጠቀም ሊያድናቸው እና ሊደርስላቸው ይገባል። ለመንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ዜጎች በአፋጣኝ መድረሱ በኋላ ላይ ለሚኖርበት የቤት ስራ እና መልሶ የማቋቋም ስራ ከወዲሁ ሊያቀልለት የሚችልም እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ነገር ግ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጉዳዩ በከባድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ዕጦት ምክንያት መሰረታዊ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ቀርተው ለሚፈጠረው ችግር ቀጠናውን እና በተለይም ደግሞ አሁን በጦርነቱ ተደናገጠውን አካባቢ የባሰ ወደ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚከተው ከወዲሁ ሊጤንበት ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ተደመድማለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013


