በዓመት እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማዕድን ምርመራ ይወጣል
ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማዕድን ናሙና ምርመራ ማዕከልን ለማደራጀት እና መሣሪያዎቹን ለማሟላት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ቤተ-ሙከራውን ለማደራጀት መሣሪያዎችን ማሟላት ዋናው ጉዳይ እንደሆነና እና መሣሪያዎችን ከውጭ አገር ማስገባት እንደሚያስፈልግ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ያስታወቀ ሲሆን፤ እሱንም ለማድረግ በትንሹ 100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልፈግ ለማወቅ ተችሏል።
የተጠቀሰው ገንዘብም ሥልጠናዎችን በአጠቃላይ የቤተ ሙከራውን ዝግጅት ሳይጨምር እንደሆነ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የማዕድን ናሙና ምርመራ እና የወርቅ ማቅለጫ ሥራዎችን ሲሠራ የነበረው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላብራቶሪ መታደስ እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ታከለ ኡማ ባሳለፍነው ሳምንት ላብራቶሪውን በጎበኙበት ወቅት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።
ከ50 ዓመታት በላይ የተሟላ የኬሚካል ምርመራ ሲያካሂድ የቆየውን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላብራቶሪ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዳልሆነና ዘመናዊ እና ደረጃውን የጠበቀ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሚኒስቴሩ በጉብኝታቸው ወቅት አስታውቀው እንደነበር በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የጂኦኬሚካል ላብራቶሪ ዳይሬክተር ነጋሽ ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ቤተ-ሙከራን የማዘመን ሥራዎች በጂኦሎጂካል ሰርቬይ በኩል እየተሠራ እንደሆነና ቤተ-ሙከራውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ የሚሠራውን ሥራ በኹለት ዙር ለመሥራት እንደታቀደም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በመጀመሪያው ዙር የኢንዱስትሪ ማዕድን የሚባሉት እንደ ወርቅ ፣ ብር ፣ ከየቦታው የሚመጡትን ብሔራዊ ባንክ የሚቀበላቸውን (gold bar) የተሰኙትን ማዕድኖች የመመርመሪያ እና ማቅለጫ መሣሪያዎች ማሟላት እና እደሳ የሚፈልጉትን ማደስ እንዲሁም አዳዲስ የሚገዙ መሣሪያዎችን መግዛት እንደሆነ ተናገረዋል።
በዚህም እስከ አሁን ባለው ለቤተ-ሙከራው የመመርመር ሥራ አስፈላጊ ሆነው የተገኙት 23 የሚሆኑ አዳዲስ መሣሪያዎችን ለመግዛት እቅድ እንዳለ አስታውቀዋል።
ኹለተኛው ዙር ደግሞ ቤተ-ሙከራውን ደረጃውን የጠበቀ የምርምር ማዕከል ለማድረግ እንደታለመና ይህንንም በተመለከተ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችን መሣሪያዎችን የማሟላት ሂደት እንደሆነም አስታውቀዋል።
ይህ ላብራቶሪ ባለመደራጀቱ (international certification organization ICO) ሰርተፍኬት ስለሌለው የመሣሪያ እጥረት እና ዘመናዊ ባለመሆኑ ማዕድን ተቀባይ ኩባንያዎች ይህ ሰርተፍኬት ከሌለው ላብራቶሪ የሚሠራውን ውጤት ለመቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ወደ ውጪ አገራት ለምርመራ የሚወጡ የማዕድን ናሙናዎች ያሉ ሲሆን ይህ ላብራቶሪ ተደራጅቶ ሲጠናቀቅ ለማዕድን ናሙና ምርመራ ከአገር ውጭ የሚላከውን ጥሬ ሀብት አገር ውስጥ በማስቀረት እንደ አገር ያለው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ እና ኢትዮጵያም ያላትን አቅም በትክክል ማወቅ እንድትችል እና እንድትሠራ ያስችላል ሲሉ ነጋሽ ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መሣሪያዎችን ማሟላትን በተመለከተ የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች ተለይተው ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመሆን የጨረታ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ እንዳሉ ጨረታውም በቅርቡ ይወጣል ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመውናል።
በቤተሙከራ እና በምርምር ረጅም እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ጂኦሎጅካል ሰርቬይ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ አሁን ያለበት ደረጃ እድሜውንና ልምዱን የሚመጥን አይደልም ሲሉ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።
አገራችንን በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር ለናሙና ምርመራ እና ለወርቅ ማጣራት ሥራ እንደምታወጣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ለማዕድን ምርመራ በዓመት ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደረግ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013



