የሰሜን ሸዋ የወፍ ዋሻ ወደ ብሔራዊ ፓርክ ሊያድግ ነው

0
1048

በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘውን የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ደን ወደ ብሔራዊ ፓርክ ለማሳደግ የክለላና መረጃ ማጠናቀር ሥራ መጠናቀቁን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአካባቢ የደን እና የዱር እንስሳት ልማት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ማራኪውን የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ደን ወደ ብሔራዊ ፓርክ ለማሳደግ ከጥቅምት 13 ቀን 2013 ጀምሮ እስከ ሕዳር 13 2013 የቆየው ክለላና መረጃዎችን የማጠናቀር ሥራ መጠናቀቁን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአካባቢ የደን እና የዱር እንስሳት ልማት ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ጥበቃ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አብርሀም ማርዬ አስታውቀዋል።

የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን በባሶና ወራና፣በአንኮበርና በጣርማ በር ወረዳዎች ከደብረ ብርሃን ከተማ 24ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ካርታውን በአዋጅ ረቂቅ ደንብ እንዲኖር ደንቡን የማዘጋጀት ሥራ ሠርተው ለክልሉ ካቢኔ እንደሚያቀርቡ ተናገረዋል።
የወፍ ዋሻ ደን የመሬት አቀማመጥ በጣም ወጣ ገባ ሲሆን 55 በመቶ ዳገታማ 35 በመቶ ወጣ ገባ፣ አምስት በመቶ ሜዳማ እና አምስት በመቶ አምባ እንደሆነ ታውቋል።

በአቀማመጡ የደጋማውን ከፍተኛ አካባቢ ከደበሌ እስከ ባሶ ደንጎራ የአፍሮ አልፓይን ገጽታና እጽዋት እንደ ጅብራ አስታ፣ ጓሣ ፣ የዋሊያ ሾህ (ጋርዳ)፣ጦስኝ፣የደጋ አሸንዳ የሚበቅሉበት በዋነኛነት ሜዳማና ከዋናው ደን ቀጥ ባሉ ገደል የተከፈለ ነው። የገደሉን አፋፍና ግርጌ ተጠንተው እስከ 15ዐ ሳንቲ ሜትር (ዲ.ቢ.ኤች)በዛፎች ዲያሜትር መለኪያ በላይ ባላቸው ግዙፍ የሐበሻ ጽድ፤ ዝገባ ፤ ኮሶ፤ ወይራ፤ ዛፎች የተሸፈነ መሆኑ ታውቋል።

ይህ ጥብቅ ደን ከደን ሐብትነት በዘለለ በውስጡ ዱር እንሰሳት በአሁኑ ሰዓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚታወቁት ተራ ቀበሮ፣ የደልጋ አንበሳ፣ ጦጣ ጥርኝ ፣ ጉሬዛ ፣ ነጠብጣም ጅብ፣ ባለመስመር ጅብ ፣ ጃርት ፣ የስታርክ ጥንቸል ፣ ሰስ ፣ ጭላዳ ዝንጅሮ ፣ ሽኮኮ፣ ተራና የምንይልክ ድኩላ ጥቂቶቹ ናቸው።

ከአእዋፍ ዝርያዎች ደግሞ ዋትልድ አይቤስ፤ ኋይት ኮላር ፒጐን ፣ ብላከ ውይንግድ ላቨበርድ፣ ቲክ ቢልድ ሪቨን ፣ ኋይት ቢልድ ስታርሊንግ ፣ብሉ ወይንግድ ጉዝ እና ክሊፍ ቻት የሚገኙ ሲሆን በአገራችን ብቻ የሚገኙ ደግሞ አንኮበር ሶሪን እና አብሲኒያን ሎንግ ክላው እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።

የአካባቢው ኅብረተሰብ ደኑ ላይ በሕገወጥ መልኩ የልቅ ግጦሽ ያደርጋሉ ያሉት ዳይሬክተሩ ደኑን ከመጠበቅ እንፃርም ወደ ብሔራዊ ፓርክ መቀየሩ አግባብነት እንዳለው ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዚህ ይህን የወፍ ዋሻ ወደ ብሔራዊ ፓርክ ሲለወጥ መልከ ምድሩም አመቺ ስለሆነ ከውጪ አገር ለሚገቡ ጎብኚዎች ከዋና ከተማው ስለማይርቅም ጭምር ቱሪስቶችን ይስባልም ብለዋል።

አእዋፋትና እጽዋት የያዘና ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረዉን የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ደን ወደ ብሔራዊ ፓርክ በማሳደግና የቱሪዝም መሰረተ ልማቱን በማስፋፋት ወደ ተሻለ የጥበቃ ትኩረትና ጥቅም ለማሻሻል ሥራዎችን እያከናዎኑ ይገኛሉ።

የወፍ ዋሻ የተፈጥሮ የመንግሥት ደን ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የንጉሥ ደን በመባል ይጠበቅ እንደነበር እና ከ1950 ዓመት ደግሞ ጥብቅ የመንግሥት ደን ተብሎ እንደነበር በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ከፍተኛ የመንግሥት ደን ተብሎ የሚጠበቅ ቦታ እንደሆነ ታውቋል።

በአማራ ክልል በብሄራዊ ፓርክ የተመዘገቡ 13 የሚሆኑ ስፍራዎች እንዳሉ ከእነዚህም ውስጥ ኹለቱ በፌደራል የአካባቢና ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል የሚተዳደሩ ሲሆኑ ሌሎቹ በክልሉ የአካባቢ የደን እና የዱር እንስሳት ልማት ባለሥልጣን ሥር ያሉ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here