ጳውሎስ ሆስፒታል በዘር ለሚተላለፍ በሽታ አዲስ ሕክምና ሊጀምር ነው

0
861

በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈጥሮ ከእናት እና ከአባት በዘር የሚተላለፍ ‘ Cystic fibrosis’ የተባለ የመተንፈሻ አካላትን የሚጎዳ በሽታን ለመመርመር ሥራ ሊጀምር መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊንየም ሕክምና ኮሌጅ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሕክምናውን ለመመርመር የሚያስችል ምንም ዓይነት የመመርመሪያ መሣሪያ አገር ውስጥ እንዳልነበር እና በአሁኑ ወቅት ግን መሣሪያውን ከመካከለኛው ምስራቅ ‘ Cystic fibrosis’ ማኅበር በእርዳታ መልክ ማግኘታቸውን እና በአሁኑ ሰዓትም መሣሪያው በሆስፒታሉ እንደሚገኝ አሳውቋል።
የመመርመሪያ መሣሪያው በገንዘብ ሲተመን ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መሆኑን ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ማኅበሩም መሣሪያውን ከማሟላት በዘለለ ሥልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም በሽታውን በተመለከተ ለሚሠሩ ማንኛውም ሥራዎች እንደሚደግፋቸው ቃል መግባቱ ተጠቁሟል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊንየም ሕክምና ኮሌጅ ውስጥ የሕፃናት እና የሳምባ ሀኪም ዶክተር አባተ የሺድምበር እንደተናገሩት በአገራችን የዚህ በሽታ ምንነት እንደማይታወቅ ምን ያህል ታማሚ እንዳለም ይሁን በሽታው በትክክል መኖሩን የሚታወቅበት ሁኔታ እንዳልነበር በሽታው ግን አለ ተብሎ እንደሚገመት አስታውቀዋል።

በአገራችን የበሽታው መመርመሪያ መሣሪያ ባለመኖሩ ምክንያት ምናልባትም በዚህ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች እንደ ሌላ በሽታ በመቁጠር ሌላ መድኃኒቶች ሲጠቀሙ የቆዩ እንደሆኑ ይገመታል ብለዋል።

በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ይገኛል በተለይ ደግሞ ሕፃናት ላይ ይታያል ያሉት ዶክተሩ ምልክት የሚያሳዩም የማያሳዩም አሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ በሽታ የዕድሜ ልክ በሽታ ነው በሰዓቱ ካልታወቀና ሕክምና ካላገኘ ብዙ ተጓዳኝ በሽታዎች እንደ ጉበት ፣ ስኳር፣ያሉ ከዛም ሲያልፍ ከኹለት እስከ አምስት አመት ባሉ ሕጻናት ላይ ደግሞ ህልፈትን ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቅሷል።

በዋናነት በሽታው የሚያጠቃው ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እንደ ክሎራይድ ፣ ሶዲየም የሚገቡበትን ቀዳዶች የንጥረ ነገሮች ማጓጓዣ ፕሮቲን በአግባቡ ሥራውን እንዳይሠራ ቅርፁ አሠራሩ እንዲለወጥ የሚያደርግ የዘረመል መለወጥ ችግር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ለሰውነታችን የሚያስፈልጉት ፈሳሾች በትክክል እንዳይመረቱ ፈሳሽ የሚያመላልሱት ትቦዎች እንዲዘጉ እንዲደርቁ ያደርጋል ከአመራረታቸው ጀምሮ እስከ ወደተፈለገው የሰውነት ክፍል ድረስ የሚወስዱበትን ሁኔታ ይረብሹታል።

በዚህም በዋነኝነትም በሽታ ያለበት ሰው የሚያሳየው ምልክት በሳንባ እና የአየር ቧንቧ አካባቢ የሚታይ ችግር ያመጣል ለምሳሌ በተደጋጋሚ ለኢንፌክሽን መጋለጥ ፣ ሳል ፣ ለመተንፈስ መቸገር ፣ መታፈን ፣ ማስቀመጥ ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ ክብደት አለመጨመር ፣ ሰውነታቸው እያደገ ከመጣ ደግሞ የጉበት በሽታ ፣ በሕይወት የመቆይት ዕድል ካላቸው ኢንሱሊን የሚያመርተውን የሰውነት ክፍልም ስለሚጎዱ ዕድሜያቸው ሲጨምር የስኳር በሽታም እንደሚያመጣ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
የሰው ልጅ 46 ዘረመል አለው ያሉት ዶክተሩ ሰባተኛው ዘረመል ላይ የሚገኝ የሰውነታችንን አሠራር የሚቆጣጠር ዘረመል ላይ በሚፈጠር ለውጥ ምክንያት የሚመጣ በሽታ እንደሆነና ሰባተኛው ዘረመል ላይ ለምን ለውጥ እነደሚመጣ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ነገር ግን ከዘር ከአያት ከቅድመ አያት የሚወረስ እንደሆነ ይታመናል ብለዋል።

ይህን የዘረመል ችግር የተሸከሙ እናት እና አባት የሚወለደው ልጅ ዘረመል ግማሽ ከእናቱ ግማሽ ከአባቱ ስለሚወስድ ኹለቱም ላይ ችግሩ ካለ ብቻ ልጁ የዚህ በሽታ ተጠቂ ይሆናል። ነገር ግን አንዳቸው ላይ ብቻ ከሆነ ችግሩ ያለው በሽታው እንደማያጠቃው ተናግረዋል።

ለበሽታው እስካሁን የሚያድን መድሀኒት እንዳልተገኘለት እና ነገር ግን በሽታው ሊያስከትላቸው የሚችሉትን ተጓዳኝ በሽታች እንዳይመጡ ከመከላከል አኳያ በሽታን መመርመር ጥቅም እንዳለው አሳውቀዋል።

ይህ በሽታ በብዛት ከጥቁሮች ይልቅ ነጮችን እንደሚያጠቃ በጥናቶች ተመላክተዋል ያሉት ዶክተሩ ነገር ግን በአፍሪካ ውስጥም በደቡብ አፍሪካ ፣ ታንዛኒያ ፣ ግብፅ መኖሩ ተረጋግጧል በዋነኝነትም በዚህ በሽታ ተጠቂ የሆነችው አገር አይስላንድ እንደሆነች ለማወቅ ተችሏል።

በአገራችን በሽታው መኖሩንና አለመኖሩን ከቱርክ የሚመጡ ባለሙያዎች ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በጋራ በመሆን የማጥናት ሥራ እንደሚሠራ እና የመመርመሪያ መሣሪያው አጠቃቀም ለዶክተሮች ሥልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ሥልጠናው በዚህ በዚህም ኹለት ሳምንት እንደሚሰጥ በመጀመሪያው ዙር 500 ለሚሆኑ ምልክቱን ላሳዩ ሰዎች በተለይም ሕፃናት ይሰጣል ምናልባት አንድ ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here