በየትኛውም የዓለም ጫፍ ታላላቅ መሪዎች እና በአስተዳደራቸው ግሩም የተባለላቸው መሪዎች እና አገርን ያስቀጠሉ በሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች መለኪያቸው በሰላም ጊዜ አገራቸውን እንዴት አስተዳደሩ በሚለው መርህ እንደሆነ ይነገራል። አገር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ወደ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ ልትገባ ትችላለች። በዚህ ወቅት ታዲያ ተገዳም ይሁን በውዴታ ለገባችበት ጦርነት እና ግጭት በሰዓቱ ወደ ጦርነት በተገባበት ወቅት ማስተዳደሩ እና አገር ማቆየቱ እምብዛም አይከብድ ይሆናል።
ነገር ግን የግጭቶች ጊዜ እና የጦርነት ጊዜያት አልፈው ሕዝብ ወደ ነበረበት ስፍራ ሲመለስ ግን ከድህረ ጦርነቱ እና ግጭቱ ጋር ሰፊ እና ከባባድ ጥያቄዎች መውጣታቸው አይቀሬ ናቸው። በጦርነት ወቅት ታፍነው የነበሩ ጥያቄዎች፣ ተጥሰው የነበሩ መብቶች በድህረ ግጭት ወቅት አይናቸውን አፍጥጠው ለመምጣታቸው ማረጋገጫ አያሻም። ይህ ሲሆን ታዲያ መንግሥት የትኛውን ጉዳይ ከየትኛው ማስቀደም እና ቅድሚያ ሰጥቶ መፍታት እንደሚኖርበት አስቀድሞ የሚያስብበት ጉዳይ ነው።
ይህን ነገር ታዲያ ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ስናመጣው መንግሥት በሕግ ማስከበሩ ወቅት የተለየ ጥንቃቄ አድርጎ ዕርምጃ ቢወስድም የዜጎች መፈናቀል ግን አልቀረም። በነባራዊ ሁኔታ ላይ ይመለሱ እና ምልከታ ይደረግባቸው ነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ለጊዜውም ገሸሽ መደረጋቸውም የማይታበል ሐቅ ነው። ይህ ጉዳይ ታዲያ ምንም እንኳን ከጊዜያት በፊት በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል ሕግ ማስከበር ተልዕኮው መጠናቀቁ ቢበሰርም አሁንም ድረስ ጨርሶ ባለመቆሙ ጥያቄዎች በይደር እንደቆሙ ይታወቃል።
በቅርብ ጊዜም ሆነ በተራዘመ ብቻ ቀናቸውን ጠብቀው ከማያልፈው ሕዝብ ዘንድ ጥያቄዎች መፍለቃቸው እና መንግሥትም ከዕውነታው ጋር መጋፈጡ የማይቀር እንደሆነም ይጠበቃል። በዚህ ወቅት ታዲያ መንግሥት ምን ለመመለስ እና አገርን እንዴት ሊያስተዳደር ተዘጋጅቷል? ምክንያቱም በሰላም ቀናት ሕዝብን ማስተዳደር ከከባድ ሥራዎች ሁሉ ከባዱ እንደሆነ ስለሚጠበቅ ነው።
በሰላም ጊዜ የልማት ጥያቄ፣ መልካም አስተዳደር ጥያቄ፣ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ እና መሰል ነገሮች ብቻቸውን ከፍተኛ ቤት ሥራ በመንግሥት ላይ ለመጣል የማያንሱ ናቸው። ይሁን እንጂ ከዚህም ባለፈ ግን በጦርነት ወቅት የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም፣ የመሬት እና የይገባኛል ጥያቄዎች፣ ከላይ ቀድሞውንም ከተነሱት ጥያቄዎች ጋር ተደምረው በርካታ ውጥረቶችን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርግ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በኢትዮጵያ ከሕግ ማስከበሩም በፊት በአንበጣ እና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሲናጥ እና ሲንገራገጭ የነበረው የምርት መጠን እና የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ሌላ ተጽእኖን ለመሸከም እንደማይችል መንግሥትም ሆነ ሕዝብ በሚገባ ይረዳዋል። ይህ ታዲያ በድኅረ ግጭት ወቅት ይዞ የሚመጣው ማኅበራዊ ቀውስ እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ ችግር በእጅጉ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው።
ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ወደ ጎረቤት አገር የተሰደዱትን ዜጎች ከጦርነት ሸሽተው ከመሆኑም ጋር ተዳምሮ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት በአገር ውስጥ የሚጠብቃቸው ቀደመው ንብረታቸው ወይም ኑሮ ዘያቸው ሳይሆን ሲቀር እንደገና የጥያቄ ምንጮች እና በመንግሥት እና በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ጫና የሚሳድሩ እንደሚሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።
አዲስ ማለዳ አሁንም ደግማ ምትለው ነገር በሰላም ጊዜ ማስተዳደር ከባድ ነው።ነገሮች በሰከነ አዕምሮ እና በጥያቄ ሲሞሉ እና ጥያቄዎችም ተጠራቅመው ወደ መንግሥት ሲሰነዘሩ በአንድ ጊዜ ይይዘው ይጨብጠው እንዳይጠፋ አስቀድሞ በመዘጋጀት እና ሊመጡ የሚችሉትን ጉዳዮችንም በተመለከተ ለመመከት አጥብቆ ሊሠራ ይገባዋል። ባለፈው ዘመን ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር በሚባልበት ወቅት የሕዝብ ችግር እና ብሶት በእጅጉ ታፈነበት እና ሰሚ ጆሮ ተነፍገው ለከፍተኛ ስቃይ እና በመንግሥት ላይ እስከ ማኩረፍ የደረሱ ሰዎችን ማስታወስ ይቻላል።
ነገር ግን ጉዳዩ በወቅቱ በጦርነት ለምትታመሰው ኢትዮጵያ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሚሠራ አልነበረም እና የሕዝብ ጥያቄ ታምቆ ረጅም ዘመናትን ለመኖር ተገዶ ነበር። ኢህአዴግም በኢትዮ ኤርትራ የጦርነት ወቅት አገርን ለማስተዳደር እና ለማንቀሳቀስ እንዲሁም የአገርን አንድነት እና አንድ ልብነት ማግኘት ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን የኢትዮ ኤርትራው ጦርነት ተጠናቆ ነገሮች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች በተመለሱበት ማግስት ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረው ካባድ አገራዊ ችግሮች ጋር ፊት ለፊት ሊጋፈጥ ግድ ብሎት ነበር።
በመሆኑም የወቅቱ ኢህአዴግን ከላይ ሆኖ ሲዘውር ነበረው ሕወሓት መስራች እና ነባር አመራሮች ወደ ኹለት ጎራ ተከፍለው ሌሎች እህት ድርጅቶችን እስኪያውኩ ድረስ ተሰነጣጥቆ ነበር።በዘው ወቅት ታዲያ ለሕዝብ ጥያቄ በድህረ ጦርነቱ ወቅት አለባብሶ ሲያርስ ነበረው ኢህአዴግ ከፍተኛ ተቃውሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ሕዝብ አምርቶ ነበር።
ይህ ሁሉ ጉዳይ ታዲያ መንግሥት በድህረ ጦርነት ወቅት ሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ አጥብቆ ካለመስራት እና ዝግጁ ካለመሆን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። በመሆኑም አሁን በሥልጣን ላይ ሚገኘው ብልጽግና ፓርቲም ሆነ መንግሥት ካለፉት ኹነቶች ትምህርት በመውሰድ ከፍተኛ የሆነ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከባድ የሚሆነውን የሰላም ጊዜ አስተዳደር ከወዲሁ እንዲያቀለው እና አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር እንዲሠራ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በድህረ ጦርነት አካል ጉዳተኞች ቁጥር እንደሚጨምር፣ የወላጅ አልባ ሕጻናት ቁጥርም እንደሚያሻቅብ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ማሻቀባቸው እና ከፍተኛ መፍትሔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ሳይጨምሩ እንደማይቀሩ ይገመታል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ምንም እንኳን የረድኤት ድርጅቶች የሚያግዙት ቢሆንም መንግሥት ግን ከማስተባበር እና ከመከታተል አኳያ እንኳን ከባድ የሚባል ጉዳይ እንደሚገጥመው ከወዲሁ ይታወቃል።
ይህ ችግር ይባሱኑ ከባድ የሚደርገው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚሊዮኖችን ለሕልፈት የሚዳርገው ኮቪድ 19 አሁንም በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አገራት ላይ የቁጣ ዱላውን ማሳረፉን እንደተያያዘው መሆኑ ነው። ቀደም ሲል በከፍተኛ ሁኔታ መንግሥትም ሕዝብም በርብርብ ለመቆጣጠር ሰፊ ጥረት ሲደረግበት የነበረው ኮቪድ 19 ጭራሹኑ በአሁኑ ሰዓት ከእነ አካቴው የግችቶች በነበሩባቸው አካባቢዎች ሰዎች በተጋላጭነት ሲንቀሳቀሱም ተስተውለዋል። ይህ ደግሞ ተጨማሪ ጉዳይ ነው እና በድኅረ ግጭት ወቅት ማስተዳደሩ እንዳይቸግር መንግሥት ከወዲሁ ሊያስብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስተላልፋለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013


