በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሦስት ደረቅ ወደቦች ለማስገንባት የቦታ መረጣ እየተደረገ ነው

0
982

በኢትዮጵያ ከሚገኙት ስምንት ደረቅ ወደቦች በተጨማሪ ሦስት ደረቅ ወደቦችን ለማሥገንባት የቦታ መረጣ ጥናት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡

ጥናቱ በኢትዮጵያ እስካሁን ከተገነቡት ስምንት ደረቅ ወደቦች በተጨማሪ በየትኛው ቦታ ላይ ደረቅ ወደብ እንደሚስፈልግ ለመለየት ያለመ ነው ተብሏል።የበቦታ ልየታ ሥራ ላይ ያተኮረው ጥናቱ በየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል የደረቅ ወደብ ተደራሽነት እጥረትና ፍላጎት አለ የሚለውን የሚመልስ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አሸብር ኖታ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡

የቦታ ልየታ ጥናቱ እየተሠራ ያሚገኘው ኢትዮጵያ ያሏትን ደረቅ ወደቦች ወደ 11 ከፍ በማድረግ የገቢና ወጪ ንግዱን የተቀላጠፈ በማድረግ የምጣኔ ሀብት እድገትን ለማገዝ ነው ተብሏል።የቦታ ልየታ ጥናቱ ያስፈለገበት ምክንያት ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የገነባቻቸው ደረቅ ወደቦች በአዋጭነት ጥናት ቢገነቡም አንዳንዶቹ የሚያስተናግዱት ወጪና ገቢ ዝቅተኛ መሆኑ ተመላክቷል።በመሆኑም ወደፊት የሚገነቡት ደረቅ ወደቦች በየትኛው የኢትዮጵያ አካባቢ ላይ ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ለመለየት መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎት ድርጅቱ የቦታ አዋጭነት ልየታ ጥናቱን የሚመራ ክፍል በድርጅቱ ሥር ተቋቁሞ ጥናቱን እያስተባበረ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል።ጥናቱን የሚመራው ክፍል በኢትዪጵያ ሁሉም አካባቢዎች ላይ ዳሰሳ በማድረግ የሚሠራው ሥራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጥናቱን የሚሠራው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሆን፣ ጥናቱን በአጋርነት ከሚያግዙት አጋር ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን እንደሚገኝበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በጥናቱ የሚለየው የቦታ አዋጭነት ልየታ የወጪና ገቢ ንግድ በበቂ ሁኔታ ያለው፣ በአካካባቢው የሚመረት የምርት መጠንና የገብያ ልውውጥ፣ አጎራባች አገሮች የድንበር ቅርበትና ምቹነት እና ወደቡ በሚገነባበት አካባቢ የኢንዱስትሪ ምርታማነት መኖር የሚሉትን እንደመስፈርት መውሰዱ ተመላክቷል፡፡
ወደቡ የወጪና የገቢ ዕቃዎችን ከማስተናገድ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለንግድ መስፋፋትም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።በአካባቢው ከተሜነትን ማስፋፋትም ሌላው ጠቀሜታው ይሆናል፡፡

የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ሲገነባ የኢትዮጵያ ደረቅ ወደቦች ቁጥር ወደ ስምንት ያድጋል።ሞጆ፣ ቃሊቲ፣ ኮምቦልቻ፣ ገላን፣ድሬዳዋ፣ሰመራ እና መቀሌ ደረቅ ወደቦች ናቸው አሁን ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት።

ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር በመሆኗ ለወደብ ኪራይ የሚወጣውን በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ለማስቀረት ባለፉት 11 ዓመታት የደረቅ ወደብ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጋለች። የወደብ መቋቋም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በዓለም አገራት ውስጥ የሕዝብ ቁጥራቸው ከ100 ሚሊዮን የተሸገረ አገራት ቁጥር 11 ሲሆኑ ኢትዮጵያም ከእነዚሁ አገራት ውስጥ ትካተታለች። ይሁን እንጂ ከእነዚህ 11 አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የባህር በር የሌላት አገር መሆኗም በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ደረቅ ወደቦች በአገር ውስጥ መገንባትም ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በወደቦች ላይ የሚቆዩበትን እና ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ሚከፈለውን ክፍያ ከማስቀረት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይነገራል።

በተመሳሳይም ጉምሩክ እና የትራንስፖርት ወረፋዎች እንዲሁም ተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በአገር ውስጥ እስኪጨረሱ ድረስ በወደቦች ላይ ሚቆዩ እና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችም የሚኖርባቸውን ተመሳሳይ ያልተፈለገ ክፍያ በማስቀረት በአገር ውስጥ ገብተው በተመጣጣኝ ክፍያ የጉምሩክ ሒደታቸውን መፈጸም የሚያስችልም እንደሆነ ይታወቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here