የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሦስት መመሪያዎችን አሻሻለ

0
1545

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሦስት የኢንቨስትመንት መመሪያዎችን አሻሽሎ ማጽደቁን አስታወቀ። የተሻሻሉት መመሪያዎች መመሪያ ቁጥር 01/2013፣ መመሪያ ቁጥር 02/2013 እና መመሪያ ቁጥር 03/2013 ተብለው ሥያሜ ተስጥቷቸዋል።

መመሪያ ቁጥር 01/2013 ወደ ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወይም ክላስተር ማዕከል የሚገቡ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን ለመመልመልና የመሥሪያ ቦታ መጠን ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣ መመሪያ እንደሆኑ ቢሮው አስታውቋል። መመሪያ ቁጥር 02/2013 ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ለተሸጋገሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሥሪያ ቦታ ወይም መሬት ለመስጠትና መጠን ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣ መመሪያ ሲሆን፣ ሦስተኛው ለመካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማስፋፊያ ቦታ ለመስጠትና መጠን ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣ መመሪያ መሆናቸውን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ቻላቸው አቤልነህ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መመሪያ ቁጥር 1/2013 ለመካከለኛና ከፍተኛ የማምረት አቅም ላላቸው ባለሀብቶች የሚሰጠውን የመሥሪያ ቦታ ባቀረቡት ፕሮጀክት መሰረት መስተናገድ የሚችሉበትን ሁኔታ ያቀፈ ነው ተብሏል። በዚህ መመሪያ ከፍተኛና መካከለኛ የማምረት አቅም ያላቸው ባለሀብቶች የሚቀርቡት ጥያቄ በቴክኖሎጅ አቅም፣ በሚፈጥሩት የሥራ ዕድል መጠንና ባላቸው የካፒታል መጠን ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በመመሪያው ላይ ተደንግጓል።

መመሪያ ቁጥር 02/2013 ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪ ተሰማርተው ሲሠሩ የነበሩ አነስተኛ አምራቾች ወደ መካከለኛ አምራችነት ለመሽጋገር በሚፈልጉበት ጊዜ የማስፋፊያ ቦታ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ሲሆን፣ ሽግግር ማድረግ የሚፈልጉ አምራቾች በተሰማሩበት ሥራ ላይ የካፒታል እድገት በመጨር ተዛማጅ ሥራ ለመሥራት በሚፈልጉበት ጊዜ የሚሽጋገሩበተን መሰፈርት ያቀፈ መሆኑን ቻላቸው ጠቁመዋል።

ሦስተኛው መመሪያ ቁጥር 03/2013 መካከለኛና ከፍተኛ አምራቾች ከተሰማሩበት ዘርፍ በተጨማሪ ተመጋጋቢ በሆኑ ሥራዎች ላይ ለመሠማራት በሚፈልጉበት ጊዜ ተጨማሪ የቦታ ጥያቄን ለማስተናገድ የተዘጋጀ መመሪያ ነው ተብሏል።

በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ ተብለው የሚጠቀሱ ውስን ቦታዎችን በአግባቡ ለአምራቾች ለማስተላለፍ የመመሪያዎቹ ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል። አምራች ባለሀብቶች በሚያቀርቡት ፕሮጀክት ልክ ተመጣጣኝ ቦታ ለመስጠት መመሪያዎቹ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉም ተብሏል። የመሥሪያ ቦታ አሰጣጥ መስፈርት የተከተለ ከማድረግ በተጨማሪ አምራቾች በሚያቀርቡት ፕሮጀክት ልክ በክልሉ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ከተሞች ቦታ ያገኛሉ ብሏል።

ከፍተኛ የኢንዱሰትሪ ፕሮጀክት የሚያቀርቡ ባለሀብቶች በክልሉ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ከተማ ተብለው በተመደቡት ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃንና ኮምቦልቻ ከተማ የመሥሪያ ቦታ እንደሚያገኙ ቻላቸው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ዕድገት ለማረጋገጥና በክልሉ ተመጋጋቢ የሆነ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም ፣ በማስፋፋት እና በማሳደግ የክልሉንና የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በየደረጃው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መመሪያዎቹ እንዲሻሻሉ መደረጉ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ሥራ ፈላጊ ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የተለያዩ ድጋፎችን በማግኘት የተሻለ ሀብት ሲያፈሩና የሥራ ዕድል ሲፈጥሩ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ በመሸጋገር የኢትዮጵያን እና የክልሉን ምጣኔ ሀብት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በሚኖራቸው ድርሻቸውን ውጤታማ መሆን አንዲችሉ የመሥሪያ ቦታ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ የማስፋፊያ ቦታ በተመለከተ ወጥ አሠራር ባለመኖሩ ሦስቱ መመሪያዎች እንዲሻሻሉ መደረጉን ቻላቸው ገልጸዋል።

መመሪያዎቹ ከወቅቱ የልማት ግብ ጋር የተገናዘበና ለኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማስፈለጉ፣ በዘርፉ የተሰማሩ የመካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሀብት እንዳያፈሩና ለውጥ እንዳያመጡ እንቅፋት የሆነባቸውን ጉዳዮች ለመቅረፍ በሚያስችሉ መመሪያዎች መሆናቸው ተመላክቷል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከዚህ በፊት የመሬት ጥያቄ ለሚያቀርቡ ባለሀብቶች የመሥሪያ ቦታ ፈቃድ የሚሰጠው በዘፈቀደ እንደነበር ያስታወሱት ቻላቸው አዲስ የተሻሻሉት መመሪያዎች የመሥሪያ ቦታ በዘፈቀደ ከመስጠት ይልቅ የቀረቡ ፕሮጀክቶችን በመመሪያዎቹ ላይ በተደነገጉ መስፈርቶች መሰረት ለማስተናገድ ያስችላል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here