የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጋቸው ውይይቶችና ንግግሮች መሠረት አብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች ጥበቃ ሊሟላላቸው መቻሉን ጠቁሞ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌና በደቡብ ክልሎች 98 የምርጫ ክልሎች ጥበቃ ስላልተመደበላቸው በአስቸኳይ እንዲያሟሉላቸው አሳሰበ፡፡
ቦርዱ የካቲት 25/ 2013 ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ጥበቃ ያልተመደበላቸው የምርጫ ክልል ቢሮዎች በኦሮሚያ ክልል 21 የምርጫ ክልሎች፣ በሶማሌ ክልል 31 የምርጫ ክልሎች፣ በአማራ ክልል 40 የምርጫ ክልሎችና በደቡብ ክልል ስድስት የምርጫ ክልሎች ጥበቃ አልተመደበላቸውም፡፡ በመሆኑም በአስቸኳይ ጥበቃ እንዲመደብላቸው አሳስቧል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ 673 የምርጫ ክልሎችን በመክፈት የዕጩዎች ምዝገባን እያከናወነ መሆኑን አስታውሶ፣ የምርጫ ክልሎችን ደኅንነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነት የክልልና የከተማ መስተዳድሮች መሆኑን አስታውቋል።
ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት የምርጫውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችና ንግግሮችን እያደረገ የቆየ መሆኑን፣ በዚህም መሠረት አብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች ጥበቃ እንደተሟላላቸው ገልጿል።
ነገር ግን ከላይ በተገለጹት አራት ክልሎች 98 የምርጫ ክልሎች፣ አስፈላጊውን የደኅንነት ከለላ ከክልል መንግሥታቱ እያገኙ አለመሆናቸውን አስረድቷል፡፡
ቦርዱ ክልሎች በአስቸኳይ ለቀሪ የምርጫ ክልል ቢሮዎች የጥበቃ ምደባ እንዲያከናውኑ አሳስቦ፣ ሳይመድብ ቀርቶ በጥበቃ አለመኖር ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ የምርጫ አፈጻጸም ችግሮች ቢያጋጥሙ የክልሎቹ መስተዳድሮችና የፀጥታ አካላት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ አስገንዝቧል።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013



