በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ትብብር በከተማ መሬት ጉዳይ የሚስተዋሉ አለመግባበቶችን መፍታት የሚያስችሉ ጥናቶች ይፋ ተደረጉ። ጥናቶቹ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ፕሮጀክትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል አማካኝነት የተሰሩ ናቸው።
በኹለቱ ተቋማት የተሰሩት 12 የጥናት ውጤቶች የከተማ መሬት ላይ ፖሊስ እንዲዘጋጅና ውይይት እንዲካሄድ እንዲሁም ለተለያዩ ምርምሮች ግብዓት ፈር ቀዳጅ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል።
ጥናቶቹ ይፋ በሆኑበት መርሃ ግብር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል መምህርና የጥናቱ አስተባባሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙራድ አብዶ እንዳሉት ከዚህ ቀደም የወጡ የከተማ መሬት ሕግጋት ሲፈተሹ ጉድለቶች ይታይባቸዋል። ሕግጋቱ በአወጣጥ ሂደታቸው፣ ግልጸኝነትን በተመለከተና አፈጻጸማቸው ላይ ጉደለት እንደሚታይባቸው ጠቁመዋል።
ተቀባይነት ያለው የከተማ ፖሊሲ የቤቶች ልማት ችግርን፣ በምግብ ዋስትና፣ በአካባቢ ጥበቃና በማኅበራዊ ፍትህ የሚታዩ ጉድለቶችን የሚፈታ መሆን እንዳለበትም ተመላክቷል። ጥናቶቹ ሲጠና የታዩ ጉድለቶችን በሚፈታ መልኩና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት በሚሆኑበት ሁኔታ መሆኑን ነው የተጠቆመው።
የሚመለከተው የመንግሥት አካል የምርምር ውጤቶቹን ወደፊት ለሚወጡ ፖሊሲዎችና ማሻሻያዎች በግብዓትነት ሊጠቀምበት መግባባት ላይ መደረሱንም ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



