ዓለማቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጃትና አቀራረብ ደረጃ በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ተጠየቀ

0
1604

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጃት እና አቀራረብ ደረጃዎች (ኢንተርናሽናል ፋይናንሺያል ሪፖርቲንግ ስታንድርድ( IFRS) በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት የሚጠይቅ ረቂቅ ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ያሉት የኦዲት ባለሙያዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆን እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎችን አሟልቶ ለመተግበር እንዲሁም በንድፈ ሃሳብ ትምህርት እና በተግባራዊ አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በዘርፉ ላይ ያተኮረ ስርዓተ- ትምህርት ተዘጋጅቶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ የሚጠይቅ ረቂቅ መዘጋጀቱን የቦርዱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአካውኒቲንግ የተመረቁ ባለሙያዎች አጠቃላይ ተቀባይነት ያላቸው የሂሳብ አዘገጃጀት መርሆችን (GAAP) በዩኒቨርስቲ የሚሰለጥኑበት ሙያ በመሆኑ ስለ IFRS ሳያውቁ እና ሳይሰለጥኑ ወደ ስራው አለም መቀላቀላቸው እና በስራው አለም የሚጠብቃቸው አሰራር የተለየ መሆኑ ባለሙያዎቹ ለአዲሱ አሰራር እንግዳ ይሆናሉ ተብሏል።

የአካውንቲንግ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ60 ዓመታት በላይ ሲሆን ፣ ሙያውን ዓለም ከደረሰበት የጥራት ደራጃ ለማድረስ እና አገሪቱን ከሌሎች ዓለማት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በሙያው ውስጥ ያሉ መምህራን እና ተማሪዎች ስለ IFRS ስልጠናዎች መስጠት ብቻ በቂ ባለመሆኑ IFRS በአካውንቲንግ ትምህርት ውስጥ ተካትቶ በመደበኛነት እንዲሰጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ሂሳብ እና ኦዲት ቦርድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን፣ ስርዓተ ትምህርቱን በመቀየር IFRS አንዱ የትምህርት አካል እንዲሆን ረቂቅ መዘጋጀቱን አቶ አበበ ገልፀዋል።

ይህንን ስርዓተ ትምህርት ለመቀየር ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ በሁሉም የባለድርሻ አካላት እና በገንዘብ ሚኒስትር ተገምግሞ፣ በኢዲተር ቦርድ ጥናት ተደርጎ የተሰራው ረቂቅ 12 አባላት ባሉት የቦርዱ ዳይሬክቶሬቶች ፀድቆ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚላክ አቶ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ያላቸው የመንግስት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት IFRS እያሰለጠኑ ሲሆን ይህ ስልጠና በተማሪዎቹ ላይ የተወሰነ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆንም በስርዓተ ትምህርቱ መደገፉ የበለጠ የበቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ያስችላል ሲሉ አቶ አበበ ገልፀዋል።

መንግሥት የአገሪቱ የሒሳብና የኦዲት ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ስታንዳርድ እንዲመራ በማሰብ፣ ይህንኑ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሪፖርት አደራረግ ሥርዓት እንዲከተሉ የሚያደርግ ሥርዓት መተግበር ጀምሮ ነበር።
ይህንኑ ሥራ የሚመራ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ IFRS በኢትዮጵያ እንዲተገበር በ2007 በፀደቀው አዋጅ መሰረት በሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ተቋቁሞ የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ሥርዓቱን ሲከታተል ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የአለማችን ሀገራት IFRSን የተቀበሉ ሲሆን ከእዚህ ውስጥ 13ቱ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው። በፈረንጆቹ 2001 በዓለም አቀፍ የአካውንቲንግ ደረጃዎች ቦርድ (ኢንተርናሽናል አካውንቲንግ ስትንደርድ ቦርድ IASB) ተቀባይነት ያገኘ የሂሳብ ስርዓት ሲሆን ጥራት ያለው የሂሳብ ሪፖርት ለማቅረብ የተመቸ እንዲሁም የንግድ እና ኢንቨስትመንትን የሚፈጥር የፋይናንስ መረጃ አቀራብ ስርዓት ነው። በአበዳሪዎች እና በተበዳሪዎች መካከል መተማመን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በሂሳብ አያያዝ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን መለየት የሚያስችል ስርዓት እንደሆነ አቶ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here