ኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ የዴሞክራሲ ስርዓትን እየገነባን ነው ተብሎ አገር መንግሥት ምስረታ ከተጀመረበት ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ያልጠሩ እና እርስ በራሳቸው የተደበላለቁ አካሔዶችን ስትመለከት ኖራለች። ዴሞክራሲን ለማስፈን፤ ጭቆናን ለመታገል የግፍ አገዘዝ አንገፍግፎኛል ያለው ቡድን ጥራኝ ዱሩ ብሎ ነፍጥ አንግቦ ጫካ ከከተመ በኋላ የተነሳበትን ዓላማ ለማንበር በርካታ መስዋዕትነትን ከፍሎ አገር ማስተዳደር ተራውን ከወታደራዊው መንግስት በመረከብ አሐዱ ያለበት የ1983 ግንቦት ውር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሲዘከር የሚኖር ታሪካዊ ቀን ነው።
ይህ ስልጣን የያዘው አካል ታዲያ አገርን ከጭቆና ለማላቀቅ፣ ዜጎች በነጻነት መብታቸው የሚከበርበትን የዴሞክራሲ ግንባታን ለማሳለጥ ነበር ወደ አራት ኪሎው ቤተ መንግስት የገባው። የተጠበቀውም በዛው ልክ ነበር። ግና ታሪክ ምስክር ነው እስከ 2010 መጋቢት ወር ድረስ የታሰበው እና በእውነታው መሬት ላይ ሲፈጸም የነበረው ተግባር በእጅጉ የተለያየ ነው። ይህም እያደር ከፍተኛ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አቀጣጥሎ፣ መሪው ፓረቲም ከመንበሩ ተሰናብቶ የተረፉትም ቅርጽ እና አቋም ቀይረው፣ ሕዝብንም በይፋ ይቅርታ ጠይቀው ሕዝብና አገርን እየመሩ ይገኛሉ።
የ27 ዓመቱ ኢህአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ‹‹በስብሷል፣ መታደስ ይገባዋል›› እና የመሳሰሉት ሀሳቦች በራሱ በአባላቱ ታምኖበት ለበርካታ ጊዜያት ጉባዔ ተቀምጧል፤ መክሯል ዘክሯል። ነገር ግን ጠብ የሚል ነገር ባለመምጣቱ ራሱን ሳያክም በራሱ ደዌ ተይዞ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል። በአንድ ትውልድ ጉዞው ታዲያ ኢህአዴግ እንደ ገዢ የፖለቲካ ድርጅት (በእርግጥ ኢህአዴግ የፓርቲነት ስያሜ ሳያገኝ ግንባር እንደሆነ ነበር ዘመኑን ያጠናቀቀው) አገርን ለማስተዳደር ቻለ እንጂ የመንግስት እና ፓርቲ ልዩነቶች ተለይተው ባለመታወቃቸው በተለያዩ ጊዜያት የኢህአዴግ ድርጅት እና ጽሕፈት ቤት የመንግስትን ሀብት ሲጠቀሙ እና በማናለብኝነት ሲያዙበት በይፋ ይታይ የነበረ በእጅጉ ወንጀል የሆነ ተግባር ነበር።
በኢሕአዴግ የገዢነት ዘመን ከመንግስት ድርጅቶች ይልቅ የፓርቲ ድርጅቶች በእጅጉ የጎለብቱበት፣ ሕዝብን ዳር በማስወጣት ፓርቲ አባላት ብቻ ተጠቃሚ የሆኑበት፣ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ሀብት ላይ በፍትሀዊነት እንዳይጠቀሙ የበይ ተመልካች እንዲሆኑ የደረገ ተግባር ዘመን እንደነበር የሚታወስ ነው።
በምርጫ ወቅትም እስከዛሬ በተደረጉ አምስት አገራዊ ምርጫዎች ላይ ኢህአዴግ የመንግስትን ሀብት ለድርጅቱ የምርጫ ቅስቀሳ ማዋያነት ያለከልካይ ሲጠቀም እና በተለይም ደግሞ ከመሐል አገር በራቁ ስፍራዎች በግብር ከፋዩ ሕዝብ የተገዙ የመንግስትና ሕዝብን ንብረቶችን በድፍረት በመጠቀም ምረጡኝ ቅስቀሳዎችን ሲያካሒድ የኖረበት ዘመን ሩቅ አይደለም። በአዲስ አበባም የከተማ አውቶብሶችን ጭምር በኪራይ በሚል ሰበብ እንዳሻው ሲጠቀምበት የተስተዋለበት አይን ያወጣ የማን አለብኝነት ተግባር ሲካሔድ መቆቱን ለማውሳት ሕያዋን ዛሬም እንገኛለን። ይህን ያመጣው ደግሞ ከመንግስት ማንአለብኝነት ባለፈ የፓርቲ እና የመንግሥት ልዩነት እና ድንበር በጉልህ አለመሰመሩ እንደነበር አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። የምርጫ ቅስቀሳዎችም ጭምር በመንግሥት የደኅንነት አባላት ሲታጀብ እንደነበርም በጉል የሚታወስ ጉዳይ ነበር። በአሁኑ የለውጥ መንግሥት ዘመንም ይህ ጉዳይ/ችግር በአንዳንድ ስፍራዎች እየታየ በመሆኑ አዲስ ማለዳ ከወዲሁ ሊታረም ይገባል ስትልም አቋሟን ታስታውቃለች።
ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ገዢው ፓርቲ በምርጫ ተሳትፎ እና ተወዳድሮ አብላጫ ድምጽ በማግኘት አገር የማስተዳደር ዕድሉን እንዲያስቀጥል በማድረግ ረገድ ሰላማዊ ቅስቀሳ እንዲያደርግ ቢጠበቅም ነገር ግን የመንግስት ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም እና የሕዝብን የማገልገያ የስራ ሰዓታት በመበድለ መሆን እንደሌለበት ሊታሰብበት ይገባል።
በዚህ ረገድ የመንግስት ሐብት ወይም የሕዝብ ሐብት እኩል ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ ገዢውን ፓርቲ ብቻ በማገልገል ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ደግሞ የሚያገል መሆን እንደሌለበት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ይህ በቀደሙት ጊዜያት ከነበረው አስተዳደር ወጥተው ለአገር ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን ባሉ አካላት የተመሰረተው አዲሱ አመራር ይህን ነገር ከወዲሁ አምርሮ ሊታገለው እደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባች። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ሕዝብ ወይም አገር ከአምባገነናዊ የፓርቲ መንግስት አዙሪት እንዳልወጣች ይታሰባል።
በተለይ ደግሞ አሁን ምርጫው እየቀረበ በመጣበት ወቅት በሚደረጉ የቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴዎች ፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዢውን ጨምሮ) ከራሳቸው የሐብት ምንጭ በሚገኝ ሐብት ብቻ የምርጫ እንቅስቃሴዎቻቸውን መፈጸም ይኖርባቸዋል እንጂ የመንግስትን እና የሕዝብን ሀብት ለአንድ ፓርቲ የምርጫ ሂደት ማካሔጃ ማድረግ በእጅጉ የተወገዘ እና ከባድ ጥፋትም የሚያስከትል፣ ገዢውን ፓርቲም ትዝብት እና ወቀሳ ላይ የሚጥል እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት የጸጥታ አካለት፣ የፍትህ ተቋማት እና ሌሎች መንግስታዊ መዋቅሮች ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ በሕግ ጥላ ስር የሚገኙትን ጨምሮ መላውን ዜጋ ዕኩል ለማገልገል የተቋቋሙ መሆናቸው ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተደጋጋሚ እንደሚናገሩት ተቋማትን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ርብርብ የሚያስፈልግ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ አካሔድ ታዲያ ተቋማት የራሳቸውን መርህ ተከትለው በፓርቲ ግፊት ሳይወሰዱ ሁሉንም እኩል አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሆኑ ማድረግ ተቀዳሚው ተግባር መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል። ነገር ግን ከዚሁ ሁሉ አስቀድሞ በዚህ ተቋማዊ ግንባታ ላይ መንግስት እና ፓርቲን የሚለየው መስመር ደመቅ ተደርጎ ሊሰመር እና አንዱ አንዱን አልፎ የማይሄድበት እና ሁሉም መስመሩን ተከትሎ የሚሰራበት መንገድ መፍጠር ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው።
አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ከተሰራ እና ከታሰበ ይህ በቅድሚያ በሁሉም ተቋማት ዘንድ ተሰርቶ ሊታይ ይገባል። ምርጫ ጋር በተያያዘም ገዢውን ፓርቲ በመወከል የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉ አካላትም ሕዝብን የማገልገያ የስራ ሰዓታቸውን በመበደል ሳይሆን ያላቸውን የስራ ሰዓት በማይነካ እና ስራ በማይበደልበት መንገድ መሆን እንዳለበትም አዲስ ማለዳ ታምናለች። በቀጣይም ይህን አይነት እርምጃ ከተወሰደ መንግስት እና ፓርቲ ልዩነታቸው ታይቶ እና ተሰምሮ አንዱ በአንዱ ላይ በላይ ወይም አዛዥ ሳይሆን ተገልጋይ እና አገልጋይ እንዲሆኑ መሰራት ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አቋሟን ተገልጻለች።
ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013


