በኢትዮጵያ በየአመቱ ነፍሰ ጡር ከሚሆኑ 3.2 ሚሊዮን እናቶች መካከል 1.3 ሚሊዮን ያህሉ በቤታቸው እንደሚወልዱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህን ያክል ቁጥር ያላቸው እናቶች በቤታቸው መውለዳቸው ደግሞ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እየሰራን ነው ለሚለው ጤና ሚኒስቴር አዳጋች ሆኖብታል ሲሉ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሰረት ዘላለም (ዶ/ር) ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
‹አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም› በምትለው ኢትዮጵያ፣ በአመት ከ11ሺሕ በላይ እናቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡም የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሕብረተሰቡን በማስተማር እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄድ የተወጡት ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ አሁንም የበለጠ የማሕበረሰብ ንቅናቄ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የወሊድ መቆጣጥሪያ አጠቃቀምን በተመለከተም መድረስ ያለብን ደረጃ ባንደርስም መሻሻል ግን እንዳለ ዶክተር መሰረት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚመዘገብባቸው ቀዳሚ አገራት ተርታ ትሰለፋለች።
የእናቶችን እና የህጻናትን ሞት ቁጥርም ለመቀነስ ጤና ሚኒስቴር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ እንደሚሰራም መሰረት ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013


